ቢኒያም አሰፋ በዓመቱ ሁለተኛ ሃትሪክ ሠራ
ጥር 17, 2007

  •  “ምንም እንኳ ሃትሪክ ብሰራም ክለባችን በማሸነፉ በይበልጥ በጣም ደስ ብሎኛል።“ ቢኒያም አሰፋ

  • “ተጫዋቾቼ የነገርኳቸውን ታክቲክ መተግበር ስላልቻሉ በሰፊ የግብ ልዩነት ልንሸነፍ ችለናል። ” የወልድያ ከነማ አሰልጣኝ ሰብስቤ ይባስ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ትናንት በአዲስ አበባው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ሲካሄድ ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች ተካሂደውበታል። በርካታ ትዕይንቶችና ግቦች የተቆጠሩበት ጨዋታ የተካሄደው ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከወልድያ ከነማ ያካሄዱት ጨዋታ ነው። አማካዮቹን ዳዊት እስጢፋኖስንና ጥላሁን ወልዴን ጨምሮ ተከላካዩ ኦሊቨርን በጉዳት ያላሰለፉት ኢትዮጵያ ቡናዎች አምስት ለሁለት በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፈው ወጥተዋል። 
Binyam Asfew After Scoring His Hatrick

በእለቱ የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ ቢኒያም አሰፋ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሶስታ ሰርቷል። በፕሪሚየር ሊጉ የ13 ሳምንታት ጉዞ በአንድ ጨዋታ ሶስት ግቦችን ያስቆጠረ ተጫዋች ባለመኖሩ ቢኒያም አሰፋ ትናንት ያስቆጠራቸው ሶስት ግቦች በዓመቱ የመጀመሪያው የፕሪሚየር ሊጉ ሃትሪክ ሆኗል። ከአራት ወራት በፊት በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ተዘጋጅቶ በነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ካስትል ዋንጫ ኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢት ሲጫወቱ ቢኒያም አሰፋ ሶስቱንም የቡና ግቦች ማስቆጠሩ ይታወሳል። የትናንትናውን ጨምሮ ቢኒያም አሰፋ በአምስት ወራት ልዩነት ሁለተኛውን ሃትሪክ ለክለቡ መስራት ችሏል። 

ከጨዋታው በኋላ አስተያየቱን ለጋዜጠኞች የሰጠው ቢኒያም አሰፋ “ምንም እንኳ እኔ ሃትሪክ ብሰራም ክለባችን በማሸነፉ በጣም ደስ ብሎኛል። በዚህ ዓመት በርካታ ግቦችን ለማስቆጠሬ የረዳኝም የክለባችን አጨዋወት ነው። የውድድር ዓመቱንም ኮከብ ግብ አግቢ ሆኜ ለመጨረስ እጫወታለሁ።” ሲል ተናግሯል።  

በእለቱ የተፈጠረው ሌላው ታሪክ ደግሞ ምንም እንኳ ወልድያ ከነማ የተሸነፈ ቢሆንም ፕሪሚየር ሊጉን ከተቀላቀለ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ጨዋታ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው በትናንቱ ጨዋታ ነው። የወልድያ ከነማው አሰልጣኝ ሰብስቤ ይባስ “ተጫዋቾቼ የነገርኳቸውን ታክቲክ መተግበር ስላልቻሉ በሰፊ የግብ ልዩነት ልንሸነፍ ችለናል። በሁለተኛው ዙር ቡድናችንን በሁሉም ቦታዎች ለውጥ አድርጎ በመቅረብ ከወራጅነት ለመውጣት እንጫወታለን” ብለዋል። 

ሌላው የእለቱ ክስተት ደግሞ ሁለቱ ቡድኖች ሲጫወቱ በኢትዮጵያ ቡና በኩል አንድም ተጫዋች የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ አለመመልከታቸው ሲሆን ክለቡም በዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ አምስት ግቦችን ከመረብ ያሳረፉት በትናንቱ ጨዋታ ነው። የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻ “ቡድናችን ካለፉት ስህተቶቹ ተምሮ ለጨዋታው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የገባ በመሆኑ ማሸነፍ ችለናል። ወልድያ ከነማ ምንም እንኳ በርካታ ጨዋታዎችን ቢሸነፍም ተጋጣሚዎቹን የሚፈትን ቡድን ነው። አህመድ ረሽድ ዋናውን ቡድን ከተቀላቀለ የመጀመሪያ ዓመቱ ላይ ቢሆንም እያሳየ ያለው ብቃት እጅግ አስደሳች ነው። እንደ ዳዊት እስጢፋኖስና ጥላሁን ወልዴ አይነት ተጫዋቾቻችን ከጉዳታቸው አገግመው ለጨዋታ ብቁ ሲሆኑልን ቡድናችን የበለጠ እየተጠናከረ ይሄዳል” ሲል ተናግሯል። 

ቀሪዎቹን የኢትዮጵያ ቡና ግቦች ሃብታሙ ረጋሳና አስቻለው ግርማ ሲያስቆጥሩ ለወልድያ ከነማ ደግሞ ብርሃኑ በላይና አብይ በየነ አስቆጥረዋል። የኢትዮጵያ ቡናው ወጣት የግራ መስመር ተከላካይ አህመድ ረሽድ ወይም ሽሪላው የጨዋታው ኮከብ ሆኖ አምሽቷል። 

 ከቀኑ አስር ሰዓት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በሲዳማ ቡና መካከል የተካሄደው ጨዋታ አንድ እኩል በሆነ ውጤት ተጠናቋል። በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የጸጋዬ ኪዳነማሪያል ልጆች በተጋጣሚዎቻቸው የግብ ክልል ላይ ደጋግመው ቢመላለሱም አንድ ጊዜ እንኳ ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኗቸዋል። በአንጻሩ የዘላለም ሽፈራው ልጆች በመሃል ሜዳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ይዘው ነበር እስከ እረፍት የቆዩት። 

ከእረፍት መልስ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የአጨዋወት ለውጥ አድርገው የገቡ ሲሆን በተለይ ሲዳማ ቡና አማካዩ እንዳለ ከበደ እናቱ ባለፈው ሳምንት ህይወታቸው በማለፉ ሃዘን ላይ በመሆኑ አሰልጣኙ ከመጀመሪያውም አጨዋወቱን ቀይሮ ነበር የገባው። የሲዳማ ቡናው የግራ መስመር ተከላካይ ሞገስ ሰለሞን የንግድ ባንክ ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ ያቀበለውን ኳስ አንዷለም ንጉሴ አቤጋ በግሩም ሁኔታ መረብ ላይ በማሳረፍ እንግዳው ቡድን የግብ ብልጫ ወሰደ። አንዷለም ግብ ከማስቆጠሩ በፊት ንጹህ የግብ እድል ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀረ እንጅ የግቡን ብዛት ሁለት ያደርስ ነበር። 

የሲዳማ ቡናው አምበልና ግብ ጠባቂ ለዓለም ብርሃኑ የሰራውን ጉልህ ስህተት ተጠቅሞ ፍሊፕ ዳውዝ ንግድ ባንክን አቻ ያደረገች ግብ አስቆጠረ። ፍሊፕ ትናንት ያስቆጠራት ግብ በዓመቱ ያስቆጠራቸውን ግቦች ብዛት ስድስት አድርሳለታለች። በእለቱም የግቡ አግዳሚ ባይመልስበት ኖሮ ተጨማሪ ግብ የሚያስቆጥርበት እድል አግኝቶ ነበር። የሲዳማ ቡናው ተከላካይ ሞገስ ሰለሞን በቀይ ካርድ የተሰናበተ ተጫዋች ሆኗል። 


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Adu [1123 days ago.]
 Bini Jegna Enbelawalene

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!