ጠንካራዎቹ የደቡብ ክልል ክለቦች
ጥር 19, 2007

 
ክፍል ሁለት

በትናንትናው የጋዜጣችን እትም የደቡብ ኢትዮጵያ ክለቦችን ጥንካሬ በተመለከተ መጠነኛ ዳሰሳ ማቅረባችን ይታወሳል። በዛሬው እትማችን ደግሞ በተጨማሪ ነጥቦች ላይ እንወያያለን። 

ለክለቦቹ ጥንካሬ ምንጭ ነው ተብሎ ከሚቀርበው ምክንያት አንዱ ክለቦቹ ህዝባዊ መሆናቸው ነው። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በዘንድሮው የውድድር ዓመት ለተጫዋቾች ዝውውር ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ወጭ አድርጎ  ውጤት ማስመዝገብ የተሳነው ሃዋሳ ከነማ ደጋፊዎች ናቸው። ክለቡ ውጤት ማስመዝገብ ባለመቻሉ በቅርቡ አሰልጣኙን እንዲያሰናብት የተገደደውና በምትኩ አዲሴ ካሳን እንዲቀጥር ከደጋፊዎቸ በደረሰው ጫና ነው። 

በዚህ ዓመት አሰልጣኝ በማሰናበትና ሌላ በመቅጠር ሃዋሳ ከነማ የመጀመሪያውና ብቸኛው ክለብ ባይሆንም የሃዋሳ ከነማን ለየት የሚያደርገው ግን ከላይ እንደገለጽኩት በደጋፊዎች ጫና መሆኑ ነው። ከሃዋሳ ከነማ በፊት አሰልጣኞቻቸውን ያሰናበቱት ደደቢትና ወልድያ ከነማ ሲሆኑ እነዚህ ሁለት ክለቦች ግን አሰልጣኞቻቸውን የቀየሩት ከክለቦቹ አመራሮች በቀረበ ጫና እንጅ ከደጋፊዎች በቀረበ አይደለም። 

የክለቦቹ ሌላ ገጽታ

የደቡብ ኢትዮጵያን በፕሪሚየር ሊግ የሚወክሉት አራቱ ክለቦች ከጥንካሬያቸው በስተጀርባ የሚነሳባቸው ደካማ ጎንም አላቸው። የክለቦቹ የመጀመሪያው ደካማ ጎናቸው ቡድናቸውን በሀይል አጨዋወት ላይ መመስረታቸው ነው። ከሃዋሳ ከነማ ውጭ ሌሎቹ ቡድኖች የተገነቡት በቴክኒካል አጨዋወት ላይ ሳይሆን ጉልበትን ቀላቅለው በመጫወት ነው። እንደዚህ አይነት አጨዋወት የሚጠቀሙ ክለቦች ኳስን መሰረት አድርገው በሚጫወቱ ክለቦች ላይ አስቸጋሪ አጨዋወትን በመጫወት የራሳቸውን ውጤት አስጠብቀው የሚወጡ ክለቦች ናቸው። ለአብነት ያህል በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እንደ ስቶክ ሲቲና ሀል ሲቲ አይነት ክለቦች እንደ አርሴናልና ማንቸስተር ዩናይትድ ያሉ ታላላቅ ክለቦችን የሚፈትኗቸው ባላቸው አስቸጋሪ የጨዋታ ስልት የተነሳ ነው። የደቡብ ኢትዮጵያ ክለቦችም በአጨዋወታቸው ላይ እንደ እንግሊዞቹ ስቶክና ሃል ሲቲ አይነት አጨዋወት በመጠቀማቸው ነው እያሸነፉ የሚወጡት ተብለው ይተቻሉ። 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክለቦች ላይ የሚነሳው ሌላው ደካማ ጎን ደግሞ ክለቦቹ እስከ ውድድር ዓመቱ አጋማሽ በጥንካሬ ከተጓዙ በኋላ በቀሪው የውድድር ጊዜ ወገቤን የማለት አመል አለባቸው እየተባሉ ነው። ለአብነት ያህልም ባለፈው ዓመት ወላይታ ድቻ እስከ ውድድር ዓመቱ አጋማሽ ድረስ በጥንካሬ ቢጓዝም በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ይዞ ያጠናቀቀው ደረጃ ግን ከአስረኛ ብዙም ያልበለጠ ሆኖ ነው። በ2004 የውድድር ዓመት ለፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ ይበቃል ተብሎ የነበረው ሲዳማ ቡና ውድድሩ ሊጠናቀቅ አምስት ጨዋታዎች እስኪቀረው ድረስ ዋንጫውን የማንሳት እድል ከፊቱ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ ግን ከሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ በብዙ ማይል ርቆ ነበር ያጠናቀቀው። ሃዋሳ ከነማም ቢሆን ተመሳሳይ ልምድ ነው ያለው። ክለቦቹ ያለፈውን ደካማ ታሪካቸውን ቀይረው በዚህ ዓመት የያዙትን ጥንካሬ ይዘው መጓዝ ይችሉ እንደሆነ ወደ ፊት የምናየው ይሆናል። 

ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ የክለቦቹ ትልቁ ድክመት ተብሎ የሚወሰደው ኮከቦቻቸውን ጠብቀው አለማቆየታቸው ነው። ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ ቢያድግልኝ ኤሊያስንና ሲሳይ ባንጫን ጨምሮ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የክልሉ ክለቦች ኮከብ ተጫዋቾቻቸውን ለታላላቆቹ የአዲስ አበባ ክለቦች በመሸጥ በምትኩ ከአዲስ አበባዎቹ የተገፉ ተጫዋቾችን ይገዛሉ። ከቢያድግልኝ ኤሊያስና ሲሳይ ባንጫ በተጨማሪ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ደጉ ደበበ፣ አዳነ ግርማና በሀይሉ አሰፋ እንዲሁም የቀድሞው የደደቢት አጥቂ ጌታነህ ከበደም ከደቡቦቹ ክለቦች የለቀቁት በኮከብነት ዘመናቸው ነው። ይህ የሆነው ደግሞ ክለቦቹ ካላቸው የበጀት ጉዳይ ቢሆንም ለዋንጫ እንጫወታለን እስካሉ ድረስ አካሄዳቸውን ሊያስተካክሉ የሚገባ ጉዳይ ነው። 
   
ይርጋ አበበ 
ኢትዮ ፉትቦል


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!