የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክለቦችንና ጋዜጠኞችን አመሰገነ
ጥር 20, 2007

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታዲየም ስድስት የአዲስ አበባና ሁለት የክልል ክለቦችን ያካተተ የእግር ኳስ ውድድር ማካሄዱ ይታወሳል። የአዲስ አበባ ከተማ ካስትል ዋንጫ የሚል ስያሜ የተሰጠውን ዋንጫ በአሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማሪያም የሚመራው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊነት መጠናቀቁ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ትናንት ምሽት በራስ ሆቴል ባደረገው የምስጋና ፕሮግራም “ውድድሩ ካለፉት ዓመታት በተሻለ ፉክክር የተካሄደ ነበር” ያሉት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ አማረ ማሞ “ለውድድሩ ድምቀት የመገናኛ ብዙሃን የተወጡት ሙያዊ ግዴታ ሊመሰገን ይገባዋል” ብለዋል። ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም “መገናኛ ብዙሃን ለውድድሩ ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን በመስጠታቸው በውድድሩ ታላላቅ ተጫዋቾች መሳተፍ ችለዋል። ይህ ደግሞ ቁጥሩ በርከት ያለ እግር ኳስ ተመልካችን ወደ ስታዲየም እንዲገባ ስላስቻለ ፌዴሬሽናችን ከአንድ ሚሊዮን ያላነሰ ገንዘብ ከስታዲየም መግቢያ ማግኘት አስችሎታል” ሲሉ ተናግረዋል። አቶ አማረ ማሞ አክለውም ውድድሩን ስፖንሰር በማድረግ የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉትን ቢጂአይ ኢትዮጵያንና ሞሃ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪን ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ካስትል ዋንጫ ስምንት ክለቦች ተሳትፈው 16 ውድድሮችን ማካሄዳቸውን የገለጹት አቶ አማረ ማሞ በውድድሩ 54 ቢጫ ካርዶችና 10 ቀይ ካርዶች መመዘዛቸውንም ተናግረዋል። አቶ አማረ በውድድሩ የተመዘዙ ቢጫና ቀይ ካርዶች በዲስፐሊን በኩል መሰራት ያለበት የቤት ሥራ እንዳለብን ያሳያል ብለዋል።

ውድድሩን ለመመልከት ቦርሳቸውንና ኪሳቸውን ዳብሰው ወደ ስታዲየም ከገቡ ተመልካቾች ፌዴሬሽኑ ከአንድ ሚሊዮን ያላነሰ ገንዘብ መሰብሰቡን የገለጹት አቶ አማረ ማሞ ከተሰበሰበው ገንዘብ መካከል ለስድስቱ የአዲስ አበባ ከተማ ክለቦች እንደየደረጃቸው የሽልማት ክፍፍል አድርጓል። በፌዴሬሽኑ ክፍፍል መሰረት የዋንጫው ባለቤት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 15 በመቶውን ወይም 119‚345 ብር ሲደርሰው ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 79‚563 ብር ደርሶታል። ተከታዩን ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁት ፈረሰኞቹ ደግሞ 55‚694 ብር ደርሷቸዋል። የኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ ድርሻ ፌዴሬሽኑ ካገኘው ገንዘብ 10 በመቶና ሰባት በመቶ መሆኑን አቶ አማረ ማሞ ተናግረዋል። አራተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው መከላከያ ወደ 32ሺህ የሚጠጋ ገንዘብ ሲደርሰው አምስተኛና ስድስተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ደደቢትና ኤሌክትሪክ ክለብ እያንዳንዳቸው ወደ 24 ሺህ የሚጠጋ ገንዘብ ተበርክቶላቸዋል።
ፌዴሬሽኑ ለስድስቱ የአዲስ አበባ ክለቦች በድምሩ ከ334ሺህ ብር በላይ የሸለመ ቢሆንም ከጎንደርና ከናዝሬት ድረስ ተጉዘው በመምጣት በተጋባዥነት የተገኙት ዳሽን ቢራና አዳማ ከነማ ምንም አይነት የገንዘብ ሽልማት አለማግኘታቸው ፌዴሬሽኑን “ምን እየሰራ ነው?” አስብሎታል።

የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፈው መስከረም መጨረሻ ላይ ባካሄደው ዘጠንኛው የአዲስ አበባ ከተማ ካስትል ዋንጫ ውድድር ከተመልካቾች የስታዲየም መግቢያ ካርድ በተጨማሪ ከቢጂአይ ኢትዮጵያ 350 ሺህ ብርና ከሞሃ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ 100 ሺህ ብር በስፖንሰርነት ማግኘቱን በምስጋና ፕሮግራሙ ላይ ተገልጿል።  

ዜና ዘገባ፦ይርጋ አበበ
ኢትዮ ፉትቦል


ethioootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!