ነገ እሁድ የሚደረጉት የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች በጉጉት ይጠበቃሉ የደረጃ ለውጥም ያስከትላሉ ተብሎ ይጠበቃል
ጥር 23, 2007

በፕሪሚየር ሊጉ ከሚሳተፉት ቡድኖች  ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ደደቢት ለብሄራዊ ቡድን በዛ ያሉ ተጫዋቾችን በማስመረጣቸው ምክንያት ወደፊት የተላለፉት ቀሪ የፕሪሚየር ሊጉ ሶስተኛ ዙር ጨዋታዎች ነገ ይደረጋሉ። ነገ የሚደረጉት ጨዋታዎች የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች ይሆናሉ። ጨዋታዎቹ የደረጃ ለውጥ የሚያስከትሉ በመሆናቸው በተመልካች ዘንድ በጉጉት  እንዲጠበቁ አድርጓቸዋል።

አዲስ አበባ ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከኤሌትሪክ  እንዲሁም  ወላይታ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ዲቻ  የሚያደርጉት ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረትን የሚስቡ ናቸው። ሐዋሳ ላይ በሐዋሳ ከነማና ደደቢት መካከል ለሚደረገው ጨዋታም ሁለቱም ቡድኖች ከፍተኛ ግምት ሰጥተው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በ24 ነጥብ በ2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወላይታ ዲቻን በሜዳው በማሸነፍ የፕሪሚየር ሊጉን የመጀመሪያ ዙር የበላይነት ከሲዳማ ቡና ተረክቦ ለመጨረስ እንደሚጫወት የሚጠበቅ ሲሆን በአንፃሩ ወላይታ ዲቻ በዘንድሮ የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ጠንካራነቱን  አጠናክሮ ለመቀጠልና ነጥቡን ወደ 24ት ከፍ በማድረግ ከፕሪሚየር ሊጉ የዋንጫ ተፎካካሪ ቡድኖች ላለመራቅ ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል። 

አዲስ አበባ ላይ በአበበ በቂላ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ከኤሌትሪክ የሚያደርጉት ጨዋታ ሌላው በጉጉት የሚጠበቅ ጨዋታ ነው። ኢትዮጵያ ቡና በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ በ3ኛነት የያዘውን ስፍራ ሳይለቅ የመጀመሪያውን ዙር  ለመጨረስ ለጨዋታው ከፍተኛ ግምት በመስጠት ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። ኤሌትሪኮች በበኩላቸው  በተከታታይ አራት ጨዋታዎችን ከተሸነፉ በኋላ ባለፈው ሳምንት ከወላይታ ዲቻ ጋር ባደረጉት ጨዋታ አቻ በመለያየት ማገገም እያሳዩ ነው  በመሆኑም ነገ 10 ሰዓት ላይ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ ትኩረት ሰጥተው ለማሸነፍ ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል  ጨዋታውን  ማሸነፍ ከቻሉ ደረጃቸውን አሁን ካለበት ከ11ኛ ወደ 7ኛ ወይም 8ኛ ማሳደግ ይችላሉ።

ሌላው ሐዋሳ ላይ  ሀዋሳ ከነማና በደደቢት መካከል የሚደረገው ቀሪ ማስተካከያ ጨዋታ ነው።  በዘንድሮ የፕሪሚየር ሊግ ውድድር እንደ አጀማመራቸው መቀጠል ያልቻሉት ደደቢቶች ጨዋታውን አሸንፈው ወደ ዋንጫ ተፎካካሪነት ቦታቸው ለመመለስ ይጥራሉ ተብሎ ይተበቃል። ሐዋሳዎች በበኩላቸው  አሁን ከሚገኙበት 13ኛ ደረጃ የወራጅ ቀጠና ለመውጣት የሚያስችላቸውን ነጥብ ለመሰብሰብ ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። 

የነገው ጨዋታን ሳይጨምር ፕሪሚየር ሊጉን ሲዳማ ቡና በ27ት ነጥብ ሲመራ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ24 እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና በ21 ነጥብ ይከተላሉ። የኮከብ ጎል አግቢነቱን ፉክክር የኢትዮጵያ ቡናው ቢኒያም አሰፋ በ11 ጎል ሲመራ  የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኑሚ በ8 ጎል ይከተላል። 
 
ዜና ዘገባ፦ ፈለቀ ደምሴ 

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!