ፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ የ13 ዙር ጉዞ በሲዳማ ቡና መሪነት ትላንት ተጠናቀቀ
ጥር 25, 2007

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ  ትናንት በአዲስ አበባው አበበ በቂላ ስታዲየምና በደቡበ ክልል ሁለት ከተሞች ባደረገው ጨዋታ የ2007 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር መርሃ ግብሩን ዘግቷል። አዲስ አበባ ላይ በአጥናፉ ዓለሙ የሚሰለጥነው ኤሌክትሪክና በጥላሁን መንገሻ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ቡና ተጫውተው ኤሌክትሪክ አንድ ለባዶ ማሸነፍ ችሏል። ሁለቱ ክለቦች ትናንት ከመገናኘታቸው በፊት የአሸናፊነት ግምቱ ሚዛን ደፍቶ የነበረው ወደ ኢትዮጵያ ቡና በኩል ነበር።
Coffee supporters

 ዳሩ ግን ጨዋታን በማንበብ የተካኑ ናቸው ተብለው በሚነገርላቸው አጥናፉ ዓለሙ የሚሰለጥነው ኤሌክትሪክ ግምቶችን ፉርሽ አድርጎ የአሸናፊነቱን አክሊል መድፋት ችሏል። በትላንቱ በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በሁቱም በኩል የተመጣጠነ ጨዋታ የታየበት ሲሆን በርካታ የጎል ሙከራዎችም ተደርገው ነበር። በ21ኛው ደቂቃ መብራት ሀይሎች ከርቀት ያደረጉትን አስደናቂ የግብ ሙከራ የቡናው በረኛ ተወርውሮ በአናት ካወጣበት   ደቂቃ ጀምሮ  በሁለቱም ቡድኖቸ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ሙከራዎች ተደርገዋል። የኤሌክትሪኩ ፒተር በ30 እንዲሁም የቡናው አስቻለው ግርማ በ31ኛውና በ39ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች የበረኞችን ብቃት የፈተኑ ነበሩ። ከረፍት መልስ ቡናዎች የመጀሪያዎቹን ደቂቃዎች ጨዋታውን አፍጥነው ለመጫወት ቢሞክሩም የመጀመሪያውን የጎል ሙከራ ለማድር የቻሉት ግን በ49ኛው ደቂቃ  በትላንትናው እለት ጠንካራ አቋም ይዘው የገቡት ኤሌክትሪኮች በፒተር አማካኝነት ነበር። ኢትዮጵያ ቡናዎች በ53ኛውና በ59ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ አጋጣሚዎችን አግኝተው ሳይጠቀሙባቸው ቀሩ። በተመሳሳይ ኤልፓዎች በ57ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ ኳስ ወደፊት አሳልፈው ኳሷን ከጎል ማገናኘት አቅቷቸው ሳይጠቀሙባት ቀርተዋል። ከቡናዎች የማጥቃቱን የበላይነት የተረከቡት ኤሌትሪኮች በ62ኛው ደቂቃ ላይ በፒተር አማካኝነት የጨዋታውን ብቸኛ ጎል አስቆጠሩ። ቡናዎች ጎል ከገባባቸው በኃሏ አቻ ለመሆን በ59ኛው እንዲሁም በ76ኛው ደቂቃዎች ላይ በቢኒያም አሰፋ አማካኝነት ካደሩት የጐል ሙከራዎች በስተቀር  ብዙም ጥረት ባለማድረጋቸው  ጥሩ እንቅስቃሴ ሳያሳዩ ተሸንፈው ሊወጡ ችለዋል።  የትላንቱ ውጤት  ደጋፊዎቻቸውን ክፉኛ ያበሳጨ ሆኗል።
Peter Celebrating His Goal

የኤሌክትሪክን የማሸነፊያ ጎል ያስገኘውን ፒተርን በተመለከተ  ከሶስት ወራት በፊት የኢትዮፉትቦልዶትኮም ሪፖርተር “ከናይጄሪያ የተገዛው ፒተር የሚባለው አጥቂ የተቃራኒ ቡድኖችን የግብ መስመር ለይቶ አያውቅም ለምን በአገር ውስጥ አጥቂዎች ቡድን ዎትን አያጠናክሩም?” ብሎ ለጠየቃቸው ጥያቄ አቶ አጥናፉ ሲመልሱ ”ተጫዋቹ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ ገና የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ስለሆነ ስለ ተጫዋቹ ሙሉ መረጃ ስለማታውቅ እንጅ አጥቂውማ የተዋጣለት ተጫዋች ነው። ይህን ደግሞ ወደ ፊት የምታየው ይሆናል” ብለው ነበር።
Electric Celebtatin their win

 አቶ አጥናፉ ሽንጣቸውን ገትረው የተከራከሩለት ናይጄሪያዊው አጥቂ ፒተር በትናንቱ ጨዋታ ቡናማዎቹን አንገት ያስደፋች ጎል በማስቆጠር ለኤሌክትሪክ ክለብ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን አሳይቷል። ድሉን ተከትሎ ኤሌክትሪክ ከነበረበት 14 ነጥብ ላይ ሶስት ነጥቦችን በማከል የነጥቡን ብዛት 17 በማድረስ ከኢትዮጵያ ቡና በአራት ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ በቅርብ ርቀት እንዲከተል አድርጎታል።

ሁለቱ የደቡብ ክልል ከተሞች ሃዋሳ እና ቦዲቲ ሁለት የአዲስ አበባ ክለቦችን ጋብዘው በሜዳቸው አንድ ጎል እንኳ ማስቆጠር ተስኗቸው ታይተዋል። በቅርቡ አቶ ታረቀኝ አሰፋን አሰናብቶ አዲሴ ካሳን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ የቀጠረው ሃዋሳ ከነማ በትናንቱ ጨዋታም ከነበረበት የሽንፈት ሃንጎቨር መውጣት ተስኖት በሜዳውና በደጋፊው ፊት በደደቢት ሁለት ለባዶ ተሸንፏል። ተደጋጋሚ ሽንፈቶችን በማስተናገዱ ጫና ውስጥ ገብቶ የነበረው የኢንስትራክተር ዮሃንስ ሳህሌ ቡድን ደደቢት ትናንት ሃዋሳ ድረስ ተጉዞ ሁለት ንጹህ ጎሎችን እና ሶስት ወሳኝ ነጥቦችን ቋጥሮ መመለሱ በመጠኑም ቢሆን እፎይታ ሊሰማው ችሏል። ለደደቢት ሁለቱን ወሳኝ ጎሎች ሁለቱ አምበሎች ብርሃኑ ቦጋለ ፋዲጋ እና ዳዊት ፈቃዱ ናቸው ያስቆጠሩት።

ወደ ቦዲቲ የተጓዙት ፈረሰኞቹ በበኩላቸው ከወላይታ ድቻ ጠንካራ ፍልሚያ አድርገው ሳይደፍሩም ሳይደፈሩም ባዶ ለባዶ ተለያይተው አንድ ነጥብ ይዘው ተመልሰዋል። ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ያቀናው የቅዱስ ጊዮርጊስ የነጥብ ኮሮጆ ዓላማ አድርጎ የነበረው ከቦዲቲ ሶስት ነጥብ ይዞ በመመለስ የፕሪሚየር ሊጉን የመሪነት እርካብ መቆጣጠር ነበር። ዳሩ ግን የመሳይ ተፈሪ ልጆች ለ2006 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮናዎች በቀላሉ መረባቸውን ለማስደፈር ባለመፍቀዳቸው ያለምንም ጎል አንድ ነጥብ ብቻ አስይዘው ሸኝተዋቸዋል።

ወላይታ ድቻዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ ባለመሸነፋቸው በአንድ በኩል የራሳቸውን የነጥብ ድምር 22 በማድረስ ከፈረሰኞቹ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት በሶስት ነጥብ ላይ እንዲረጋ ሲያደርጉ በሌላ በኩል ደግሞ በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ወይም ሞሪኖ ለሚሰለጥነው ሲዳማ ቡና መሪነቱን አስጠብቆ እንዲቀጥል ውለታ ሰርተውለታል።

ባለፉት 13 ሳምንታት የፕሪሚየር ሊጉ ጉዞ ሲዳማ ቡና 27 ነጥብ በመያዝ ከፍተኛ ነጥብ ሲሰበስብ ኢትዮጵ ቡና 19 ግቦችን በማስቆጠር የፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ የአጥቂ መስመር የገነባ ክለብ አድርጎታል። በአሰልጣኝ ዶ ሳንቶስ የሚሰለጥነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በ13 ጨዋታ መረቡን አምስት ጊዜ ብቻ በማስደፈር የተከላካይና የግብ ጠባቂውን ጥንካሬ ሲያስመሰክር ወልድያ ከነማ ደግሞ ለተጋጣሚዎቹ በሙሉ በሩን ከፍቶ በመጠበቅ እንግዳ ተቀባይነቱን ያሳየ ክለብ ሆኗል።

ፕሪሚየር ሊጉን ሲዳማ ቡና በ27 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ፈረሰኞቹ 25 ነጥቦችን ይዘው ሲከተሉ ወላይታ ድቻ በ22 እና ኢትዮጵያ ቡና በ21 ነጥቦች ተከታዮቹን ደረጃ ይዘዋል። የወራጅ ቀጠናውን ወልድያ ከነማ ያለተቀናቃኝ ተቆጣጥሮታል። ሃዋሳ ከነማ የግርጌውን ቦoታ ከወላይታ ድቻ ለመረከብ ጥረት እያደረገ የመስላል አስር ነጥቦችን ብቻ በመያዝ 13 ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ከፍተኛ ግብ አግቢነቱን የኢትዮጵያ ቡናው ቢኒያም አሰፋ 11 ጎሎችን በማስቆጠር ይመራል። ኢትዮጵያ ቡና በፕሪሚየር ሊጉ 13 ጨዋታዎችን አካሂዶ 19 ጎሎችን ብቻ ያስቆጠረ ቢሆንም አጥቂው ቢኒያም አሰፋ ግን ብቻውን 11 ጎሎችን በማስቆጠር የክለቡ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን አሳይቷል።

የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተከላካይ ሳላዲን ባርጌቾ ደደቢት ላይ በፎርቢች ያስቆጠራት ጎል፣ የኢትዮጵያ ቡናው ቢኒያም አሰፋ ደደቢት ላይ እና አዳማ ከነማ ላይ ያስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አብዱልከሪም መሃመድ ወይም ምርምር አዳማ ከነማ ላይ ያስቆጠራት ግብ እንዲሁም የአዳማ ከነማው ታከለ ዓለማየሁ ደደቢት ላይ ያገባት ጎል በፕሪሚየር ሊጉ የግማሽ ዓመት ጉዞ ከተቆጠሩ ማራኪ ጎሎች ቀዳሚዎቹ ናቸው። ወላይታ ድቻ፣ ሲዳማ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንጻራዊነት ወጥ አቋም በማሳየት ረጅሙን የውድድር ዓመት ጉዞ ያጋመሱ ሲሆን ደደቢት፣ ሐዋሳ ከነማና መከላከያ ደግሞ በመጠኑም ቢሆን ከተጠበቁት በታች ሆነው የተገኙ ክለቦች ሆነዋል።

ዜና ዘገባ፦ይርጋ አበበ

ኢትዮ ፉትቦል


ethioootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!