የዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ውድድር፦ የተተኪዎች መፍለቂያ ምቹ መድረ -ክፍል 2-
ጥር 29, 2007

ክፍል ሁለት

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘውን የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ውድድር በቦታው ተገኝተን ያነጋገርናቸውን አሰልጣኞችና ተጫዋቾች የመጀመሪያ ክፍል ማቅረባችን ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ ካለፈው የቀጠለውን ክፍል ይዘን ቀርበናል።

ስምንተኛው የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ውድድር ቅዳሜ ከሰዓት ሲጀመር በመክፈቻው የተገናኙት አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲና አርሲ ዩኒቨርስቲ ናቸው። በዚያ ጨዋታ ከተሳተፉ ተጫዋቾች መካከል የአስተናጋጁን አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የእግር ኳስ ቡድን በአምበልነት እየመራ የገባው አብዱልማሊክ መሃመድና አማካይ ተከላካዩ አቤል ፈንታው በደጋፊዎች አድናቆት ከተቸራቸው ተጫዋቾች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው።
 
አብዱልማሊክ
44 ቁጥር ማሊያ ለብሶና ጸጉሩን በተለያዩ ቀለሞች አዥጎርጉሮ በተከላካይ መስመር ተሰልፎ የሚጫወተው  ከተጋጣሚ ቡድን አጥቂዎች ጋር ፊት ለፊት ሲገናኝ ፍርሃት አይታይበትም። ቡድኑ አደጋ ላይ ሲወድቅ የሚያደርገው የማበረታታት ስራም በእጅጉ ልምድ ያለው ተጫዋች ያስመስለዋል። ቡድኑ ተጋጣሚውን አራት ለአንድ ባሸነፈበት ጨዋታም ለቡድን አጋሩ አመቻችቶ ያቀበለው ኳስ ወደ ጎል ተቀይሯል። ይህ ሁሉ ችሎታው ተጫዋቹን ተቀብሎ እምነት ሰጥቶ የሚያሰልፈው ታላቅ ክለብ ቢያገኝ አደራ መቀበል የሚችል ወጣት መሆኑን አስመስክሯል።

በአማካይ ተከላካይ ቦታ የሚሰለፈው አቤል ፈንታው ደግሞ የተጋጣሚ ቡድን አጥቂዎችን ጉዞ በመግታት የራሱን ቡድን ከአደጋ የሚከላከል ታታሪ ተጫዋች ነው። በተደጋጋሚ ጊዜ ከእይታ ውጭ ሆኖ ስራውን በትጋት የሚከውነው አቤል ከዚህ በፊት በትውልድ መንደሩ ወልድያ ከተማ ከፕሮጄክት ጀምሮ እስከ ወልድያ ከነማ እግር ኳስ “ቢ” ቡድን የደረሰ የተጫዋችነት ዘመን አለው። ሁለቱ ተጫዋቾች ለዝግጅት ክፍላችን ስለቡድናቸው አጠር ያለ አስተያየት ሰጥተዋል። የተጫዋቾቹን ሙሉ ቃል እነሆ!!

በማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም የትምህርት መስክ እየተማረ ያለው አብዱልማሊክ አስተያየቱን መስጠት ሲጀምር ”ዘንድሮ ትምህርቴን አጠናቃለሁ እንደፈጣሪ ፈቃድ እቅዴ ከትምህርት በኋላ በእግር ኳስ እቀጥላለሁ ብዬ ነው የማስበው። ከቤተሰብም ቢሆን ከፍተኛ ድጋፍ ስለሚደረግልኝ በእግር ኳሱ መግፋት እፈልጋለሁ” ይላል። የቡድን አጋሩ አቤል በበኩሉ በኢንተርናሽናል ትሬድ ማኔጅመንት ተማሪ ሲሆን ወደፊት ከእግር ኳስ ጋር መለያየት እንደማይፈልግ ሲናገር በልበ ሙሉነት ነው። “ከዚህ በፊትም በወልድያ ከነማ ሁለተኛው ቡድን ተጫዋች ሆኜ ነው ያሳለፍኩት። የትምህርት እድሉን ሳገኝ ቅድሚያ ለትምህርቱ የሰጠሁት የቤተሰብ ፍላጎት በትምህርቱ እንድገፋበት በመሆኑ ነው የተማርኩት። በልጅነቴ በፍቅር ከወደኩባት እግር ኳስ ጋር እስከመጨረሻው እቀጥላለሁ። በዚህ ዓመት ተመራቂ በመሆናችን በሜዳችን የተዘጋጀውን ውድድር በአሸናፊነት በማጠናቀቅ ዩኒቨርስቲያችንን በድርብ ድል መሰናበት እንፈልጋለን” ሲል ይናገራል። ሁለቱ ተጫዋቾች የሰጡንን አስተያየት ወደፊት በስፋት የምንዳስሰው ይሆናል።

ተወልዶ ያደገው በኦሮሚያ ክልል ዝዋይ ከተማ ነው። የከፍተኛ ትምህርቱን የሚማረው ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ታሪካዊቷ አክሱም ከተማ ውስጥ በሚገኘው አክሱም ዩኒቨርስቲ ነው አብርሃም ግርማ። የሚማርበትን ዩኒቨርስቲ ወክሎ አዳማ የተገኘው አብርሃም ግርማ ቡድኑ ትናንት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ አሶሳ ዩኒቨርስቲን ገጥሞ አንድ ለባዶ ሲያሸንፍ የቡድኑን ብቸኛ የማሸነፊያ ጎል ያስቆጠረው ራሱ ነበር። ከመሃል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ በግሩም አጨራረስ በአሶሳ ዩኒቨርስቲ መረብ ላይ ያሳረፈው አብርሃም በጨዋታው ማራኪ እንቅስቃሴ ያሳየ ተጫዋች ነበር። የልጁን ችሎታ አይቶ ዝም ማለት ያልፈለገው ኢትዮፉትቦል ዶትኮም አስተያየቱን ጠይቆታል። አብርሃም “ከልጅነቴ ጀምሮ እግር ኳስን በፕሮጄክት ተጫውቼ ነው ያደኩት። ወደፊትም በትልቅ ደረጃ መጫወት እፈልጋለሁ። ለዚህም ከቤተሰብ የሚደረግልኝ ድጋፍ ህልሜን እንድኖር ማረጋገጫ ሆኖኛል። አባቴ ስልክ ሲደውልልኝ ትምህርት እንዴት ነው ብሎ አይጠይቀኝም ኳስ እንዴት ነው በደንብ እየተጫወትክ ነው? ብሎ ነው የሚጠይቀኝ። ይህ ደግሞ እኔ በርትቼ እንድጫወት አድርጎኛል።” ይላል። አብርሃም ይደግፉኛል ያላቸው ቤተሰቦቹ በትናንትናው ጨዋታም አባቱና ወንድሙ በስታዲየም ተገኝተው ሲያበረታቱ ታይተዋል።

ወጣቱ ልጅ ጨዋታው በተጀመረ በ15ኛው ደቂቃ አካባቢ ከተጋጣሚ ቡድን ተከላካይ በደረሰበት የሀይል ጨዋታ ግራ እጁ ተሰብሮ ነበር። አብርሃም ግን ጉዳቱን ችሎ ጨዋታውን ጨርሶታል። ምክንያቱን ጠይቀነው ነበር“ ጉዳቱ የደረሰብኝ እንዳልከው ገና በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ላይ ነበር። ነገር ግን የጉዳቱ መጠን ከፍተኛ ባለመሆኑና እኔም የመጫወት ፍላጎት ስላለኝ ሙሉ 90 ደቂቃውን ልጨርስ ችያለሁ።” ብሏል። አብርሃም አያይዞም ታላቅ ደረጃ እደርስበታለሁ ብሎ የሚያስበውን እግር ኳስ እውን ለማድረግ የክለቦችና የታላላቅ አሰልጣኞች ድጋፍ እንደሚያስፈልገው እምነቱ መሆኑን ተናግሯል።

ሪፖርታዥ፦ ይርጋ አበበ
ኢትዮ ፉትቦል


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!