መንታዎቹ “የአስቱ” ኮከቦች
የካቲት 01, 2007

አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርስቲ ስምንተኛውን የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ውድድር እያስተናገደ ይገኛል። በውድድሩ 34 የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች እየተሳተፉ መሆኑን ከዝግጅት አስተባባሪዎች መረጃውን አግኝተናል። አስተናጋጁ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ወይም ተማሪዎቹ ባወጡለት የቁልምጫ ስም “አስቱ” ጠንካራ ቡድን ይዞ መቅረቡ የተነገረ ሲሆን በተለይ በወንዶች እግር ኳስ በፍጻሜው የአሸናፊነቱን አክሊል እንደሚደፋ የበርካቶች ግምት ሆኗል። 
Astu Group Picture

ዩኒቨርስቲው ይህን ግምት ያገኘው አንድም አስተናጋጅ መሆኑ ሲሆን ወዲህ ደግሞ የቡድኑ ስብስብ ከግምት ስለገባ መሆኑን አስተያየታቸውን ለዝግጅት ክፍላችን የሰጡ ተመልካቾች ይናገራሉ። 

ኢትዮፉትቦል ዶትኮም የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ እግር ኳስ ቡድን ጥንካሬ ምንጭ የሆኑትንና ምናልባትም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ትኩረት ቢሰጧቸው ነገ ትልቅ ደረጃ ሊደርሱ እንደሚችሉ ተስፋ የተጣለባቸውን ሁለት ተጫዋቾችን እናስተዋውቃችኋለን። 
                                      መንትዮቹ እነማን ናቸው?

ከ22 ዓመት በፊት በሰሜን ወሎ ዞን ርዕሰ ከተማ ወልድያ ተወልዶ ያደገውና የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተስፋዬ አለባቸው ወይም ቆቦ አድናቂ የሆነው አቤል ፈንታ እና ከ21 ዓመት በፊት በአዳማ ከተማ ተወልዶ ያደገው አብዱል ማሊክ መሃመድ ዛሬ በስፋት ታሪካቸውንና የወደፊት እቅዳቸውን ሊነግሩን ቀጠሮ ይዘዋል። እነዚህ በትውልድ ቦታና ዘመን የተለያዩ መንትዮች ምን አመሳሰላቸው? የሚል ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል። መልሱ ወዲህ ነው የሁለቱ መመሳሰል በሙያና በችሎታ እንጅ በደም የሚያመሳስላቸውም ሆነ የሚያጣምራቸው አንዳችም ነጥብ የለም። 
The twins
ሁለቱም ተጫዋቾች በዩኒቨርስቲው የሚኖራቸው ቆይታ የሚጠናቀቀው በዚህ ዓመት ነው። ያለፉትን ሁለት ዓመታት የዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ውድድር ላይ ዩኒቨርስቲያቸውን ወክለው የሚጠበቅባቸውን ግዴታ በብቃት ተወጥተዋል። ሁለቱም የሚጫወቱት በቡድናቸው የመሃል ሜዳ አጋማሽ የኋለኛው ክፍል ነው። መንትያዎቹ የዩኒቨርስቲው ፈርጦች። የዩኒቨርስቲውን እግር ኳስ በአምበልነት የሚመራው አብዱልማሊክ መሃመድ የቡድኑን የተከላካይ መስመር በብቃት የሚወጣ ታጋይ ተከላካይ ሲሆን ወሎየው አቤል ፈንታው ደግሞ ከተከላካዮች ፊት ቆሞ ለተከላካይ መስመሩ ሽፋን የሚሰጥ የአደጋ ጊዜ ቀድሞ ደራሽ ወታደር ነው። 
ብዙዎች የአቤልን ቦታ በተለምዶ የክሉድ ማኬሌሌ ቦታ እያሉ የሚጠሩት የአማካይ ተከላካይ መስመር ሲሆን አቤል ደግሞ በጨዋታ እንቅስቃሴው የቅዱስ ጊዮርጊሱን ተስፋዬ አለባቸው ወይም ቆቦን እያደነቀ ማደጉን ይናገራል። ከፍተኛ ሃለፊነትን በሚጠይቀው የአማካይ ተከላካይ ቦታ ላይ ላለፉት ሁለት ዓመታትና በዚህ ዓመት በድምሩ ለሶስት ዓመታት ዩኒቨርስቲውን ወክሎ እንደተጫወተ ይናገራል። እየተማሩ መጫወት አስተሳሰብን ስለሚያሰፋ በኳስ አገፋፍም ሆነ በፍልስፍና የተሻልክ ያደርግሃል የሚለው አቤል “እየተማሩ መጫወት ሌላው አድቫንቴጅ እግር ኳስ እንደሚታወቀው አካላዊ ንክኪ የሚበዛበት ስፖርት እንደመሆኑ በጨዋታ መሃል ጉዳት ቢፈጠር የሚደርሰውን ቀውስ መቋቋም እንድትችል ያደርግሃል። የተማርክ ከሆንክ ከእግር ኳስ በጉዳት ብትለይም ኑሮህን በሌላ መስክ የመግፋት እድሉን ታገኛለህ።” ብሎ ያምናል። 

                 መንትዮቹ ስለ ክለቦች ምልመላ ችግር ምን ይላሉ?

Abdul Malik
አብዱልማሊክ ይጀምራል። “በአገራችን የተለመደ አንድ አነጋገር አለ “የፈለገውን ያህል ኳስ መጫወት ብትችልም ዘመድ ከሌለህ ታዕምረኛ እግርህን እንደያዝክ ከቤትህ ትቀመጣለህ” የሚል። አባባሉን እጋራዋለሁ የአገራችን ክለቦች ችግር መሆኑን በተደጋጋሚ ጊዜ አይቸዋለሁ” ይላል።  “ነገር ግን መልማዮች እኛን ብቻ ሳይሆን ከቀበሌና ከሰፈር ውድድሮች ላይ እንኳ ቢሄዱ ቡድናቸውን ማጠናከር የሚችሉ ተጫዋቾችን እንደሚያገኙ እርግጠኛ ነኝ። እኛም አሁን የምንጫወተው የክለብ መልማዮች መጥተው እየተመለከቱ ነው ብለን አስበን አይደለም።” ሲል አስተያየቱን ይሰጣል። 

አቤል በበኩሉ “ተጫዋቾችን በዘመድ ይመርጣሉ በሚለው አልስማማም” ብሎ አስተያየቱን መስጠት ይጀምራል። “ነገር ግን በዩኒቨርስቲዎች ውድድር ላይ የመልማዮች ችግር የሚመነጨው ከአመለካከት ነው። ከአመለካከት ስልህ ውድድሩ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ስለሆነ ተማሪዎች እግር ኳስን ሙያዬ ብለው ከልባቸው ስለማይዙት ጥሩ ማች ፊትነስ አላቸው ብለው አያምኑም። ተጫዋቹን ብንፈልገው እንኳ ትምህርቱን አቋርጦ ክለባችንን አይቀላቀልም ብለውም ያስባሉ። አስተሳሳባቸው ስህተት መሆኑን የምታየው ግን አሁን ለመከላከያ እየተጫወተ ያለው ሙሉቀን  ተመልከት እሱ የተገኘው ከዩኒቨርስቲ ጨዋታ ነው። ብዙዎቻችን የምናውቃቸው ፍጹም ገብረማሪያምና እንዳለ ከበደ አሁን ከደረሱበት ደረጃ የደረሱት ሁለቱንም ዘርፎች ማለትም ኳሱንና ትምህርቱን እኩል ትኩረት ሰጥተው ስለሰሩ ነው። ክለቦችም አስተሳሰባቸውን ቀይረው ውድድሩን ቢመለከቱ መልካም ነው። ምክንያቱም የተማረ ኳስ ተጫዋች ለዲሲፕሊን ተገዥ ከመሆኑም በላይ የሚነገረውን ለመተግበር የተዘጋጀ ነው” ሲል ይናገራል። 

                                     የመንትዮቹ መልዕክት 

አንድ ሰው ካሰበው ደረጃ ለመድረስ ብዙ መሰናክሎችን ማለፍ አለበት የሚለው አብዱልማሊክ አንድ ተጫዋች ካሰበው ደረጃ ለመድረስ ራሱን መጠበቅ አለበት። ለምሳሌ እዚህ አዳማ ከነማ የሚጫወት አንድ ተጫዋች አለ ታከለ ዓለማየሁ የሚባል። ይህ ልጅ ከዚህ ደረጃ ለመድረስ ራሱን ከማንኛውም አሰናካይ ድርጊት ቆጥቦ ነው። በምንም አይነት መንገድ ራሱን ለአታላይ ነገሮች አሳልፎ የእግር ኳስ ጉዞውን እንዲሰናከልበት እድል አይፈጥርም። ልክ እንደ ታከለ ሁሉ ሌሎች ወጣት ተጫዋቾችም ራሳቸውን ከአታላይ ነገሮች ጠብቀው ብቃታቸውን እየጨመሩ መጓዝ አለባቸው። እንደ አላህ ፈቃድ የእኔም እቅድ ይህ ነው።

ሌላው ለወጣት ተጫዋቾች መናገር የምፈልገው አሰልጣኞቻቸውን እንዲያከብሩ ነው። ይህ ማለት አሰልጣኝ በእድሜም ሆነ በችሎታ ከተጫዋቹ ያነሰ ሊሆን ይችላል ነገር ግን ተጫዋቹ አሰልጣኙን አላከበረም ማለት ኳሱ ደግሞ በተራው ተጫዋቹን ይንቀዋል።” ይላል። 

ለስኬት የሚያበቃው ትልቁ መንገድ ቁርጠኝነት መሆኑን የሚናገረው ደግሞ የተከላካይ አማካዩ አቤል ፈንታው ነው። ማንም ሰው እሆናለሁ፤ መድረስ እፈልጋለሁ፤ ብሎ ካሰበው ደረጃ ለመድረስ የሚያግደው ነገር የለም ቁርጠኝነቱ ካለው። ለምሳሌ እኔ ወልድያ በነበርኩበት ጊዜ ኦቨር ቤንች ሆነው የሚቀመጡ ልጆች ነበሩ። እነዚያ ልጆች ኦቨር ቤንች የሆኑበትን ምክንያት ሲጠይቁ ችግራቸው ይነገራቸዋል። ያኔ ከመደበኛው ልምምድ በኋላ ለራሳቸው ልምምድ ይሰሩ ነበር። ልጆቹ አላማቸው እግር ኳስ ተጫዋች መሆን ስለሆነ አሁን ህልማቸውን እውን ማድረግ ችለዋል። ስለዚህ ወጣቶች የህልማቸውን ለመኖር ቁርጠኝነትና የዓላማ ጽናት ሊኖራቸው ይገባል” ሲል መልክዕቱን ይገልጻል። 

   የመንትዮቹ ደስታ 
“እንደነገርኩህ ከስድስት ወር በኋላ ከዩኒቨርስቲ እመረቃለሁ። እርግጠኛ ሆኜ የምነግርህ በመመረቄ ቤተሰቦቼ ደስተኛ አይሆኑም። የቤተሰቦቼ ትልቁ ደስታ እግር ኳስ ተጫዋች ሆኜ ሲያዩኝ ነው። በመክፈቻው ጨዋታ ድንገት ስሜ ሲጠራ በጣም ድንግጥ ብዬ ስዞር ያልጠበኩትና ያላሰብኩትን ሰው ነበር ያየሁት። አባቴና ወንድሜ ጨዋታውን እየተመለከቱ ነበር። ባይገርምህ አባቴ የእኔን ጨዋታ እየተመለከተ በትልቅ ደረጃ ጎል ያገባሁትም ያኔ በመሆኑ ተደስቶ ነበር ከሜዳ የወጣው። የእኔ ትልቁ ደስታም የቤተሰቦችን ምኞት እውን ማድረግ ነው በትልቅ ደረጃና በብሔራዊ ቡድን ደረጃ በመጫወት።” ሲል የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርስቲ አምበል ይናገራል።  

አቤል ፈንታው ደግሞ “በህይወቴ አልኮል ጠጥቼ አላውቅም በፕሮጄክት ስጫወት ደግሞ አንድም ቀን ቢጫ ካርድ አይቼ አላውቅም። አሰልጣኞች የሚያዙኝን ለመፈጸም ወደኋላ አልልም። የተቻለኝን ጥረት ሁሉ አድርጌ ከማስበው የእግር ኳስ ደረጃ መድረስ እፈልጋለሁ። ለዚህ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት የኳሱ ኢንዱስትሪ እየሰፋ መጥቷል። እኔም ትምህርቴን ከተመረኩ በኋላ በቀጥታ ወደዛው እንደምገባ ነው የማስበው። የማስበውን ካሳካሁ ደስታዬ ወደር የለውም” ሲል ሃሳቡን ያጠቃልላል። 

ኢትዮፉትቦል ዶትኮም ወጣቶቹ እቅዳቸው እንዲሳካላቸው እየተመኘ በቀጣይ ጊዜያት ደግሞ የሌሎች ተስፈኞችን ተመሳሳይ ቃለ ምልልስ እንደምናቀርብ ቃል እየገባን ለዛሬው በዚሁ እንሰናበታለን። 

ሪፖርታዥ፦ይርጋ አበበ 
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
gedamu [1107 days ago.]
 Your report coverage on the young players is interesting, It builds the young boys Moral.

usman mohammed [1099 days ago.]
 oww malik betam des yemil tesfa new. ene memkreh megnothen esktasaka becha sayhon kasakahem behuala wed miasnakluh negroch endatgeba new. genzeb yebzu esportgnochen mind silwex aychalhuna pls. betrfe hasabeh ke ALLAH ga endmisakalh(ye guadegnahem) bale mulu tesfa negn

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!