1992ቱን በ2015
የካቲት 02, 2007

ጊዜው እ.ኤ.አ 1992 ነበር 18ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ የሚካሄደው። በጊዜው ሁለቱ የምዕራብ አፍሪካ ሃያላን የእግር ኳስ አገሮች ጥቋቁር ክዋክብትና ዝሆኖቹ የሚፋለሙበት ጨዋታ። ሁለቱ ቡድኖች ለ120 ደቂቃ ተፋልመው መሳ ለመሳ በመለያየታቸው አሸናፊው የተለየው በመለያ ፍጹም ቅጣት ምት ነበር። የአፍሪካ ዋንጫን አንስታ የማታውቀው አይቮሪኮስት 11 የመለያ ምቶችን መትታ ሁሉንም አስቆጥራ ከጋና በአንድ ጎል በልጣ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን አነሳች።
Côte d'Ivoire African Champion 2015

ከ23 ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትዕግስት በኋላ ደግሞ ሁለቱ ምዕራባውያን ሃያላን ቡድኖች በታናሿ አገር ኢኳቶሪያል ጊኒ ለተመሳሳይ ግዳጅ ተገናኙ በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ። በትናንት ምሽቱ ጨዋታም ሁለቱ ቡድኖች 120 ደቂቃ ቢፋለሙም አንዳቸውም ጎል ማስቆጠር ባለመቻላቸው አሸናፊውን ለመለየት ወደ መለያ ፍጹም ቅጣት ምት አመሩ። ታሪክም ራሱን ደገመ ሁለቱም ቡድኖች 22 መለያ ምቶችን ሲመቱ ጋናውያን ስምንቱን አይቮሪያውያን ደግሞ ዘጠኙን መረብ ላይ በማሳረፍ በታሪካቸው ለሁለተኛ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጠጫን ማንሳት ቻሉ።
 Côte d'Ivoire  Africn Cmapion 2015

በእስራኤላዊው አቭራም ግራንት የሚመሩት ጥቋቁር ክዋክብቶቹ በአንድሬ አየውና በአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ በተመረጠው አትሱ አማካኝነት የአይቮሪያኑን የግብ ክልል በተደጋጋሚ ጊዜ ቢሞክሩበትም የግቡ ቋሚ ብረት መልሶባቸዋል። አምበሉ አሳሞኣ ጂያን ደግሞ ለጎል የቀረበ ኳስ ቢያገኝም ማስቆጠር ሳይችል ቀርቷል። በዝሆኖቹ በኩል ደግሞ የሮማው አጥቂ ጀርቪኖ በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ጎል ክልል ቢቀርብም አጨራረሱን ባለማሳመሩ እና አዲሱ የማንቸስተር ሲቲ አጥቂ ዌልፍሬድ ቦኒ የቀድሞ ብቃቱን ይዞ አለመገኘቱ ጨዋታው ባዶ ለባዶ እንዲጠናቀቅ ምክንያት ሆነዋል።

ፈረንሳያዊው ሃርቭ ሬናፕ ከሶስት ዓመት በፊት የዛምቢያን ብሔራዊ ቡድንን ቺፖሎ ፖሎን እያሰለጠኑ ከአይቮሪኮስት ጋር ለፍጻሜ መድረሳቸው ይታወሳል። በጊዜው የአይቮሪያኑ ተጫዋቾች ጄርቪኖና ኮሎ ቱሬ ፍጹም ቅጣት ምት በመሳታቸው ዛምቢያ አሸናፊ መሆን ችላ ነበር። ዛሬ ደግሞ ታሪክ ተቀይሮ አይቮሪኮስት በመለያ ፍጹም ቅጣት ምት ጋናን አሸንፋ የዋንጫውን አንገት ስትጨብጥ ታሪካዊው ሬናፕ የቡድኑ ፊታውራሪ በመሆን ታሪክ ሰርተዋል። በሶስት ዓመት ውስጥም ከሁለት አገሮች ጋር በመሆን ሁለት የአፍሪካ ዋንጫን ማንሳት ችለዋል።

የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ጋቦናዊው ዳኛ ባካሪ ፓፓ ጋሳማ በዋና ዳኝነት ሲመሩት 38 ሺህ ኢኳቶሪያል ጊኒያውያን ደግሞ ጨዋታውን በስታዲየም ተገኝተው ተከታትውታል። የፊፋው ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ሴፍ ብላተርንና የካፉን ፕሬዚዳንት ይሳ ሃያቱን ጨምሮ በርካታ የፊፋና የካፍ የሥራ ሀላፊዎችን በስታዲየም ታድመው ያለ ጎል የተጠናቀቀውን ጨዋታ ተከታትለውታል።


ይርጋ አበበ
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!