አዳማ ከተማ ሁለተኛ ተወካይዋን ልታገኝ ነው
የካቲት 03, 2007

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሚካፈሉ 14 ክለቦች መካከል አዲስ አበባ ስድስቱን በመያዝ የክለብ ሃብታም ከተማ ሆናለች። ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ ከተሞች በፕሪሚየር ሊጉ የሚካፈል ክለብ ያለቸው ቢበዛ አንድ ብቻ ነው። ይህ በመሆኑ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ክለቦች በተለያዩ ምክንያቶች በውድድሩ ተጠቃሚ ሲሆኑ ይታያል። ይህን የተረዱት የክልል ከተሞችም በከተማቸው ቢያንስ ከአንድ በላይ ክለቦችን ለመያዝ የእግር ኳሳቸውን ደረጃ ለማሳደግ ሲንቀሳቀሱ ይታያል። ከእነዚህ ከተሞች መካከል የስምጥ ሸለቆዋ ውብ ከተማ አዳማ አንዷ ናት። አዳማ ከተማ ከዚህ በፊት ከተማዋን ለረጅም ዓመታት በጥንካሬ ሲወክል የቆየው አዳማ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ባለቤት ስትሆን ከቀጣዮቹ ዓመታት ጀምሮ ደግሞ በከተማዋ ስም የሚጠራ አዲስ ክለብ መቃቋሙን ለዝግጅት ክፍላችን መረጃው ደረሰን።

 አዳማ ከተማን የሚወክለው ክለብ ማነው?

“ማውንቴን አዳማ እግር ኳስ ክለብ” ሁለተኛው የአዳማ ከተማ ክለብ ሆኖ በምሥራቅ ሸዋ ስፖርት ኮሚሽንና በአዳማ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የተመዘገበ አዲሱ ክለብ ነው። ስለ ስያሜው መነሻ ነጥብ እንዲነግሩን የክለቡን አመራሮች አነጋግረናቸዋል። አዳማ ከተማ ዙሪያዋን የተከበበችው በዘጠኝ ትላልቅ ተራራዎች ነው። ከተማዋን የከበቡትን ተራራዎች በመውሰድ የክለቡ ስም ማውንቴን አዳማ የእግር ኳስ ክለብ ተብሎ መሰየሙን የክለቡ ፕሬዙዳንት አቶ ቶላ ፈይሳ ይናገራሉ።

ክለቡ መቼ ተመሰረተ? ሲመሰረት ይዞ የተነሳው ራዕይስ ምንድ ነው? ለሚለው ጥያቄ አቶ ቶላ “ክለቡ ከተመሰረተ ከስምንት ወር በላይ ሆኖታል። ራዕዩ ከተማዋን በዓለም አቀፍ መድረክ ሊወክል የሚችል ክለብ ማድረግ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። የክለቡ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ጥላሁን በበኩላቸው “አገራችን ውስጥ ተጫዋች አልጠፋም ነገር ግን በታዳጊዎችና በወጣቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ባለመኖሩ ብቻ ነው እግር ኳሳችን ሊያድግ ያልቻለው። እኛም ክለቡን ስናቋቁም አላማ አድርገን የተነሳነው የራሳችንን ክለብ ከማጠናከር በተጨማሪ ለአገሪቱ የሚጠቅሙ ተጫዋቾችን የሚያፈራ አካዳሚ መክፈት ነው” ሲሉ ይናገራሉ።

የክለቡ የገቢ ምንጭ ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ለሀላፊዎቹ አቅርበንላቸው ነበር። ከሀላፊዎቹ እንደተገለጸልን የክለቡ የገቢ ምንጭ የአዳማ ከተማ ነዋሪ የሚያደርግለት የገንዘብ መዋጮና ክለቡን ለመደገፍ ቀና ፍላጎት ባላቸው ባለሃብቶች በሚያገኘው ድጋፍ መሆኑን ነግረውናል። የክለቡ የገቢ ምንጭ ህዝቡ እንዲሆን የተወሰነበትን ምክንያት የሚያብራሩት ሃላፊዎቹ “እንደሚታወቀው የአገራችን ክለቦች የገንዘባቸው ምንጭ የመንግስት በጀት ነው። ይህ በመሆኑ ደግሞ በእግር ኳሱ እድገት ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩ ይታወቃል። እኛም ይህንን በማየት ነው ህዝቡ የራሴ ብሎ የሚንከባከበውና በቁርጠኝነት የሚደግፈው ክለብ ማቋቋም የወሰንነው። ክለቡ በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንኳ ከአምስት ሺህ በላይ ህዝብ ክለቡን በገንዘብ ለመደገፍ ተመዝግቦ ክፍያ እየፈጸመ ይገኛል” ሲሉ ተናግረዋል። ሀላፊዎቹ አያይዘውም የከተማዋን ነዋሪዎችና የከተማ አስተዳደር ሀላፊዎች ክለቡን ለማቋቋም በተደረገው ጥረት ያሳዩትን ትብብር አመስግነዋል።

ክለቡ በአሁኑ ሰዓት ከዋናው ቡድን በተጨማሪ ከ13 ዓመት በታች፣ ከ15 ዓመት ታችና እድሜያቸው ከሰባት ዓመት ጀምሮ ያሉ ታዳጊዎችን ይዞ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን የክለቡ ሀላፊዎች ይናገራሉ። በህጻናት ላይ ትኩረት ማድረግ የፈለገበትን ምክንያት ጠይቀናቸው ነበር። ሀላፊዎቹ ሲመልሱም “እንደሚታወቀው ተማሪዎች በትምህርት ቤት የስፖርት ክፍለ ጊዜ አላቸው። በትምህርት ቤት ጊዜያቸው ጀምሮ ስለ እግር ኳስ ጥሩ ግንዛቤ ይዘው እንዲያድጉ በማድረግ የተሻለ የእግር ኳስ ተጫዋች እንዲሆኑ ለማድረግ ነው” ሲሉ መልሰዋል።  


ዘጋቢ፦ ይርጋ አበበ
ኢትዮ ፉትቦል
ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
አሸብር ሽፈራዉ [537 days ago.]
 LIKE THAT

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!