የአፍሪካ ዋንጫ ለዋሊያዎቹ ምን ትምህርት ሰጥቶ አለፈ?
የካቲት 04, 2007

ትንሿ አገር ኢኳቶሪያል ጊኒ የአህጉሩን ትልቁን የእግር ኳስ ውድድር በትንሽ ቀን ዝግጅት ለሌሎች የአህጉሩ አገሮች ትልቅ ትምህርት አስተምራ እንግዶቿን ሸኝታለች። የወቅቱ የምድራችን ትልቁ ወረርሽኝ ኢቦላ የአገሮችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ከማሻከሩም በላይ በእግር ኳሱ ላይ የራሱን አሻራ በማሳረፉ 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ላይካሄድ ይችላል የሚል ስጋት በብዙ የስፖርቱ ተከታታዮች እሳቤ ውስጥ ነበር። ከድሮውም ቢሆን ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ አይነት ድግስ የሚወደው ካፍ በኢቦላ ቫይረስ ደግሞ ይበልጡኑ ተፈትኖ ሊወድቅ ሲንገዳገድ ነበር ትንሿ አገር ትልቅ ውለታ የዋለችለት።

     ከርሰ ምድሯ በቅርቡ የነዳጅ ዘይት መያዙ ተረጋግጦላት በአንድ ጀምበር ከድህነት የወጣችው የ750 ሺህ ህዝብ ባለቤቷ ኢኳቶሪያል ጊኒ በሶስት ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የካፍን ትልቁን ውድድር እንድታዘጋጅም ያልታሰበ ሲሳይ እጇ ላይ ወደቀላት። እንደ ድሮው ቢሆን ኖሮ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ትግል ይጠይቅ የነበረው የአዘጋጅነት እድል ፕሬዚዳንት አባሚያንግና ልጆቻቸው የሚያስተዳድሯት አገር ኢኳቶሪያል ጊኒ በነጻ ያለምንም ፉክክር አገኘችው። በዚህ የተነሳም በአራት ስታዲየሞቿ ውድድሩን አስተናግዳ በስኬት እንግዶቿን ሸኝታለች። ኢትዮፉትቦል ዶትኮም ስለ ውድርሩ ዝግጅትና የአዘጋጅ አገር ዝግጅት በተመለከተ የሚለው ባይኖርም በውድድሩ ከተካፈሉ 16 አገሮች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምን ይማራል? የሚለውን ሃሳብ ይዳስሳል። በዚህ ሃሳብ ዙሪያ አንባቢያን እንደተለመደው ሃሳባቸውን ቢያካፍሉን የምናስተናግድ መሆኑን እንገልጻለን።

ፕሮፌሽናል ልምድ የውጤት መሰረት

የዋንጫውን እጀታ መያዝ የቻሉት የያያ ቱሬ እጆች ከስኬቱ በስተጀርባ ብሔራዊ ቡድኑ በፕሮፌሽናል ተጫዋቾች የተጠቀመ መሆኑን አሳይቷል። የአይቮሪኮስት ብሔራዊ ቡድን በግማሽ ፍጻሜ የተገናኘው ልምድ ከሌላቸው ግን ደግሞ የመጫወት ፍላጎት ካላቸው የኮንኮ ዴሞክታሪክ ሪፐብሊክ ቡድን ጋር ነበር። በወቅቱ ዝሆኖቹ ካስቆጠሯቸው ሶስት የማሸነፊያ ጎሎች መካከል አምበሉ ያያ ቱሬና አጥቂው ጀርቪንሆ ያስቆጠሯቸው ጎሎች የተጫዋቾቹን የዳበረ ልምድ ያሳዩ ነበሩ። ብሔራዊ ቡድኑ በሩብ ፍጻሜው ከወቅቱ የአህጉሩ ጠንካራ ቡድን አልጄሪያ ጋር ሲጫወትም ትልቅ ጨዋታን ማሸነፍ የሚችሉት የአይቮሪኮስት አጥቂዎች ዌልፍሬድ ቦኒ እና ጀርቪንሆ ነበሩ ሶስቱንም የማሸነፊያ ጎሎች ያስቆጠሩት።
Ghana

ጠንካራ ፍልሚያ በታየበት የፍጻሜው ጨዋታ ዝሆኖቹ ከጥቋቁር ክዋክብቶቹ ጋር ሲገናኙ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ እና ተጨማሪ 30 ደቂቃ ጎል ማስቆጠር ተስኗቸው በመለያ ምት ሲለያዩ ጋና የዋንጫው ባለቤት ለመሆን ከጫፍ ደርሳ ነበር። የሃርቭ ሬናፕ ልጆች የመጀመሪያዎቹን ሁለት ፍጹም ቅጣት ምቶች ሲያባክኑ ጋናዎች የዋንጫውን አንድ ጆሮ እንደያዙ እርግጠኛ ሆነውም ነበር። ዳሩ ግን ከፍተኛ ልምድ ያካበተው የፓሪሴንት ጄርሜው ተከላካይ ኦሪየር ያስቆጠራት ፍጹም ቅጣት ምት ለኮትዲቯር ተስፋን ይዛ መጣች። የቱሬ ወንድማማቾች ኮሎ ቱሬና ያያ ቱሬ ተከታታይ ፍጹም ቅጣት ምቶችም አገሪቱን በፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ልምድ ታግዛ ዋንጫውን ማንሳት እንደቻለች ያሳየ ሆኗል።

ይህንን ነጥብ ከተመለከትን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፕሮፌሽናል ተጫዋች አለመኖሯ በአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ያላትን ምኞት ሳያደናቅፍ እንዳልቀረ እንድንገምት ያደርጋል። ለዚህ ነጥብ ማጠንከሪያ ሃሳብ ለማንሳት ቢያስፈልግ በ20ኛው የዓለም ዋንጫ በጥሎ ማለፉ ውድድር ጀርመንና አልጄሪያ ሲገናኙ የአሸናፊነት እድሉን ቀድማ ያገኘችው ጀርመን ብትሆንም በጨዋታው ግን ከአልጄሪያ የገጠማት ፈተና ቀላል አልነበረም። በ120 ደቂቃ እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ ጀርመን ማሸነፍ የቻለችው በቡድኗ ውስጥ ባካተተቻቸው ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ከፍተኛ ልምድ ታግዛ እንጅ በጨዋታ ከአልጀሪያ የተሻለች ሆና አልነበረም። በተመሳሳዩ በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ የአልጄሪያና የኮትዲቯር ጨዋታም የታየው የዝሆኖቹ ተጫዋቾች ፕሮፌሽናልነት በአልጀሪያዎቹ ጥንካሬ ላይ የበላይነቱን ወስዶ አልጄሪያን ተሸናፊ ሲያደርግ ነው።

የውድድሩ ክብደትና የዋሊያዎቹ ዝግጅት

የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከቀድሞው ይዘቱ ጋር ካስተያየነው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የውድድሩ ጠንካራነትና ተወዳጅነት እየቀነሰ መሆኑ ግልጽ ነው። ያም ሆኖ ግን በመድረኩ የሚካፈሉ ቡድኖች ሲጫወቱ የሚያሳዩት ፍጥነትና ጉልበት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ሲነጻጸር ዋሊያዎቹ ገና ሊሰሩት የሚገባ የቤት ስራ መኖሩን ያሳየ ሆኗል። ለአብነት ያህል አንድ ነጥብ ብቻ ለማንሳት ብንሞክር የጋና ብሔራዊ ቡድን የመሃል ሜዳ ሞተር የሆነው ዋካሶ በአንድ ጨዋታ በደረሰበት ጉዳት ቅንድቡን መሰበሩን እናስታውሳለን። ነገር ግን ዋካሶ ቅንድቡ በፕላስተር ታሽጎም ቢሆን ቀሪዎቹን ጨዋታዎች በሙሉ ብቃቱ ሆኖ ጨርሷል። በዋካሶ ላይ የደረሰው ጉዳት በኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ላይ ደርሶ ቢሆን የዋካሶን ጀብድ ይፈጽሙት ነበር ወይ? ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ ምን ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው ኢትዮጵያውያኑ የዋካሶን ያህል በቀሪዎቹ ጨዋታዎች ላይ አይሳተፉም።

ሌላው ውድድሩ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ያስተማረው በጎ ትምህርት የተጫዋቾች ፍጥነት ለቡድኖች አሸናፊነት ወሳኝ መሆኑን ነው። በእግር ኳስ ጨዋታ ፍጥነት ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ለስፖርቱ ቅርበት ያላቸውም ሆነ እግር ኳስን በሩቁ የሚከታተሉ ሰዎች የሚስማሙበት ነጥብ ነው። በውድድሩ ሩብ ፍጻሜና ግማሽ ፍጻሜ የአይቨሪኮስቱ አጥቂ ጀርቪንሆ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ስንመለከት የአጥቂው ፍጥነት ለየትኛውም የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች አስፈሪ መሆኑን ነው። በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአልጄሪያና በማላዊ ሲሸነፍ የተመለከትነው የተጋጣሚ ቡድን አጥቂዎች ለዋሊያዎቹ ተከላካዮች ፈታኝ በመሆናቸው ነበር።

የአሰልጣኞች የታክቲክ እውቀት

ይህንን ነጥብ የምንለካው የፍጻሜውን ጨዋታ ብቻ በመመልከት ይሆናል። እንደሚታወቀው በፍጻሜው የተገናኙት ሁለቱ ጎረቤታማቾች ጋና እና አይቮሪኮስት ሲሆኑ ሁለቱን ቡድኖች የሚያሰለጥኗቸውን አሰልጣኞች ሰብዕና እናያለን። በቅድሚያ የተሸናፊውን ቡድን አሰልጣኝ እስራኤላዊው አቭራም ግራንትን የቅርብ ጊዜ የአሰልጣኝነት ታሪክ ስንመለከት በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ፣ የኢሮፓ ሊግ ውድድርና በምድራችን ተወዳጅ ሊግ በሆነው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዘለቀ ልምድ አላቸው። አሰልጣኙ ታላቁን የእንግሊዝ ክለብ ቼልሲ ለአውሮፓ ቻምፒዪንስ ሊግ የፍጻሜ ተፋላሚ ማድረግ የቻሉ ሲሆን ትንሹን ፖርትስማውዝን ደግሞ ለኤፍኤ ካፕ የፍጻሜ ተፋላሚ ማድረግ ችለዋል። ከሁለቱ ክለቦች በተጨማሪም ዌስትሃም ዩናይትድንም ለካፒታል ዋን የፍጻሜ ተፋላሚ ማድረግ ችለው የነበረ ቢሆንም ከአንዱም ክለብ ጋር የዋንጫ ባለቤት መሆን አልቻሉም።
የዋንጫው ባለቤት የሆኑት የአይቮሪኮስቱ አሰልጣኝ ፈረንሳያዊው ሀቭሪ ሬናፕ ደግሞ በአገራቸው ፈረንሳይ በሚገኙ የታችኛው ሊግ ተወዳዳሪ ክለቦች የዘለለ የአውሮፓ ልምድ የላቸውም። ከዚህ ይልቅ ግለሰቡን ወደ ዝናው ዓለም ያመጣቸው ከዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ጋር 28ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ሲያነሱ ነው። የአፍሪካን እግር ኳስ ጠንቅቀው ያውቃሉ የሚባሉት ፈረንሳያዊው ሬናፕ ከእስራኤላዊው አቻቸው በልጠው የዋንጫውን አንገት እንዲጨብጡ ያደረጋቸው በእድል አይደለም። ከእድል ይልቅ የጋና አቻቸው በሰሩት ስህተት ነበር ማለት ይቻላል። የጋና ብሔራዊ ቡድን የውድድሩ ኮከብ ጎል አግቢ አንድሪ አየውን እና ኮከብ ተጫዋች ሆኖ የተመረጠውን አትሱን መያዝ ቢችልም አይቮሪኮስትን አሸንፎ ዋንጫውን ማንሳት አልቻለም። ለጋና ተሸናፊነት የተገለጸው ምክንያት አቭራም ግራንት በተጫዋች ቅያሪና አሰላለፍ ላይ ባሳዩት ስህተት ነው የሚል ነበር። በተለይ አፒያህ የተባለውን አጥቂ አሰልፈው ወጣቱን ጆርዳን አየሁን ተጠባባቂ ማድረጋቸው ትልቅ ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተነግሯል። አምበሉን አሳሞኣ ጂያንን በመለያ ምት መምቻ ሰዓት ቀይረው ማስወጣታቸውም ለኮትዲቯር አሸናፊነት ውለታ ሰርተዋል አስብሏቸዋል። የአሰልጣኞችን ታክቲካል ብቃት ከተመለከትን የዋሊያዎቹ አሰልጣኞችም ከውድድሩ ትምህርት የሚወስዱበት ይመስለናል።  

ዘገባ፦ ይርጋ አበበ
ኢትዮ ፉትቦል
ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!