ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለማድረግ አልጀርያ ገባ።
የካቲት 05, 2007

የትናንትናው ውሏችን በአጭሩ ይሄንን ይመስላል

ዕለተ ማክሰኞ ከለሊቱ አስር ሰአት ነበር ወደ አልጀርያ ኤል ኡልማ ከተማ ጉዞዋችንን የጀመርነው፡፡ጉዞዋችን እጅግ በጣም አሰልቺ እና አድካሚ የሚባል አይነት ነበር፡፡ አውሮፕላን ውስጥ ተቀምጠን የሄድንባቸውን ሰአታት ብንቆጥር እንኳን ከኢትዮጵያ ግብፅ ሶስት ሰአት፤ ከግብፅ አልጀሪያ ስድስት ሰአት እንዲሁም ከአልጀርስ ኮንስታንቲን አርባ አምስት ደቂቃ የአውሮፕላን ጉዞ አድርገናል፡፡ በአጠቃላይም በአውሮፕላን ብቻ አስር ሰአታትን ለመጓዝ ችለናል፡፡ በየኤርፖርቶቹ ላይ ለትራንዚት ሲባል ቢያንስ ለሁለት ሰአታት ያህል የጉዞዎችን ሰአት ጥበቃ ተቀምጠናል፡፡ ከኮንስታንቲን ኤል ኡልማ የአንድ ሰአት ጉዞ አድርገን ለስታዲየሙ ቅርብ ነው ወደ ተባለው አልማናራ ሆቴል ያመራነውም በመኪና ተጉዘን ነው፡፡ ሆቴላችን ስንደርስም በጉዞ እጅግ ተዳክመን ነበር፡፡ የቡድን መሪያችን አቶ ታፈሰ በቀለም ከዚህ በፊት ወደ ማንኛውም ሀገር ለጨዋታ ስንሄድ ሀሙስን እንጠቀም ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ጉዞ ተጨዋቾችን የሚያደክም መስሎ ስለታየን ረቡዕ ቀንን በመንገድ ላይ አሳልፈን ሀሙስ እና አርብን በትኩረት ልምምድ አድርገን ለጨዋታው ለመዘጋጀት ስንል ነው ጉዞውን ቀደም ብለን የጀመርነው ብለዋል፡፡

ትናንት ኤል ኡልማ ከተማ የገባው የቅዱስ ጊዮርጊስ ልኡካን ቡድን እስከ አሁን ድረስ ልምምድ ያልሰራ ሲሆን ከአንድ ሰአት በኋላ በአንድ የልምምድ ማዕከል ውስጥ ልምምዳችንን የምናከናውን ይሆናል፡፡ የአየር ሁኔታውን በተመለከተ በአሁኑ ሰአት በዚህች ከተማ ያለው አየር ከብዙዎቹ የሰሜን አፍሪካ ከተሞች የተለየ ሲሆን እጅግ በጣም ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ያለ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ከባድ በረዶን የቀላቀለ ዝናብ ጥሎ እንደነበር በየመንገዱ ዳር ያየነው እስከ አሁንም ያልጠፋው በረዶ ያሳብቃል፡፡ የክለባችን አስተዳደርም ይህንን ቀድሞ በመረዳት ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአውሮፓ አዳዲስ የተጨዋቾች የበረዶ ልብሶችን ገዝቶ ለተጨዋቾች የተከፋፈለ ሲሆን ተጨዋቾቹም እሱን በመልበስ በሆቴሉ ውስጥ ሲዘዋወሩ ታይተዋል፡፡

መላው የቡድኑ አባላት በአሁን ሰአት ምሳ ተመግበው እረፍት እያደረጉ ሲሆን ከአንድ ሰአት በኋላም ወደ ልምምድ የሚወጡ ይሆናል፡፡ የልምምድ ማዕከሉ አርተፊሻል ሳር የለበሰ መሆኑን የተነገረን ሲሆን ዋናውን ጨዋታ የምንጫወትበት ሜዳ ደግሞ ተፈጥሮዋዊ ሳር ነው ፡፡ ለዛሬ በዋናው ስታዲየም ልምምድ መስራት ስለማንችል የምንሰራው በአንድ የልምምድ መስሪያ ማዕከል ይሆናል ማለት ነው፡፡ 

ፍጹም ገብረ ማርያም ትናንት የልደት ቀኑ ነበር፡፡  በአንድ ቀን በሶስት ሀገራትም ልደቱ የተከበረለት ተጨዋች ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ፤ ከዚያም ግብፅ ስንደርስ በግብጽ አየር ማረፊያ ውስጥ በቸኮላት ልደቱን ያከበርንለት ሲሆን፤ አልጄርያ ከገባን በኋላም እንዲሁ መልካም ልደት የሚለው መዝሙር ተዘምሮለታል፡፡

መረጃዎችን ማግኘት ለምትፈልጉ በስልክ ቁጥር 0779496043 በመደወል ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ይቻላል፡፡


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!