ትኩረት የሚያሻው የግብ ጠባቂዎች ጉዳይ? ፕሪሚየር ሊጉ ከውጪ በተገዙ በረኞች እየተጨናነቀ ነው።
የካቲት 10, 2007

- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አምስቱ ክለቦች ቋሚ ግብ ጠባቂዎቻቸው የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ናቸው። 

-የደደቢት የግብ ክልል ከዚህ ወር ጀምሮ በጋናዊ ግብ ጠባቂ ሊጠበቅ ተወስኖለታል።

-ወልድያ ከነማ ለውጤቱ መጥፋት ምክንያቱ ብዙ ቢሆንም የውጭ አገር ግብ ጠባቂ ያስፈልገኛል ብሎ ካሜሩናዊ በረኛ ማስመጣቱ ተነግሯል።

በ2004 ዓ.ም ሶስተኛ ሩብ ዓመት አካባቢ ነው የኢትዮጵያን እግር ኳስ ችግር ከምንጩ ለማወቅና የችግሩን ምንጭ ለማድረቅ ጥናት የሚያደርግ ቡድን ተቋቁሞ የጥናቱን ውጤት ያቀረበው። አጥኚው ቡድን የጥናቱን ውጤት ይፋ ሲያደርግ “የኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግሩ የግብ ጠባቂ ነው” ሲል ደመደመ። ስለዚህም ፌዴሬሽኑ በዚህ ቦታ ላይ ጠንከር ያለ ስራ መስራት አለበት የሚል ሃሳብ ሰነዘረ። ጥናቱ ከተካሄደ ከሶስት ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሚወዳደሩ 14 ክለቦች መካከል አምስቱ ከቡድናቸው ቋሚ ብረቶች መካከል የሚቆሙ የጎል ዘበኞች የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ናቸው። 

የውጭ አገር በረኞች የነማንን የግብ ክልል ይጠብቃሉ?

በአሁኑ ወቅት ተወዳጅ ከሆኑት የዓለማችን ሊጎች መካከል ቀዳሚ የሆነው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን በምሳሌነት አንስተን የሊጉን ክለቦች የግብ ክልል በትጋት የሚጠብቁ ግብ ጠባቂዎችን ማንነትና ዜግነት እንመልከት። የሸክ መንሱር የግል ንብረት ነው እየተባለ የሚነገርለት ማንቸስተር ሲቲ በሶስት ዓመታት ውስጥ ሁለት የፕሪሚየር ሊግና አንድ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ሲያነሳ የቡድኑን ምሽግ በንቃት የጠበቀው እንግሊዛዊው ጆ ሃርት ነበር። ከማንቸስተር ሲቲ ውጭ ያሉ ስድስቱ ታላላቅ ክለቦች ማለትም ማንቸስተር ዩናይትድ፣ አርሴናል፣ቼልሲ፣ ሊቨርፑል፣ ቶተንሃምና ኤቨርተን በውጭ አገር ግብ ጠባቂዎች የሚጠበቅ የግብ ክልል አላቸው። 

የእንግሊዝን ፕሪሚየር ሊግ ተሞክሮ ወደ አገራችን ስናመጣው ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ እናገኘዋለን። የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በተከታታይ በማንሳት ቀዳሚ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉን ዋንጫ 11 ጊዜ ሲያነሳ የክለቡን የግብ ክልል በኢትዮጵያውያን ግብ ጠባቂዎች እየጠበቁ ዋንጫ ያነሳው ስድስት ጊዜ ብቻ ነው። 
Robert St.George goalkeeper

በአሁኑ ወቅትም የክለቡን የግብ ክልል በቋሚነት እየጠበቀ ያለው ዩጋንዳዊው ሮበርት ኦዶንካራ ነው። ከዓሊ ረዲ በኋላ አስተማማኝ ግብ ጠባቂ ማግኘት አልቻለም እየተባለ የሚተቸው ኢትዮጵያ ቡና በዚህ ወቅት ከያዛቸው ሶስት የቡድኑ ግብ ጠባቂዎች መካከል አንደኛው ናይጄሪያዊው ኔልሰን ነው። 

ከሁለቱ ክለቦች በተጨማሪ በዚህ የውድድር ዓመት ከብሔራዊ ሊጉ ያደገውና በጠንካራ አቋም ላይ የሚገኘው አዳማ ከነማ ግብ ጠባቂው ሩዋንዳዊ ነው። ያለፉትን ሶስት ዓመታት በቋሚነት ሲሳይ ባንጫ ተቆጣጥሮት የነበረው የደደቢት የግብ ክልል ከዚህ ወር ጀምሮ በጋናዊ ግብ ጠባቂ ሊጠበቅ ተወስኖለታል። በዚህ ዓመት ፕሪሚየር ሊጉን ተቀላቅሎ አጀማመሩ ያላማረለት ወልድያ ከነማ ለውጤቱ መጥፋት ምክንያቱ ብዙ ቢሆንም የግብ ጠባቂው ግን የጎላ በመሆኑ የውጭ አገር ግብ ጠባቂ ያስፈልገኛል ብሎ ካሜሩናዊ በረኛ ማስመጣቱ ተነግሯል። 

ኢትዮጵያዊ ግብ ጠባቂዎች ለሊጉ አይመጥኑም?

በርካታ አስተያየት ሰጭዎች ስለ ኢትዮጵያውያን ግብ ጠባቂዎች ሲናገሩ የሚደጋገመው ሃሳብ የግብ ጠባቂዎች ብቃት ሊያድግ ያልቻለው ፕሮፌሽናል የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ስለሌለ ነው ጠንካራ ግብ ጠባቂዎች በአገራችን የሌሉት የሚለው ነው። በተለያዩ የእድሜ ክልሎች የሚገኙ የአገራችን ብሔራዊ ቡድኖች በሚያደርጉት የነጥብም ሆነ የወዳጅነት ጨዋታዎች በርካታ ጎሎች የሚቆጠሩባቸው በግብ ጠባቂዎች ስህተትና እንዝላልነት የተነሳ መሆኑን ተመልክተናል። ግን ለብሔራዊ ቡድኑም ሆነ ለፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የሚመጥኑ ግብ ጠባቂዎችን የአገራችን ምድር ማፍራት አልቻለም? የሚለውን ጥያቄ ስናነሳ መልሱ ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን።

የኢትዮጵያ ክለቦችን የሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች ያልተሰራን ተጫዋች ፈልገው በማግኘት መሞረድና ወደ ታላቅ ደረጃ ማድረስ ወይ አይፈልጉም አለዚያ ለዚህ አይነት ችሎታ አልታደሉም። ይህንን ጠንከር ያለ ትችት መሰል አስተያየት እንድንሰነዝር ካስገደዱን ነጥቦች መከካል በመንግስት በጀት የሚተዳደረውና በርካታ ገንዘብ ወጥቶበት ስራ የጀመረው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚን ክለቦች ሲጎበኙት አለመታየቱ ነው። ሌላው ነጥብ ደግሞ በቅርቡ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ አስተናጋጅነት ሲካሄድ በሰነበተው የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ውድድር ላይ በስፍራው ተገኝቶ የወጣቶችን ምትሃታዊ ችሎታ ተመልክቶ ለማስፈረም ያሰበ ክለብ በጣም ውስን ነበር። ይህ ባይሆን ኖሮ እንኳን ለፕሪሚየር ሊጉ ተወዳዳሪ ክለቦች ይቅርና በአፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ ግብ ጠባቂ በአገሪቱ የማይኖርበት ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም ነበር። 

የወደፊት የአገሪቱ  እግር ኳስ  እጣ ፈንታስ?

ለ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አዲስ አበባ ላይ በማሊ አቻው ሁለት ለባዶ ተሸነፈ። የቡድኑ አሰልጣኝ ፖርቹጋላዊው ማሪያኖ ባሬቶ ለጋዜጠኞች ድህረ ጨዋታ መግለጫ ሰጡ። አሰልጣኙ በጊዜው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አስተያየት የሰጡ ቢሆንም በተለይ ትኩረት ያደረጉት “አገራችሁ ውስጥ ጥሩ አጥቂ ለማግኘት ሞክሬ ነበር ነገር ግን ታላላቆቹን ክለቦች ስመለከት በውጭ አገር አጥቂዎች የተሞሉ ሆነው አገኘኋቸው። ሰለዚህ የነበረኝ አማራጭ ባሉኝ ልጆች ተጠቅሜ ቡድኔን ገነባሁ” ሲሉ አገሪቱ ውስጥ የአጥቂዎቸ ድርቀት መኖሩን የጠቆሙበት አስተያየት ነበር። አሁን አሁን ግን አገሪቱ ውስጥ አጥቂ ብቻ ሳይሆን የግብ ጠባቂዎችም ጉዳይ ትኩረት ያልተሰጠው አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ ብቅ ብሏል። በተለይ አሁን ያለው የክለቦች አካሄድ በእጅጉ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። ያገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ ብቻ ሳይሆን የአገሩን መረብ በአገሩ ጎል ጠባቂ የምንልበት ዘመን አሁን ይሁን!! 

ትንታኔ፦ ይርጋ አበበ 
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!