በዩኒቨርስቲዎች ውድድር ከደመቁት ወጣቶች መካከል በጥቂቱ
የካቲት 13, 2015

 ባሳለፍነው ሳምንት የተጠናቀቀው ስምንተኛው የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ውድድር በእግር ኳስ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአሸናፊነት ማጠናቀቁ ይታወሳል። በስፖርት ውድድሩ ከአስር በላይ የስፖርት አይነቶች የተካሄዱ ቢሆንም የበርካቶችን ቀልብ መሳብ የቻለው ግን በእግር ኳስ ጨዋታ ላይ የታየው የወጣቶች ክህሎት ነው። ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች በሚያስብል መልኩ በውድድሩ ጠንካራ ቡድን ይዘው የቀረቡ ሲሆን በተለይ የምስራቅ ኢትዮጵያው ጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ የውድድሩ ክስተት ሆኗል። ጂጅጋ ዩኒቨርስቲ በሩብ ፍጻሜ አስተናጋጁን አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርስቲን በመለያ ምት አሸንፎ ወደ ግማሽ ፍጻሜ እንዲያልፍ የአንበሳውን ድርሻ የወሰደው የቡድኑ አምበልና አጥቂ መሃሙድ መሀመድ የተባለው አጥቂው ነው።

Mohmud Mehamed

ተወልዶ ባደገበት ምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢ ለሚገኘው አፍረን ቀሎ ለሚባል ክለብ እንደሚጫወት የተነገረለት ወጣት ከኳስ ጋር ያለው ዝምድና እጅግ የሚገርም የሚባል አይነት ነው። ከተከላካዮች ጋር ሲገናኝ ፍጹም የማይረበሽ ሲሆን በሁለቱም እግሮቹ የሚጠቀም መሆኑ ደግሞ ተጫዋቹን ይበልጥ ተመራጭ ያደርገዋል። ፍጥነቱና ጉልበቱ ደግሞ ለተፈጥሯዊ ቴክኒካል ችሎታው አድማቂዎቹ ናቸው። እነዚህ ችሎታዎቹ ደግሞ ተጫዋቹ ቡድኑን እስከ ግማሽ ፍጻሜ እንዲጓዝ ያስቻሉት ሲሆን በተለይ በጥሎ ማለፉ ሃዋሰ ዩኒቨርስቲንና በሩብ ፈጻሜው ደግሞ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርስቲን አሸንፈው ወደ ቀጣዩ ዙር እንዲያልፉ አስችለውታል። ታላላቆቹ ክለቦች ወጣቱን ልጅ በቅርበት ቢመለከቱትና የሙከራ እድል ቢሰጡት ልክ እንደ ዳዋ ሁጤሳ ሁሉ መሃሙድ መሀመድም ተስፋ ያለው መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም የሰጡ ተመልካቾች ገልጸዋል።

 ውድድሩ ሲከፈት በመክፈቻው የተገናኙት ቀድሞ በአንድ ዩኒቨርስቲ ስም ይጠሩ የነበሩት በቅርቡ ግን በአዋጅ መለያየታቸው የተገለጸው አርሲ ዩኒቨርስቲና አስተናጋጁ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርስቲ ነበሩ። በዚያ ጨዋታ በአዲሱ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ስታዲየምም ሆነ ለውድድሩ የመክፈቻውን ጎል ያስቆጠረው እንግዳው ቡድን አርሲ ዩኒቨርስቲ ሲሆን የጎሏ ባለቤት ደግሞ አምበሉ ሀይለሚካኤል ብርሃኑ ነው። 
ሀይለሚካኤል ብርሃኑ

አጥቂው ሀይለሚካኤል ብርሃኑ ከኢትዮፉትቦል ዶትኮም ጋር ባደረገው አጠር ያለ ቃለ ምልልስ እንደገለጸው ተወልዶ ያደገው በርካታ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን ባፈራችው ሃዋሳ ከተማ ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ እግር ኳስ እየተጫወተ ማደጉን የሚናገረው ሀይለሚካኤል በፕሮጀክት ታቅፎ ከተማ አስተዳደሩን፣ ሲዳማ ዞንና ደቡብ ክልልን ወክሎ ተጫውቷል። 

“የከፍተኛ ትምህርት እድል ሲመጣልኝ ትኩረቴን ወደ ትምህርቱ በማዞሬ እንጅ ራዕዬ ኳስ ተጫዋች መሆን ነው” የሚለው ወጣቱ አጥቂ “አሁን ግን በዚህ ዓመት ትምህርቴን ስለማጠናቅቅ ወደ እግር ኳሱ ትኩረቴን ማዞር እፈልጋለሁ” ሲል ይናገራል። አያይዞም ክለቦች በሙከራ ችሎታውን እንዲፈትሹለት ሲናገር የሙከራ ጊዜውን በድል እንደሚወጣ በልበ ሙሉነት ነበር። ዘጠና ደቂቃ ሙሉ መሮጥ የማይደክመውና የሀይል አጨዋወትን ተጠቅሞ መጫወት መገለጫው የሆኑት የአርሲ ዩኒቨርስቲው አጥቂ በስምንተኛው የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስፖርት ውድድር ላይ ከፍ ወዳለ ደረጃ የመሸጋገር እድል ካላቸው ወጣቶች አንዱ ለመሆን ሁሉንም መስፈርት ያሟላ ተጫዋች ነው።

 ሰባተኛው የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ስፖርት ውድድር የተካሄደው በምስራቁ የአገራችን ክፍል ከሚገኙት ዩኒቨርስቲዎች አንዱ በሆነው ሀሮማያ ዩኒቨርሰቲ ነበር። በዚያ ውድድር በእግር ኳስ ለፍጻሜ የቀረቡት የሰሜን ኢትዮጵያው ተወካይ መቀሌ ዩኒቨርሰቲና የምዕራብ ኢትዮጵያ ተወካዩ አምቦ ዩኒቨርሰቲ ሲሆኑ በውጤቱም ሰሜኖቹ አንድ ለባዶ አሸንፈው የዋንጫው በላቤት መሆናቸው ይታወሳል። ሁለቱ ቡድኖች በዚህ ዓመትም በግማሽ ፍጻሜው ተገናኝተው በተመሳሳይ ውጤት መቀሌ ዩኒቨርሰቲ አሸንፎ ወደ ፍጻሜው ተቀላቅሏል። ሁለቱን ጨዋታዎች ጨምሮ በሁሉም የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ጨዋታዎች ከቡድኑ ጎልቶ የሚወጣውና በአመለ ሸጋነቱ የተመሰገነው ተጫዋች ከጋምቤላ ክልል የተገኘው ጋምቤላ የሚባለው ተከላካይ ነው።

 ተከላካዩ እድሜው በግምት ሃያን መድፈር እንኳ ያልቸኮለ መሆኑ ተክለ ሰውነቱና አጠቃላይ ገጽታው ያሳብቃሉ። ረጅምና ፍጹም ቀጭን የሆነው ጋምቤላ ተወልዶ ያደገው ጋምቤላ ከተማ ውስጥ መሆኑን ይናገራል። አጨዋወቱና ቁመቱ ከኢትዮጵያ ቡናው አማካይ ተከላካይ ጋቶች ፓኖም ጋር የሚመሳሰለው የመቀሌ ዩኒቨርሰቲው ተከላካይ ፍጹም የተረጋጋና አመለ ሸጋ ነው። አጥቂዎችን ከጨዋታ ውጭ የማድረግ ሲስተም ሲጠቀምም ሆነ ከአጥቂዎች ጋር ፊት ለፊት ሲገናኝ የማይረበሽ መሆኑ መለያዎቹ ናቸው። ፍጥነቱም ቢሆን አንድ ተከላካይ ሊይዘው ከሚገባው በላይ ፈጣን ሲሆን የአየር ላይ ኳስ ሲሻማም በበላይነት የሚያጠናቅቀው እሱ ነው። ይህ በአስራዎቹ መጨረሻ ላይ የሚገኝ ወጣት እጅግ በጣም በቅርቡ ወደ ከፍተኛ ደረጃ መደረስ የሚያስችል እድል እንዳለው ምልክቶች አመላክተዋል። ክለቦችም ሆነ የታዳጊና የወጣት ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞችና መልማዮች ጋምቤላን ጨምሮ ከላይ በጠቀስናቸውና ወደፊት ችሎታቸውን በምናቀርብላቸው ወጣቶች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ መልዕክታችን ነው።

ዘገባ፦ይርጋ አበበ
ኢትዮ ዩትቦል
ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Hailemichael Birhanu [1024 days ago.]
 First of all i would d like to thank this web and and its reporters for promoting young and talented players from such tournament, i believe this is a big opportunity for clubs & players. I suggest clubs to pay attention to such tournaments from which our country could get talented players to our national team in the future like Fitsum Teferi.

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!