ማውንቴን አዳማ የመጀመሪያ የነጥብ ጨዋታውን አካሄደ
የካቲት 16, 2007

አዳማ ከተማ ሁለተኛ ክለብ ማግኘቷን በቅርቡ መዘገባችን ይታወሳል። ለአዳማ ከተማ ወጣቶችና እግር ኳስ አፍቃሪ ህዝብ ሁነኛ አማራጭ ሆኖ የቀረበው ክለብ ደግሞ ማውንቴን አዳማ እግር ኳስ ክለብ መሆኑንም ዘግበን ነበር። ማውንቴን አዳማ እግር ኳስ ክለብ ህጋዊ ሰውነት አግኝቶ በምስርቅ ሸዋ ዞን የክለቦች ውድድር ለመሳተፍ ሲጠባበቅ ቆይቶ ባሳለፍነው ማክሰኞ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከመተሃራ ከነማ ጋር መተሃራ ላይ ተጫውቷል። ሁለቱ ቡድኖችም ጨዋታቸውን ሁለት እኩል በሆነ ውጤት አጠናቀዋል።
Mountain Adama

የክለቡ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ጥላሁን “ክለባችን የመጀመሪያ የነጥብ ጨዋታ እንደማድረጉና ጨዋታውም ከሜዳችን ውጭ እንደመሆኑ ውጤቱ ተስፋ ሰጭ ሆኖ አግኝተነዋል። ተጋጣሚያችንን እስከ መጨረሻው ደቂቃ እየመራን ቆይተን ባለቀ ሰዓት የተቆጠረችብን ጎል ነጥብ ተጋርተን እንድንወጣ አስገደደን እንጅ በመጀመሪiያ ጨዋታችን ከሜዳችን ውጭ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘን ለመውጣት ተቃርበን ነበር” ሲሉ ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም ተናግረዋል።

ከጨዋታው አንድ ቀን ቀደም ብሎ አስተያየቱን ለዝግጅት ክፍላችን የሰጠው የክለቡ አማካይ ተከላካይ ደረጀ አበበ በበኩሉ”የመጣሁት ከመተሃራ ነው። ምኞቴ ኳስ ተጫዋች መሆን ሲሆን እንደምታየው አዳማ ውስጥ ክለብ ያለው አንድ ብቻ ነው። እሱም ቢሆን ቡድኑን የሚያጠናክረው ወጣቶችን በማሳደግ ሳይሆን የበቁ ተጫዋቾችን ከሌሎች ክለቦች በማስፈረም በመሆኑ ለእኛ ለወጣቶች ሁሉም ነገር ዝግ ነበር። አሁን ግን ይህ ክለብ በመመስረቱ እኔ ብቻ ሳልሆን ቁጥራቸው በርከት ያሉ የከተማው ወጣቶችም ህልማቸውን እውን ለማድረግ ምቹ መድረክ ሆኖልናል” ሲል ይናገራል።

የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አቶ አፈወርቅ ደግሞ ቀደም ባሉት ዓመታት የተለያዩ ክለቦችን በማሰልጠን ልምድ እንዳለው ገልጾ ማውንቴን አዳማ እግር ኳስ ክለብን ለማሰልጠን የተስማማው ክለቡ ያለውን ራዕይ ከመስራቾቹ ጋር ቁጭ ብሎ ከተወያየ በኋላ መሆኑን ይናገራል።
Afework Mountain Adama Coach

አሰልጣኝ አፈወርቅ አያይዞም ማውንቴን አዳማ እግር ኳስ ክለብ በቅርብ ዓመታት ውስጥ አዳማ ከተማን በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚወክል ክለብ ሆኖ እንደሚቀርብ በእርግጠኝነት ነው የሚናገረው።

ከክለቡ መሰራቾች አንዱ የሆኑት አቶ ዳምጠው ገመቹ ግን የክለቡ ራዕይ በኢትዮጵያ ፕሪሚር ሊግ መሳተፍ አይደለም ይላሉ። አቶ ዳምጠው የክለቡን ራዕይ ሲገልጹ “የስፔን ብሔራዊ ቡድን ከ2008 እስከ 2012 የተካሄዱ የአውሮፓ ዋንጫና የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ የነገሰው ከባርሴሎና እግር ኳስ አካዳሚ በተገኙ ተጫዋቾች መሆኑ ይታወሳል። የእኛ አገርም በቅርብ ዓመታት ውስጥ በአህጉሩ ውድድሮች ላይ ወደ ንግስናው እንድመጣ ከክለባችን ታዳጊዎች ማሰልጠኛ የሚወጡ ወጣቶች ትልቅ ግብአት እንዲሆኗት እንሻለን። ለዚህ ደግሞ እድሜያቸው ከሰባት ዓመት ጀምሮ እስከ 17 ዓመት ያሉ ህጻናትንና ታዳጊዎችን ይዘን ወደ ስልጠና ገብተናል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ክለባችን በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ብቻ ሳይሆን አገሩን ወክሎ በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድር ብርቱ ተፎካካሪ እንዲሆን ማድረግ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ደግሞ ጌጡ ነው እንዲሉ ማውንቴን አዳማ እግር ኳስ ክለብ የተወሰኑ ወጣቶች ከኪሳቸው ሳይቀር እያወጡ የሚደግፉትና የአዳማ ከተማ ነዋሪን ጨምሮ ሁሉም እግር ኳስ አፍቃሪ ህዝብ በገንዘብ እየደገፈ በባለቤትነት የሚከታተለው ማውንቴን አዳማ እግር ኳስ ክለብ አሁን ሙሉ በሙሉ ወደ ውድድር ገብቷል። በሜዳው የሚያካሂዳቸውን ጨዋታዎች በአዳማው አበበ ቢቂላ ስታዲየምና ሌሎች ሁለት ስታዲየሞችን እንዲጠቀም ከከተማ አስተዳደሩ ፈቃድ የተሰጠው ቢሆንም የክለቡ መሰራቾች ግን ክለባችን የራሱ ሜዳ ሊኖረው ይገባል ብለው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ምንም እንኳ የስታዲየም ግንባታ ወጭ ከባድ ቢሆንም የማውንቴን አዳማ እግር ኳስ ክለብ መስራቾች ግን ይህን ለማሳካት የክልሉ መንግስት፣ ህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ከጎናቸው ከሆኑ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በራሳቸው ስታዲየም የሚጫወቱ ክለብ ሆነው ብቅ እንደሚሉ ይናገራሉ።

ክለቡ በአሁኑ ወቅት የሚለማመደው ከተማዋ ውስጥ በሚገኝ አንድ አቧራማና ለልምምድ በማይመች ሜዳ ነው። በዚያ ሜዳ ሲጫወቱ ወጣቶቹ ችሎታቸውን አውጥተው ማሳየትት ካለመቻላቸውም በላይ ለጤናቸውም አስጊ ነው ማለት ይቻላል ምክንያቱም ከመሬቱ የሚነሳው አቧራ ለጤና ጠንቅ ነውና። የክለቡ መስራቾች ግን “የመለማመጃ ሜደውን ችግር በተመለከተ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ተነጋግረናል። በቀጣዮቹ ወራት ውስጥ ሜዳውን አሳጥረን አረንጓዴ የማድረግ ስራውንም እናከናውናለን። ለዚህ ደግሞ ማዘጋጃ ቤት አብሮን ለመስራት ተስማምቷል” ሲሉ ይናገራሉ።

እንደ ማውንቴን አዳማ አይነት በህዝብ ትብብር የሚቋቋሙ ክለቦች ከከተማው ነዋሪዎች ጨምሮ ሌሎች አካላትም ድጋፍ የሚቸራቸው ከሆኑ በአገራችን ያለውን የክለቦች አወቃቀር በማስቀረት ህዝባዊነት የተላበሱ ክለቦችን ቁጥር እንዲበዙ ያደርጋል።  ክለቦች ከመንግስት ድጎማና ቀጥተኛ ተረጅነት ተላቀው ህዝባዊ ክለብ ሆነው በሁለት እግራቸው ሲቆሙ በሌሎች አገሮች እንደምናየው የእግር ኳስ እድገት በአገራችንም ይታያል ማለት ነው። ይህ ደግሞ እግር ኳሱን ወደ ቢዝነስ በመቀየርና የተጫዋቾቹንም ሆነ የአሰልጣኞቹን ኪስ ከማዳጎሱም በላይ ባላሃብቶች በእግር ኳሱ ላይ መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ይጋብዛቸዋል። ለዚህ ደግሞ እንደ ማውንቴን አዳማ አይነት የህዝብ ክለቦችን በማንኛውም መንገድ በመደገፍ እግር ኳሳቻንን ማሳደግ እንችላለን ማለት ነው።

ሪፖርታዥ፦ይርጋ አበበ
ኢትዮ ፉትቦል


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!