ፓሽን እግር ኳስ አካዳሚ ፈረንሳያዊ አሰልጣኝ ቀጠረ
የካቲት 19, 2007

ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ የተቋቋመው ፓሽን የእግር ኳስ አካዳሚ የቀድሞውን የሴንት ኤቲዮን ግብ ጠባቂ ኒኮላስ ሳንቹዚ ልምዳቸውን ለአካዳሚው ታዳጊዎች እንዲያካፍሉ ጠራ። ትናንት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል መግለጫ የሰጡት የአካዳሚው መስራቾች “አካዳሚው ሲከፈት አላማ አድርጎ የተነሳው ለታዳጊዎች የስልጠና እና የጨዋታ ልምድ ማመቻቸት ሲሆን ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ልምድ ያላቸውን የውጭ አገር አሰልጣኞች ወደ አገር ቤት በማስመጣት ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ማድረግ ነበር። በዚህ በኩል ካየነው ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ 18 ተጫዋቾችን የያዘ ቡድን ወደ አሜሪካ ቺካጎ ወስደን የጨዋታ ልምድ አግኝተናል። አሁን ደግሞ ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን አሰልጣኝ ወደ አገራችን በማስመጣት ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ስላሰብን ነው አሰልጣኙን ያስመጣናቸው” ብለዋል።

የአካዳሚው መስራቾች በተለይ ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም እንደገለጹት ፈረንሳያዊው አሰልጣኝ ስልጠና የሚሰጡት ለፓሽን እግር ኳስ አካዳሚ ሰልጣኞች ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሰልጣኞችም ልምዳቸውን ያካፍላሉ። “የአገራችን እግር ኳስ እድገት ማነቆ ሆኖ የቆየው ሳይንሳዊ ስልጠናና የዓለም አቀፍ ውድድር ልምድ ማጣት ነው። ፓሽን እግር ኳስ አካዳሚም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ወደ ስራ ገብቷል” ያሉት ከአካዳሚው መስራቾች አንዱ የሆኑት ኢንስትራክተር አብርሃም ናቸው። ሌላው የአካዳሚው መስራች የቀድሞው የኢትዮጵያ መድን፣ የኢትዮጵያ ቡና እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ አሰግድ ተስፋዬ “ለአካዳሚው ሰልጣኞች ዓለም አቀፍ የውድድር ልምድ እንዲኖራቸው እቅድ በያዝነው መሰረት ባለፈው ዓመት ወደ አሜሪካ ቺካጎ በመሄድ የመጀመሪያ ጨዋታችንን ማድረጋችን ይታወሳል። በቀጣይ ደግሞ ወደ ስዊድንና ጣሊያን በመሄድ ውድድር እናካሂዳለን” ሲል ተናግሯል።

የፓሽን እግር ኳስ አካዳሚ ሰልጣኞችን ጨምሮ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ወጣቶች ስልጠና ለመስጠት የመጡት ፈረንሳያዊው ኒኮላስ ሳንቹዚ ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ያላቸውን እውቀት ተጠይቀው “የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት በደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ነበር። በጊዜው ቡድኑን ስመለከት በጣም ድንቅ የእግር ኳስ ክህሎት ያላቸው ተጫዋቾችን ስመለከት ተገርሜያለሁ። ከዚያ በፊት የነበረኝ ግንዛቤ የተሳሳተ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ። አገራችሁ በአትሌቲክሱ ያላት ደረጃ ከፍ ያለ ሲሆን በእግር ኳስም የአትሌቲክሱን ያህል ከፍ እንድትል ወደ ፊት ሰፊ ስራ አብሬ ለመስራት ከፓሽን አካዳሚ ጋር ፍላጎት አለኝ” ሲሉ ተናግረዋል።

አሰልጣኝ ኒኮላስ ሳንቹዚ የእግር ኳስ ታሪካቸውን የጀመሩት በግብ ጠባቂነት ሲሆን በተለይ ለፈረንሳዩ ታላቅ ክለብ ሴንት ኤቲዮን ተጫውተው አሳልፈዋል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ተዘዋውረው በመስራት ልምድ ማካበታቸውን ግለ ታሪካቸውን የሚገልጸው ዶክመንት ሲቪ ያሳያል። አሰልጣኙ ተዘዋውረው  ከሰሩባቸው አገራት መካከል ወደ ግብጽ ተጉዘው አሌክሳንድሪያ የሚባለውን ክለብ፣ ወደ ኮንጎ ተጉዘው ታላቁን ቲፒ ማዜንቤንና ወደ ሞሪታኒያ በመጓዝ የሞሪታኒያን ብሔራዊ ቡድን በምክትል አሰልጣኝነት መስራት ችለዋል።

ፓሽን እግር ኳስ አካዳሚ ከተቋቋመ አንድ ዓመት ያለፈው ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለ165 ታዳጊዎች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል። ከእነዚህ ታዳጊዎች መካከል 48 ታዳጊዎችን በነጻ የሚያሰለጥን መሆኑን መስራቾቹ ገልጸዋል። መስራቾቹ አያይዘውም አካዳሚው በሙሉ አቅሙ እየሰራ አለመሆኑን ገልጸው ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ “የሜዳ ችግር ስላለብን ነው። ወደ ፊት መንግስት ችግራችንን ተመልክቶ መፍትሄ እንደሚሰጠን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል። 

 ፈረንሳያዊውን አሰልጣኝ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስልጠና እንዲሰጡ ያመቻቹት የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አቶ ግርማ ሳህሌ ናቸው። አቶ ግርማ በተለይ ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም እንደገለጹት ከዚህ በኋላም የእግር ኳስ ልምድ ያላቸውን ሌሎች ባለሙያዎችን ጨምሮ ጋዜጠኞችንም ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ምዳቸውን እንዲያካፍሉ ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ።

ዘገባ፦ ይርጋ አበበ
ኢትዮ ፉትቦል


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!