የባህር ዳር ሰታዲየም የመጀመሪያ ኢንተርናሽናል ጨዋታ ዛሬ ያካሂዳል
የካቲት 21, 2007

ከሰባት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበትና በአገራችን በግዝፈቱ የመጀመሪያ የሆነው የባህርዳር ሁለገብ ብሔራዊ ሰታዲየም ዛሬ የደደቢትንና የሲሸልሱን ኮትዲኦርን ጨዋታ በማስተናገድ የመጀመሪያ ኢንተርናሽናል ግጥሚያ ያካሂዳል። ሁለቱ ቡድኖች ከ15 ቀናት በፊት በሲሸልስ ያደረጉትን የመጀመሪያ ጨዋታ በእንግዳው ቡድን ሶስት ለሁለት አሸናፊነት መጠናቀቁ የሚታወስ ሲሆን የደደቢቱ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሳህሌ ግን “የመጀመሪያ ጨዋታችንን በሰው ሜዳ እንዳሸነፍን ሁሉ እነሱም በሰው ሜዳ ሊያሸንፉ ስለሚችሉ በዛሬው ጨዋታ ሳንዘናጋ እንጫወታለን” ማለታቸውን የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል። 
Bahirdar Stadium

 የሲሸልስ ኢሚግሬሽን ህግ ከምዕራብ አፍሪካ የሚሄዱ ተጓዦችና ከሌሎች የዓለም ክፍል የሚሄዱ መንገደኞች ወደ አገሪቱ የሚያስገባቸው ቪዛ የተለያየ በመሆኑ ከ15 ቀናት በፊት በተካሄደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ደደቢት አራት የምዕራብ አፍሪካ ተጫዋቾቹን ሳያሰልፍ መጫወቱ ይታወሳል። ወደ ሲሸልስ የሚያስገባቸውን ቪዛ ባለማግኘታቸው በመጀመሪያው ጨዋታ ለክለባቸው ያልተሰለፉት አራቱ ምዕራብ አፍሪካውያን የደደቢት ተጫዋቾች አዳሙ መሃመድና ሸይቩ ጅብሪልን ጨምሮ አዲስ ፈራሚው ግብ ጠባቂ ይገኙበታል። በዛሬው ጨዋታ ከአራቱ ምዕራብ አፍሪካውያን ተጫዋቾች በተጨማሪ ጉዳት ላይ የነበረው ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት በአሰላለፍ ውስጥ የሚገቡ መሆናቸውን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። 

በአፍሪካ ቻምፒዮን ሊግ እየተሳተፈ ያለው የ11 ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ነገ በባህርዳር ብሔራዊ ሁለገብ ሰታዲየም ከአልጄሪያው ኤል ኤሉማ ክለብ ጋር ይጫወታል። በዚህ ጨዋታ ፈረሰኞቹ በባህር ዳር ከሚገኘው ደጋፊያቸው በተጨማሪ 50 አውቶብሶችን ክለቡ ያዘጋጀ በመሆኑ በርካታ የክለቡ ደጋፊዎች ወደ ባህር ዳር ተጉዘው ቡድናቸውን የሚያበረታቱ መሆኑ ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ የባህር ዳር ከተማ ወጣቶችና ነዋሪ በሙሉ ክለቡን በታላቅ ክብር አቀባበል ማድረጉን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። 

ሁለቱ ቡድኖች ከ15 ቀን በፊት አልጄሪያ ላይ በነበራቸው ጨዋታ ባለሜዳው ቡድን አንድ ለባዶ በሆነ ጠባብ የጎል ልዩነት ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን በዛሬው ጨዋታ ግን ፈረሰኞቹ ውጤቱን መቀልበስ እንደሚችሉ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ብራዚላዊው ዶ ሳንቶስ ተናግረዋል። 

የደደቢትንም ሆነ የቅዱስ ጊዮርጊስን ቡድኖች አሰላለፍ ማግኘት ባለመቻላችን የቡድኖቹን ቋሚና ተጠባባቂ ተጫዋቾች ትክክለኛ አሰላለፍ መግለጽ ባንችልም ከስፍራው ባገኘነው አንዳንድ መረጃ መሰረት የሁለቱ ኢትዮጵያውያን ክለቦች ግምታዊ አሰላለፍ የሚከተለውን ይመስላል። 

ደደቢት

ግብ ጠባቂ ካሜሩናዊው አዲሱ ግብ ጠባቂ የመጀመሪያ ተሰላፊ እንደሚሆን ሲጠበቅ ከካሜሩናዊው ግብ ጠባቂ ፊት ያሉትን አራት ቦታዎች ጋናዊው አዳሙ መሃመድ፣ ስዩም ተስፋዬ፣ አምበሉ ብርሃኑ ቦጋለ እና  በአማካይ መስመሩ ላይ ሳምሶን ጥላሁን ሸይቩ ጅብሪል ታደለ መንገሻ መስፍን ኪዳኔ ሲመሩት የፊት መስመሩን ዳዊት ፈቃዱና ሳሙኤል ሳኖሜ እንደሚመሩት ይጠበቃል። 

ፈረሰኞቹ 

ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ የመጀመሪያ ተሰላፊ መሆኑ ሰፊ ግምት የሚሰጠው ግብ ጠባቂ ነው። ተከላካይ መስመሩን ዘካሪያስ ቱጅ ደጉ ደበበ ሳላዲን ባርጌቾና አለማየሁ ሙለታ ይመሩታል። አማካይ መስመሩን አዳነ ግርማ ተስፋዬ አለባቸው ቆቦ አሉላ ግርማ  አጥቂ መሰመሩን ደግሞ ዳዋ ሁጤሳ ኡመድ ኡክሪና ፍጹም ገብረማሪያም ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። 

ኢትዮፉትቦል ዶት ኮም ለሁለቱም ክለቦች መልካም ወጤት ይመኛል። 

ይርጋ አበበ
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!