ታዳጊ ብሔራዊ ቡድናችን የድሬዳዋ ሽንፈቱን ይቀለብሳል?
የካቲት 26, 2007

"አብዛኞቹ ተጫዋቾች የተመረጡት ከጊዮርጊስና ደደቢት ነው። እነዚህ ክለቦች በነበረባቸው ኢንተርናሽናል ጨዋታ ልጆቹን ለረጅም ጊዜ ማግኘት አልተቻለም።"  አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ለኢትዮፉትቦል

የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን በዋናው ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ እየተመራ ለ11ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል። ቡድኑ ለዝግጅት ሰፋ ያለ ጊዜ አላገኘም እየተባለ አስተያየት እየተሰጠ ሲሆን ሜዳ ላይ የታየው ውጤትም አስተያየት ሰጭዎች ትክክል መሆናቸውን ነው። በመጀመሪያ የነጥብ ጨዋታው ከሱዳን አቻው ጋር ተጫውቶ በደጋፊው ፊት ሁለት ለአንድ መሸነፉ ይታወሳል። በዛ ጨዋታ ላይ እንግዳው ቡድን ባለሜዳውን በጎል ብቻ ሳይሆን በጨዋታ እንቅስቃሴም የበላይነቱን ወስዶ መታየቱ አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ቡድናቸውን በሚገባ ለማቀናጀት ሰፊ ጊዜ እንዳላገኙ አመላካች ሆኗል።

የሁለቱ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ ነገ በሱዳን የሚካሄድ ሲሆን የአሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ቡድን ወደ ሱዳን የሚያቀናው አሁንም በቂ ዝግጅት ሳያደርግ ነው እየተባለ ይገኛል። ለዚህ አስተያየት ማጠንከሪያ የሚሆነው ደግሞ የብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ አብላጫ ቁጥር የሚይዙት ተጫዋቾች የተመረጡት ከቅዱስ ጊዮርጊስና ደደቢት ክለቦች ነው። ሁለቱ ክለቦች በአህጉራዊ ውድድር በነበረባቸው ጨዋታ ተጫዋቾቹን የተጠቀሙባቸው ሲሆን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በቂ የዝግጅት ጊዜ አላደረጉም። ልምምድ ካለማድረጋቸውም በላይ ደግሞ እንደ ሳላዲን ባጌቾ ናትናኤል ዘለቀ ዳዋ ሁጤሳና አንዳርጋቸው ይላቅ አይነት የፈረሰኞቹ ኮከቦች በአንድ ሳምንት ሁለት ጨዋታ እንዲያደርጉ ስለሚደረግ ድካም ሊሰማቸው ይችላል። ቅድስ ጊዮርጊስና ደደቢት ከአልጄሪያና ሲሸልስ ክለብ ጋር በሁለት ሳምንት ውስጥ ሁለት ጊዜ የተጫወቱ ሲሆን ወጣት ብሔራዊ ቡድኑም በተመሳሳይ በሁለት ሳምንት ውስጥ ሁለት ጨዋታ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ከሁለቱ ክለቦች የተመረጡ ተጫዋቾችን በሶስት ሳምንት ውስጥ አራት ጨዋታ እንዲያደርጉ የሚያስገድዳቸው ይሆናል። የኢትዮፉትቦል ዘጋቢ አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶን በዚህ ጉዳይ አስተያየታቸውን ጠይቋቸው አብዛኞቹ ተጫዋቾች የተመረጡት ከጊዮርጊስና ደደቢት ነው። እነዚህ ክለቦች በነበረባቸው ኢንተርናሽናል ጨዋታ ልጆቹን ለረጅም ጊዜ ማግኘት እንዳልቻሉ ነበር የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድንና የሱዳን አቻው ድሬዳዋ ላይ ከመጫወታቸው በፊት በሱዳን ለረጅም ጊዜ በመስራት ስለ ሱዳን እግር ኳስ በቂ እውቀት ያለውን አሰልጣኝ ውበቱ አባተን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ስለ ተጋጣሚያችን ቡድን ወቅታዊ አቋምና ዝግጅት ጠይቆት ነበር። በወቅቱ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የመለሰው የሱዳን ብሔራዊ ቡድን ለዚህ ጨዋታ በሚገባ መዘጋጀቱንና የቡድኑ ወቅታዊ አቋምም ከዓመታት በፊት ከምናውቀው የሱዳን ቡድን የተሻለ መሆኑን ነበር። በየደረጃው ያሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች ኢንተርናሽናል ጨዋታ ሲኖራቸው ረዘም ላለ ጊዜ ዝግጅት በማድረግ የሚታወቁ ቢሆንም ሱዳንን የሚገጥመው ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ግን እንደ ቀድሞው ረጅም ጊዜ ሳይዘጋጅ ወደ ውድድር የገባ ቡድን ነው። ቡድኑ ዛሬ ወደ ሱዳን ተጉዞ ነገ ምሽት ጨዋታውን የሚያካሂድ ይሆናል። ድሬዳዋ ላይ እጁን የሰጠው የማሪያኖ ባሬቶ ስብስብ ሱዳን ላይ ውጤት ይዞ ይመለስ ይሆን?


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!