የት ይገኛሉ?
የካቲት 27, 2007

ለክቡራን የኢትዮፉትቦል ዶትኮም አንባቢያን። ከዛሬ የካቲት 27/2007 ዓ.ም ጀምሮ በየሳምንቱ አርብ የት ይገኛሉ? በሚል ርዕስ ስለ ቀድሞ የአገራችን እግር ኳስ ተጫዋቾች ወቅታዊ መረጃ የምናቀርብበት አምድ ማቅረብ እናቀርባለን። በዚህ አምድ ስር የሚቀርቡ ጽሁፎችን ወቅታዊነት ለመጠበቅ የቀድሞዎቹ ተጫዋቾች የሚገኙበትን ቦታና አጠቃላይ መረጃ ብታቀርቡልን ከምስጋና ጋር ተቀብለን የምናስተናግድ መሆኑን እንገልጻለን። ከዛሬ ጀምሮ በተከታታይ ሶስት ሳምንታት የምናቀርበው በ2001 እ.ኤ.አ አርጀንቲና ላይ በ13ኛው የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ከነበረው የወጣት ብሔራዊ ቡድናችን ተጫዋቾች መካከል የተወሰኑትን ይሆናል። 

እንደ አውሮፓውያን የዘመን ስሌት በ2001 ዓ.ም የላቲን አሜሪካዋ ታላቅ የእግር ኳስ አገር አርጀንቲና 13ኛውን የወጣቶች ዓለም ዋንጫ አዘጋጅታ ነበር። በዚያ ውድድር አፍሪካን ወክለው የተገኙት አራት አገሮች አንጎላ፣ ጋና፣ ግብጽና ኢትዮጵያ ነበሩ። ከአራቱ የአህጉሩ ተወካዮች ጋና ለፍጻሜ ቀርባ በአስተናጋጇ አርጀንቲና ተሸንፋ ሁለተኛ ስትወጣ ግብጽ በበኩሏ ሌላኛዋን ላቲን አሜሪካዊት ፓራጓይን በደረጃው አንድ ለባዶ አሸንፋ የነሃስ ሜዳሊያ ይዛ ተመልሳለች። ቀሪዎቹ ቡድኖች ማለትም አንጎላና ኢትዮጵያ ግን ከተሳትፎ የዘለለ ታሪክ ሳይሰሩ ነበር የተመለሱት።

 በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ በዓለም ዋንጫ መድረክ ላይ የተሳተፈው የመጀመሪያ ቡድን የሆነው ያ ቡድን ከያዛቸው ተጫዋቾች መካከል የተወሰኑትን አንስተን የት እንደሚገኙ እንጠቁማለን። በዚህ ሃሳብ ዙሪያ አንባቢያን አስተያየታቸውን ብቻ ሳይሆን የሚያውቁትን መረጃም እንዲሰጡን እንጠይቃለን።

ደያስ አዱኛ

ዝዋይ ተወልዶ ያደገውና በመብራት ኃይል ክለብ ችሎታውን ያጎለበተው ደያስ አዱኛ በዲያጎ ጋርዚያቶ እየተመራ አርጄንቲና ደርሶ ለተመለሰው ቡድን የግቡን ክልል በቋሚነት የጠበቀ ግብ ጠባቂ ነበር። በአርጀንቲናው የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን በቴሌቪዥን ሲያስተላልፉ የነበሩ ኮሜንታተሮች የደያስ አዱኛን ስም ሲጠሩ “ደያስ አዱግና” እያሉ ሲጠሩት የምናስታውሰው የግብ ክልሉ ጀግና ከዓለም ዋንጫው መልስ መብራት ኃይልን ለቆ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫውቶ የፕሪሚየር ሊግና ጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን ደጋግሞ ማንሳት ችሏል።

አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ እያሰለጠነ የምስራቅ አፍሪካ ዋንጫን ሲያነሳ የግቡን ክልል የመራውም ይሄው የዝዋዩ ተወላጅ ግብ ጠባቂ ነበር። ከፈረሰኞቹ ጋር ከተለያየ በኋላ ግን ከአገሩ ጋርም ተለያይቶ ኑሮውን አሜሪካ ካደረገ ቆይቷል። በአሁኑ ሰዓት ምን እየሰራ እንደሆነ ግን ወቅታዊ መረጃ የለንም።

                         ሁሴን ሰማን

የዘር ሃረጉ ከጉራጌ ብሔረሰብ የሚመዘዘውና ባህር ዳር ተወልዶ ያደገው ሁሴን ሰማን ብዙዎች የሚያስታውሱት አርጀንቲና ተጉዞ ከነበረው የአሰልጣኝ ጋርዚያቶ ስብስብ መካከል አርጀንቲና ላይ ጠፍቶ በመቅረቱ ነው። የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና አጥቂ አርጀንቲና ላይ ቀርቶ ለተወሰነ ጊዜ ቢቆይም ወደ አገሩ ተመልሶ ለክለቡ የተወሰኑ ጨዋታዎች ተጫውቶ ነበር። ነገር ግን እግሩ ላይ በደረሰበት ጉዳት የተነሳ እግር ኳስን በጊዜ አቁሞ ወደ ንግድ ስራ ፊቱን ካዞረ ቆይቷል። ሁሴን ሰማን በአሁኑ ሰዓት ባህር ዳር ከተማ ላይ ቡቲክ ከፍቶ እየሰራ መሆኑን ምንጮቻችን ያደረሱን መረጃ አመልክቷል።

በቀለ እልሁ

የአማካይ ተከላካይ መስመር ተጫዋቹ በቀለ እልሁ ለእህል ንግድ ሲጫወት ነበር በዲያጎ ጋርዚያቶ ፊት ሞገስ አግኝቶ አገራዊ አደራ እንዲሰጠው እድል ያገኘው። ከመሃል ሜዳ አክርሮ ወደ ጎል በመሞከር ተለይቶ የሚታወቀው በቀለ እልሁ ለረጅም ደቂቃዎች ያለድካም መጫወትም ሌላው መገለጫዎቹ ነበሩ። አርጀንቲና ተጉዞ በነበረው ቡድን ውስጥም 15 ቁጥር ማሊያ ለብሶ በሶስቱም የብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታዎች ላይ ሙሉ ጨዋታዎችን የተጫወተ ሲሆን በተሰለፈባቸው ሶስቱም ጨዋታዎች ያሳየው ብቃት በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የማይዘነጋ ነው።
Bekele Elhu

ከእህል ንግድ ወደ መብራት ኃይል በከፍተኛ የፊርማ ገንዘብ ተዘዋውሮ ከኮረንቲዎቹ ጋር ስኬታማ ጊዜያትን ማሳለፍ ችሏል። ከመብራት ኃይል ከለቀቀ በኋላም በአንድ ወቅት “የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቀጣይ ዘመን መገለጫ” ይባል ለነበረው ኒያላ ፈርሞ ተጫውቷል። በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ደግሞ ከአርጀንቲናው ወጣቶች የዓለም ዋንጫ ጀምሮ የሴካፋን ዋንጫ ሩዋንዳ ላይ ከአስራት ሀይሌ ጋር ማንሳት ችሏል።
ይህንን ሁሉu ገድልና ውለታ የዋለው በቀለ እልሁ በአሁኑ ወቅት ህይወቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መሆኑን የፕላኔት ስፖርት የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ምስጋናው ታደሰ በቅርቡ መረጃውን ለህዝብ ገልጾ ነበር። በወቅቱ የጋዜጠኛ ምስጋናውን መረጃ ያነበቡና ያዳመጡ በርካታ አንባቢያን የቀድሞውን የብሔራዊ ቡድን አማካይ ለመርዳትና ያለበትን ለማወቅ ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል። ሌሎች ደግሞ በቀለን ለመርዳትና ወደ ቀድሞ ህይወቱ እንዲመለስ ለማስቻል ተጨማሪ መረጃ ማግኘት የሚፈልጉ ወገኖች ባቀረቡልን ጥያቄ መሰረት ኢትዮፉትቦል ዶትኮም ይህንን መረጃ አቅርቧል። በቀለ እልሁ በአሁኑ ወቅት በኬኒያና ኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ በምትገኘው ሞያሌ ከተማ እየኖረ ሲሆን ለሃገሩና ለቀድሞ ክለቦቹ ሲጫወት ደርሶበት የነበረው የጀርባ ጉዳት እንደገና አገርሽቶበት በከፍተኛ የህመም ስቃይ ላይ ይገኛል።

በቀጣይም የቀድመውን የአገራችንን ባለውለታ በስልክ አግኝተን ተጨማሪ መረጃዎችን ይዘን እንመለሳለን። ዛሬ ይህንን መረጃ እንድናቀርብ መረጃውን በማቀበል የተባበረንን የሃትሪክ ጋዜጣና ቤስት ስፖርት መጽሄት እንዲሁም የፕላኔት ስፖርት የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ጋዜጠኛ ምስጋናው ታደሰን በአንባቢያን ስም እናመሰግናለን።

በቀለ እልሁን ለመርዳትና በግል ለማግኘት የምትፈልጉ አንባቢያን በኢትዮፉትቦል ዶትኮም አድራሻ info@ethiofootball.com ወይም ጋዜጠኛ ምስጋናው ታደሰን misganaw2000@yahoo.com በኢሜይል በማግኘት የተጫዋቹን ስልክ ልታገኙና የምትችሉትን በቀጥታ ልትረዱት ትችላላችሁ።

ይቀጥላል!!

ካሳ ሀይሉ
ለኢትዮ ፉትቦል
ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
መሀመድ ይማም [743 days ago.]
 አድናቂ

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!