ኤሌክትሪክ በሁለተኛው ዙር ሳይቆራረጥ ይቀጥላል
የካቲት 30, 2007

“ኤሌክትሪክ በሁለተኛው ዙር ሳይቆራረጥ ይቀጥላል”
 አጥናፉ ዓለሙ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር መርሃ ግብር ከረጅም የእረፍት ጊዜ በኋላ የፊታችን አርብ እንደሚጀመር ከፌዴሬሽኑ የደረሰን መረጃ አመለከተ። የፊታችን ዓርብ ፕሪሚየር ሊጉ ሲጀመር የአሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ ቡድን ኤሌክትሪክ ከገብረመድህን ሀይሌው መከላከያ ጋር ይጫወታሉ። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር የመክፈቻ ጨዋታቸውን በአዲስ አበባ ስታዲየም አካሂደው አዝናኝ ጨዋታ ቢያሳዩም ያለ ግብ ባዶ ለባዶ ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።
ELPA

የ2007 ዓ.ም ፕሪሚየር ሊጉ ሲጀመር በተከታታይ ሰባት ጨዋታዎችን ያለሽንፈት ተጉዞ በቀሪዎቹ አራት ተከታታይ ጨዋታዎች የሽንፈት ጽዋን ለመጎንጨት የተገደደው ኤሌክትሪክ ክለብ ከሽንፈት ሀንጎቨሩ መወጣት የቻለው ከወላይታ ድቻ ጋር አንድ እኩል በተለያየበት ጨዋታ ነበር። ከድቻ ጋር እኩል ተለያይቶ ከአራት ጨዋታ በኋላ አንድ ነጥብ ወደ ኮሮጆው ማስገባት የቻለው ኤሌክትሪክ በፕሪሚየር ሊጉ ተስተካካይ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን አንድ ለባዶ አሸንፎ ሙሉ ሶስት ነጥብ በመያዝ ነበር የመጀመሪያውን ዙር ያጠናቀቀው።

ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ መክፈቻ የመጀመሪያ ሰባት ሳምንታት ያለሽንፈት ተጉዞ በኋላ መንሸራተት ያሳየ ሲሆን ይህ ባህሉ በሁለተኛው ዙር አይደገምም ወይ? የሚል ጥያቄ ለአሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ አቅርበንላቸው ነበር። “ክለባችን በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት የነበረውን ወጥ አቋም ይዞ መቀጠል ያልቻለው በአንዳንድ ስህተቶች ነበር” ያሉት አቶ አጥናፉ “በተለይ የአጥቂ መስመራችን የነበረበት ክፍተት ዋጋ አስከፍሎን ነበር። አሁን ግን ጉዳት ላይ የነበረው ማናዬ ፋንቱ ከጉዳቱ ሙሉ በሙሉ አገግሞ ወደ ጨዋታ ከመግባቱም በላይ ከወጣት ቡድናችን ያሳደግናቸው ወጣት አጥቂዎችም ለቡድናችን ጥንካሬ ወሳኝ ይሆኑልናል። በእርግጠኝነት ክለባችን በሁለተኛው ዙር ወጥ አቋም ይዞ ይቀጥላል” ሲሉ ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም ተናግረዋል።

ፕሪሚየር ሊጉን የደቡብ ኢትዮጵያው ሲዳማ ቡና እየመራ ሲሆን ሲዳማ ቡና በ13 ጨዋታ የሰበሰበው ነጥብ 27 ነው። ይህም በያንዳንዱ ጨዋታ ሁለት ነጥብ ዜሮ ሰባት ነጥቦችን ማስመዝገብ ችሏል ማለት ነው። ከሲዳማ ቡና ቀጥሎ ያለውን ደረጃ ደግሞ በየጨዋታው አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሁለት ነጥቦችን ማስመዝገብ የቻሉት ፈረሰኞቹ ይዘውታል። ወላይታ ድቻና ኢትዮጵያ ቡና ሶስተኛና አራተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ወልድያ ከነማ በአምስት ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሁለት አሰልጣኞችን አሰናብቶ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ቡና እና አልሃሊ ሻንዲ አሰልጣኝ ውበቱ አባተን በቅርቡ የቀጠረው ሃዋሳ ከነማ 12ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ የፊታችን ቅዳሜ ወደ አርባምንጭ ተጉዞ በደቡብ ደርቢ ከአርባ ምንጭ ከነማ ጋር በመጫወት ሁለተኛውን ዙር ይጀምራል።

የኢትዮጵያ ቡናው ቢኒያም አሰፋ በመጀመሪያው ዙር 11 ጨዋታዎችን ብቻ ተጫውቶ 10 ጎሎችን አስቆጥሮ ከፍተኛ ጎል አግቢነቱን ሲመራ የደደቢቱ ናይጄሪያዊ አጥቂ ሳሙኤል ሳኖሜ ደግሞ ከቢኒያም በሶስት ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በዚህ ዓመት ከብሔራዊ ሊጉ ወራቤ ከነማ ወላይታ ድቻን የተቀላቀለው ባዬ ገዛኸኝ በስድስት ጎል ሶስተኛ ደረጃ ሆኖ ይከተላል።

የኢትዮጵያ ፐሪሚየር ሊግ በአዲስ መልክ መካሄድ ከጀመረበት 1990 ዓ.ም ጀምሮ ዘንድሮ ለ18ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ፈረሰኞቹ 11 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ቀዳሚ ናቸው። ኤሌክትሪክ ክለብና ሃዋሳ ከነማ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ጊዜ ዋንጫውን አንስተዋል። የበርካታ ደጋፊ ባለቤት የሆነው ኢትዮጵያ ቡና አንድ ጊዜ ብቻ ዋንጫውን ሲያነሳ ከተመሰረተ 20 ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረውና በፕሪሚየር ሊጉ ሲሳተፍ ዘንድሮ አምስተኛ ዓመቱን የያዘው ደደቢት አንድ ጊዜ የዋንጫው ባለቤት መሆን ችሏል።

ካሳ ሀይሉ
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!