ሉሲዎቹ በሜዳቸው በመሸነፋቸው ወደ መላ አፍሪካ ጨዋታዎች የሚያደርጉትን ጉዞ አበላሹ
መጋቢት 13, 2007

ምዕራብ አፍሪካዊቷ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የፊታችን መስከረም አጋማሽ 11ኛውን የመላ አፍሪካ ጨዋታ ታስተናግዳለች። በዚያ ውድድር ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሉሲዎቹ ከካሜሩን አቻቸው ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ትናንት የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አድርገው ሁለት ለአንድ ተሸንፈዋል። የእንግዳው ቡድን የመሃል ሜዳ የበላይነትና የጎል ሙከራ ብልጫ በታየበት የሁለቱ ቡደኖች ጨዋታ ሉሲዎቹ ጨዋታው በተጀመረ በ16ኛው ደቂቃ የደደቢቷ ሎዛ አብርሃም ባስቆጠረቻት ጎል መምራት ችለው ነበር። ሎዛ አበራ ላስቆጠረቻት ጎል የካሜሩኗ ተከላካይ ስህተት ጉልህ ድርሻ ቢኖረውም የሎዛ ጎል አጨራረስ ግን የተጫዋቿን ልምድ ያሳየ ሆኗል። 

Ethiopian Women National Team Vs Camerron

ከጎሏ መቆጠር በፊትም ሆነ በኋላ በደንብ ተደራጅተው መጫዎት ያልቻሉት ሉሲዎቹ በራሳቸው የግብ ክልል አቅራቢያ በተጋጣሚያቸው ተጫዋቾች ላይ የሀይል አጨዋወት ሲተገብሩ ታይተዋል። ጨዋታውን የመሩት ግብጻዊዋ ዳኛም የሉሲዎቹን ተደጋጋሚ የሀይል አጨዋወት በቸልታ ባለማለፋቸው የቅጣት ምት ለካሜሩን ብሔራዊ ቡድን ለመስጠት ተገድደዋል። በተለይ በስድስተኛው ደቂቃ ካሜሩኖች ከቅጣት ምት አክርረው የመቷት ኳስ ለሉሲዎቹ ግብ ጠባቂ ዳግማዊት መኮንን ፈታኝ ነበረች። 

ሉሲዎቹ ገና በ16ኛው ደቂቃ ጎል ያስቆጠሩ ቢሆንም ተጨማሪ ጎሎችን ለማስቆጠር ከመጫወት ይልቅ ቀሪዎቹን 75 እና ከዚያ በላይ ደቂቃዎች ውጤት ለማስጠበቅ ሲሞክሩ ታይተዋል። ይህ ድርጊታቸውም በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ዋጋ ሊያስከፍላቸው ችሏል። ከጨዋታው አንድ ቀን ቀደም ብሎ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በሀይሏ ዘለቀ ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም “ካሜሩኖች በአየር ላይ እና ረጅም ኳስ የሚጫወቱ በመሆናቸው እኛ ኳስ ተቆጣጥረን በመጫዎት ለማሸነፍ እንጫወታለን” ሲሉ ተናግረው ነበር። ሆኖም ጨዋታው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ብሔራዊ ቡድናችን ኳስ ተቆጣጥሮ ከመጫወት ይልቅ ለእንግዳው ቡድን ተስማሚ የሆነውን የአየር ላይ ኳስ በረጅም መቀባበልን በመምረጡ በቀላሉ የመሃል ሜዳ የበላይነቱን ሊቀማ ችሏል።  
Ethiopian Women National Team Vs Camerron

በካሜሩን ብሔራዊ ቡድን በኩል ሰባት ቁጥር ማሊያ ለባሿ ጋብርኤሏ ምጉየኒ ለሉሲዎቹ ተከላካዮች ፈተና ሆና ያመሸች ሲሆን እሷን በቀላሉ ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች ሲንቀሳቀሱ አለመታየታቸው አነጋጋሪ ሆኗል። በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የመሃል ሜዳ የበላይነትና የኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ የተወሰደበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋች ለውጥ ወይም የአጨዋወት ለውጥ አድርጎ ይገባል ተብሎ ቢጠበቅም በመጀመሪያው አሰላለፉና አጨዋወቱ በመግባቱ በሁለተኛው አጋማሽም በካሜሩን አቻው የበላይነት እንደተወሰደበት ጨዋታውን ሊያጠናቅቅ ተገድዷል።
 በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የካሜሩኗ ጋብርኤሏ ንጉየሚ ለሁለቱም የመስመር ተከላካዮች ፈታኝ እንቅስቃሴ ስታደርግ የታየች ሲሆን ይህ ጥረቷ ተሳክቶላትም በ83ኛው ደቂቃ ጥሩአንቺ መንገሻን አታላ በማለፍ ክሮስ ያረገችውን ኳስ ተቀይራ የገባችው 12 ቁጥሯ አጥቂ ለእንግዳው ቡድን የመጀመሪያ ጎል ልታስቆጥር ችላለች። ከግቧ መቆጠር በኋላ ይበልጥ የተደናገጡት የሉሲዎቹ ተከላካዮች በራሳቸው የግብ ክልል በሰሩት ጥፋት የተሰጠውን ቅጣት ምት አሁንም ጋብርኤሏ ስታሻማ ዘጠኝ ቁጥሯ ቡድኗን አሸናፊ ያደረገች ጎል በግንባሯ ገጭታ አስቆጥራለች። 

Ethiopian Women National Team Vs Camerron


የሉሲዎቹ ጠንካራ ጎን

ሉሲዎቹ ሙሉውን 90 ደቂቃና ተጨማሪውን ሰዓት ጨምሮ በተጋጣሚያቸው የኳስ ቁጥጥርም ሆነ የጎል ሙከራ የተበለጡ መሆኑ ግልጽ ነው። በተለይ የተከላካይ መስመሩና አማካይ መሰመሩ በቀላሉ እጁን የሚሰጥ ሆኖ የታየ ሲሆን አጥቂው ክፍልም ቢሆን ይህን ያህል አመርቂ እንቅስቃሴ አሳይቷል ማለት አይቻልም። ነገር ግን ከሉሲዎቹ የትናንቱ ጨዋታ አንድ ጥንካሬ ታይቷል ይሄውም ከቋሚ ተሰላፊዎቹ መካከል አምስቱ ቡድኑን የተቀላቀሉት በዚህ ዓመት ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ኢንተርናሽናል ጨዋታ ያደረጉት አምስቱ የሉሲዎቹ አባላት ያሳዩት እንቅስቃሴ ተስፋ የሚያስቆርጥ አልሆነም። ፦

ከዚህም በላይ ቡድኑ ኢንተርናሽናል ጨዋታም ሆነ የወዳጅነት ግጥሚያ ካደረገ አንድ ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን ለትናንቱ ጨዋታም የተዘጋጀው 25 ቀናትን ብቻ ነው። በ25 ቀናት ዝግጅት ብቻ ወደ ጨዋታ የገባው የአሰልጣኝ በሀይሏ ዘለቀ ቡድን የተሰባሰበው ከ12 ክለቦች ነው። ይህ ማለት ደግሞ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ በሁለት ዞን ማዕከላዊ ሰሜን ዞንና ደቡብ ዞን ተብሎ የተከፈለ በመሆኑ ብሔራዊ ቡድኑን የተቀላቀሉት ተጫዋቾች አብዛኞቹ በስም እንኳ የማይተዋወቁ ነበረ ማለት ነው። በስም እንኳ የማይተዋወቁና ለረጅም ጊዜ አብረው ዝግጅት ያላደረጉ ተጫዋቾችን በ25 ቀን ዝግጅት ብቻ ይዞ ለውድድር መቀረብ ለዚያውም የአፍሪካ ቻምፒዮን የሆነውን የካሜሩንን ብሔራዊ ቡድን መግጠም የአሰልጣኞቹንም ሆነ የተጫዋቾቹን ጥንካሬ ያሳየ ነው ማለት ይቻላል። 

ከጨዋታው በፊት ከኢትዮፉትቦል ዶትኮም ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገው የነበሩት የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በሀይሏ ዘለቀ “ይህ ቡድን በካሜሩን አቻው ቢሸነፍና ከመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ውጭ ቢሆን እጣ ፈንታው ምን ይሆናል?” ተብለው ተጠይቀው “ቡድኑ እየተዘጋጀ ያለው ለኮንጎው ውድድር ብቻ አይደለም። በድኑ የተዋቀረው ከ60 ፐርሰንት በላይ በአዳዲስ ተጫዋቾች ነው። እነዚህ ተጫዋቾች ደግሞ በአጭር ጊዜ ዝግጅት የሚጠበቀውን ውጤት ያመጣሉ ተብሎ አይታሰብም። ስለዚህ እየተዘጋጀን ያለነው በቀጣዮቹ ረጅም ጊዜያት ጠንካራ የሆነ ቡድን በመገንባት ላይ ነው” ሲሉ የቡድኑ ጉዞ ለአንድ ግዳጅ ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ ተናግረው ነበር። አሰልጣኝ በሀይሏ በቡድናቸው ከያዟቸው 25 ተጫዋቾች መካከል 15 ያህሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔራዊ ቡድኑን የተቀላቀሉ መሆናቸው ተገልጿል። የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን ደግሞ በቀጣዩ ሰኔ በካናዳ ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ አፍሪካን ወክሎ የሚካፈል ሲሆን ያለፈው ዓመት የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን ነው። 

 የቡድኑ ደካማ ጎን

በትናንቱ ጨዋታ በግልጽ እንደታየውም ሆነ ከላይ እንደገለጽኩት ብሔራዊ ቡድኑ በመሃል ሜዳ የኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመቅረብ በእንግዳው ቡድን ተበልጦ ታይቷል። ከዚህ በተጨማሪም የታክቲካል ዲስፕሊን ችግር በተጫዋቾቹ ላይ ታይቷል። ለዚህ ነጥብ ማጠንከሪያ የሚሆነው ደግሞ ግብ ጠባቂዋን ዳግማዊት መኮንንን ጨምሮ መላ የቡድኑ አባላት ተጨማሪ ጎል ለማግባት ከመንቀሳቀስ ይልቅ የአንድ ለባዶ መሪነታቸውን አስጠብቆ ለመውጣት ያደረጉት ጥረት የማይደገፍ ነው። አንድ ቡድን ነጥብ አስጠብቆ መውጣት የሚችለው ለ75 እና ከዚያ በላይ ደቂቃ ተፋልሞ ሳይሆን በጨዋታው መጠናቀቂያ አካባቢ መሆን ሲገባው ሉሲዎቹ ግን ሙሉውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በዚህ ስራ ተጠምደው አምሽተዋል። 

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የቡድኑ ትልቅ ድክመት ሆኖ የታየው ያለውን ጥሎ የሌለውን ሲፈልግ መታየቱ ነው። ሃሳቡን ለማብራራት ያህል ቡድኑ በተደራጀና አጭር የኳስ ቅብብል ላይ ጠንካራ በመሆኑ ተጋጣሚውን በኳስ ቁጥጥር መብለጥ ሲገባው ከተጋጣሚው ያነሰ የአካል ብቃትና ፍጥነት እንዳለው እየታወቀ የራሱን ቀሚስ አውልቆ በተጋጣሚው ቀሚስ ልክ እገባለሁ ማለቱ ነው። ይህ ደግሞ ሉሲዎቹ ከ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ እስከ ሶስተኛው የቻን ዋንጫ ድረስ የነበረውን የዋሊያዎቹን ድክመት የደገመ ሆኖ ታይቷል። ዋሊያዎቹም እንደ ናይጀሪያና ሊቢያ አይነት ቡድኖችን በኳስ ቁጥጥር መብለጥ ሲገባቸው በሀይል አጨዋወት ለመጫወት መሞከራቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው ይታወሳል። 

በአጠቃላይ ግን አዲሱ የሉሲዎች ስብስብ ወደፊት ሰፊ የጨዋታ እድልና ልምድ እያገኙ ሲሄዱ ይበልጥ እየበሰሉና እየተቀናጁ የሚሄዱ ልጆች ናቸው። የሉሲዎቹ ተጋጣሚ የነበሩት ካሜሩኖች ከሉሲዎቹ ተሽለው የታዩት የ2010 የአፍሪካ ኮከብ አሰልጣኝ ስለሚያሰለጥናቸው ወይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደካማ ስለሆነ ሳይሆን ካሜሩን ውስጥ ከ17 ዓመት በታች ጀምሮ እስከ ዋናው ብሔራዊ ቡድን ድረስ ሶስት ቡድን ያለው በመሆኑ ቡድኑን ቶሎ ቶሎ በተተኪዎች ስለሚገነባ ነው። ሉሲዎቹም ወደፊት ከስር ከስር በተተኪዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩ ከሆነ ቡድኑ በተፈጥሯቸው በቴክኒክ ጠንካራ የሆኑ ተጫዋቾችን ስለያዘ ነገ ትልቅ ደረጃ መድረስ ይችላል ባይ ነን። 

ካሳ ሀይሉ 
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!