ውበቱ አባተ የሃዋሳ ከነማ መልኅቅ ይሆናል?
መጋቢት 15, 2007

ሃዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ከአዲስ አበባ ውጭ የሚገኝ ክለብ ሲያነሳ የመጀመሪያው እስካሁንም የመጨረሻው ክለብ ነው። በውጤታማው አሰልጣኝ ከማል አህመድ ወይም በደዌ እየተመራ ለሁለት ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት የቻለው ሃዋሳ ከነማ ከሻምፒዮንነቱ በተጓዳኝ ክለቡን በመልካም ስም የሚያስጠራው ቡድኑን በወጣቶችና ታዳጊዎች በመገንባት ተፎካካሪ የሚሆንበት ተሞክሮው ነው። ነገር ግን ውጤታማውና የበርካታ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች መፍለቂያ የሆነው ሃዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ በዚህ ዓመት ውጤት ፊቱን አዙሮበት የወራጅ ቀጠናው አድማቂ ለመሆን ተገዷል።
 
ሊጉ ከመጀመሩ በፊት ከአስር ሚሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ ለተጫዋች ዝውውር ወጭ ያደረገው ክለብ በ13 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሁለቱን ብቻ አሸንፎ አስር ነጥብ ብቻ በመያዝ ከግርጌው አድማቂ ወልድያ ከነማ ቀጥሎ 13ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ተገድዶ ነበር። የመጀመሪያው ዙር ከመጠናቀቁ ሶስት ሳምንታት ቀደም ብሎ አሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ ወይም ዳኘን ለውጤቱ ማጣት ምክንያት ነህ ብሎ በማሰናበት በምትኩ ሌላ አሰልጣኝ ቀጥሮ ነበር። ዳኘን ተክተው ቦታውን የተረከቡት አሰልጣኝም ቢሆኑ አንድ ጨዋታ ብቻ አሸንፈው በተከታታይ በመሸነፋቸው ቦታውን ለውበቱ አባተ 

ለማስረከብ ተገደዱ። 

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የተለያዩ ክለቦችን በማሰልጠን ትልቅ ስም ያተረፈ አሰልጣኝ ቢሆንም በበርካታ የስፖርቱ ቤተሰብ ይበልጥ እንዲታወቅ ያደረገው ግን በ2003 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ካነሳ በኋላ ነው። ቡናማዎቹ በፕሪሚየር ሊጉ አንድ ዋንጫ ብቻ ያነሱ ሲሆን ይህንን ዋንጫም ያገኙት በናዝሬቱ ተወላጅ ውበቱ አባተ መሆኑ አሰልጣኙን የክለቡ ደጋፊዎች በታላቅ ክብርና ፍቅር ያወድሱታል። ዋንጫውን ባነሱበት ዓመትም የቤት መኪና መሸለማቸው ለአሰልጣኙ ያላቸውን ክብር ያሳያል። አቶ ውበቱ ከቡና ጋር ከተለያየ በኋላ ብዙም ስኬታማ ጊዜን ባያሳልፍም ወደ ሱዳን በመሄድ ከሱዳኑ አልሃሊ ሻንዲ ጋር ለ22 ወራት ስኬታማ ጊዜን በማሳለፍ ወደ አገሩ የተመለሰው በቅርቡ ነው። ሃዋሳ ከነማም ይህንን ውጤታማ አሰልጣኝ ነው ከድቀት እንዲታደገው የቀጠረው። 

ሃዋሳ ከነማ በዘመነ ውበቱ አባተ

ማራኪ ጨዋታ የሚጫወት ክለብ በመገንባት ከሚታወቁት የአገራችን አሰልጣኞች መካከል አንዱ የሆነው ውበቱ አባተ ወደ ሃዋሳ ከነማ ሲያቀና ክለቡ በመስጠም ላይ ያለ ጀልባ ነበር። በመስጠም ላይ ያለ ጀልባን ለመታደግ ራሱን መልኅቅ አድርጎ የሚያስብ አሰልጣኝ ይኖራል ተብሎ ባይታሰብም ውበቱ ግን በድፍረት የክለቡን ሀላፊነት ተረክቦ ወደ ሃዋሳ አመራ። አሰልጣኝ ውበቱ አባተን በስልክም ሆነ በአካል አግኝተን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት በተለያዩ ምክንያቶች ባይሳካልንም ለአሰልጣኙና ለክለቡ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደነገሩን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ሃዋሳ ከነማን የተረከበው ከወራጅነት መታደግ እችላለሁ በልበ ሙሉነት ነው። 

አሰልጣኙ ከአዲሱ ክለቡ ጋር ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ያደረገ በመሆኑ በቀሪዎቹ 11 ጨዋታዎች የሚገጥመውን ማወቅ ባይቻልም በሁለቱ ጨዋታዎቹ በተከታታይ ማሸነፉ ግን ክለቡን ከወራጅ ቀጠና በአንድ ጊዜ  አውጥቶ 11ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አስችሎታል። አስር ነጥብና ስድስት የጎል እዳ ተሸክሞ የነበረው ሃዋሳ ከነማ አሁን 16 ነጥብና የጎል እዳውንም ከስድስት ወደ ሁለት ዝቅ ማድረግ ችሏል። ክለቡ በተታታይ  ሁለት ጨዋታዎችን ማሸነፉ እንደ ትልቅ ውጤት መታየት ባይኖርበትም ያሸነፋቸውን ቡድኖች ደረጃና የቡድን ጥልቀት ስንመለከት ግን የሃዋሳ ከነማን ድል ትልቅ ነጥብ እንድንሰጠው ያስገድዳል። ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ በደቡብ ደርቢ ከሜዳው ውጭ ከአርባምንጭ ከነማ ጋር ተጫውቶ ሁለት ለባዶ ሲያሸንፍ በሁለተኛው ሳምንት ደግሞ ያለፈው ዓመት ቻምፒዮኑን ቅዱስ ጊዮርጊስን ሁለት ለባዶ አሸንፏል። 

ሃዋሳ ያሸነፋቸው ሁለቱ ክለቦች ማለትም አርባምንጭ ከነማ በቀጣዩ ጨዋታ ወላይታ ድቻን ከሜዳው ውጭ አንድ ለባዶ ሲያሸንፍ ፈረሰኞቹ በበኩቸው ሃዋሳን ከመግጠማቸው በፊት በሜዳቸው አዳማ ከነማን ሁለት ለባዶ አሸንፈው ነበር ሃዋሳን ያገኙት። ይህ የሚያሳየው ደግሞ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከአዲሱ ክለቡ ጋር ያደረጋቸው ሁለት የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ያሸነፈው አሸናፊዎችን ነው ማለት ነው። ሃዋሳ ከነማ መጋቢት 25 ከሜዳው ውጭ የጥሎ ማለፍ አሸናፊውን ደደቢትን በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚገጥም ይሆናል። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ግንኙነታቸው ሃዋሳ ላይ ደደቢት ሁለት ለአንድ ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን በጥሎ ማለፉ ደግሞ ሃዋሳ ከነማ አበበ ቢቂላ ላይ አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉ ይታወሳል። 

በሌሎች የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ባለፈው ሳምንት በሃዋሳ ከነማ የተሸነፈውና አሰልጣኙን ያሰናበተው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው ከሌላው የደቡብ ክለብ ወላይታ ድቻ ጋር ማክሰኞ ከአመሻሹ 11፡30 ላይ ይጫወታል። በመጀመሪያው ዙር ቦዲቲ ላይ ያለ ግብ አቻ የተለያዩት ሁለቱ ክለቦች በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛና ሶስተኛ ላይ የተቀመጡ ሲሆን ጨዋታውን ተጠባቂ ያደርገዋል።  ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ተደጋጋሚ ሽንፈት እያስተናገዱ ጫና ላይ የሚገኙት አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻና አጥናፉ ዓለሙ የሚገናኙበት የኤሌክትሪክና የቡና ጨዋታ ይካሄዳል። ኢትዮጵያ ቡና ባለፈው ሃሙስ ሙገር ሲሚንቶን ሶስት ለአንድ አሸንፎ ከውጥረቱ በመጠኑም ቢሆን አሰልጣኙ እፎይ ያሉ ቢሆንም ከኤሌክትሪክ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ግን ተጠባቂ ነው። 

ሳምንት እሁድ አርባምንጭ ከነማ ከመከላከያ ሲጫወቱ ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራ የፕሪሚየር ሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን ያስተናግዳል። በሊጉ 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሙገር ሲሚንቶ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ያስተናግዳል። 

ካሳ ሀይሉ
ኢትዮ ፉትቦል


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!