ፈረሰኞቹ የሊጉን መሪነት እንደገና ተረከቡ
መጋቢት 16, 2007

ብራዚላዊውን አሰልጣኝ ዶሳንቶስን ያሰናበቱት ፈረሰኞቹ በምክትል አሰልጣኞቹ እየተመሩ ጠንካራውን ወላይታ ድቻ በማሸነፍ  በጎል ክፍያ የሊጉን መሪነት መያዝ ቻሉ። ትናንት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የተካሄደውን የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በምንያህል ተሾመ፣ ምንተስኖት አዳነ እና አዳነ ግርማ ጎሎች ሶስት ለአንድ በማሸነፍ የሊጉን መሪነት መቆጣጠጥ ሲችል ለወላይታ ድቻ በባዶ ከመሸነፍ የታደገችዋን ብቸኛ የማጽናኛ ጎል ያስቆጠረው ጎል አዳኙ ባዬ ገዛኸኝ ነው። ባዬ ገዛኸኝ የትናንቱን ጨምሮ በአጠቃላይ በውድድር ዓመቱ ሰባት ጎሎችን በማስቆጠር የከፍተኛ ጎል አግቢዎችን ምድብ መቀላቀል ችሏል። 

ፈረሰኞቹ በዚህ ዓመት ካደረጓቸው 16 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች 31 ነጥብ መሰብሰብ የቻሉ ሲሆን 12 ተጨማሪ የጎል ክፍያም ይዘዋል። የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ 11 ጊዜ በማንሳት ቀዳሚ የሆኑት ፈረሰኞቹ በዚህ ዓመትም የሊጉን ዋንጫ ያነሳሉ ተብለው ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ክለቦች አንዱ ቢሆንም እያሳዩ ያለው አቋም ግን ደጋፊዎቻቸውን ያስደሰተ አልሆነም። 

St.George Supporters

በክለቡ ወቅታዊ የሜዳ ላይ አቋም ያልተደሰቱት ደጋፊዎች በቅርቡ በተሰናበቱት ብራዚላዊ አሰልጣኝ ላይ ቁጣቸውን ማሰማታቸው የሚታወስ ነው። የክለቡ የቦርድ አመራርም የደጋፊዎቹን ጩኸት በመስማት ለቡድኑ ውጤት የተጠበቀውን ያህል አለመሆን ምክንያት ናቸው ያላቸውን አሰልጣኝ በቅርቡ አሰናብቷል። እስካሁን ድረስ በምትካቸው ሌላ አሰልጣኝ ያልቀጠረ ቢሆንም በተጠባባቂ አሰልጣኞቹ እየተመራ ጠንካራውን ወላይታ ድቻን ማሸነፉ ደጋፊዎቹን በመጠኑም ቢሆን ያስደሰተ ውጤት ሆኗል። 

ፕሪሚየር ሊጉ ዛሬም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ 9፡30 ላይ በተከታታይ ሽንፈት እያስተናገዱ ያሉት ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክና ኢትዮጵያ ቡና ይጫወታሉ። ኤሌክትሪክ ከያዘው የቡድን ስብስብና ከአሰልጣኝ ብቃት አኳያ ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ከሰባተኛው ሳምንት በኋላ እያሳየ ያለው ወጥ ያልሆነ አቋም አሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙን እያስተቻቸው ይገኛል። የበርካታ ደጋፊ ባለቤት የሆነው ኢትዮጵያ ቡናም ቢሆን በሲቲ ካፑ ያሳየውን አቋም የተመለከቱ የስፖርት ቤተሰቡና የክለቡ ደጋፊዎች ቡድኑን ለሊጉ ዋንጫ ቢያጩትም ሜዳ ላይ እያስመዘገበ ያለው አቋም ግን የተጠበቀውን ያህል መሆን አልቻለም። በውጥረት ውስጥ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ ከተሸናነፉ ለተሸናፊው ቡድን አሰልጣኝ የስራ ጫና እንደሚበዛበት ግልጽ ሲሆን ለዚህም ሁለቱም ቡድኖች ጠንካራ ፍልሚያ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። 

ትናንትና ዛሬ የተካሄዱት ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚካሄዱ ቀደም ብሎ ፕሮግራም ተይዞላቸው የነበረ ቢሆንም ፌዴሬሽኑ ወደ አበበ ቢቂላ እንዲዛወሩ አድርጓል። ለተጫዋቾችና ለደጋፊ አመች ባልሆነው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታዎች መካሄዳቸው የሊጉን ድምቀት እንዳያደበዝዘው ተሰግቷል። 

ፕሪሚየር ሊጉን ፈረሰኞቹ በ31 ነጥብና 12 ተጨማሪ የጎል ክፍያ ሲመሩት አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሲዳማ ቡና በተመሳሳይ ነጥብና በጎል ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ሆኖ ይከተላል። ትናንት በቅዱስ ጊዮርጊስ የተሸነፈው ወላይታ ድቻ ሶስተኛ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና አራተኛ ነው። ከቡድናቸው የሊጉን መሪነት ያጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በአጥቂያቸው ቢኒያም አሰፋ የሊጉን ኮከብ ጎል አግቢነት ደረጃ ይመራሉ በ12 ጎሎች። 

ካሳ ሀይሉ 
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!