አስቻለው ግርማ በአዲሱ አምብሮ ጫማው ጎል ባስቆጠረበት ጨዋታ ቡና ደረጃውን አሻሻለ
መጋቢት 17, 2007

ታዋቂው የስፖርት ጫማ አምራች ካምፓኒ አምብሮ ምርቱን በኢትዮጵያ በስፋት ለማስተዋወቅ ሁለት ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን መምረጡ ይታወሳል። በአምብሮ ከተመረጡት ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ቡናው የመስመር አጥቂ አስቻለው ግርማ ትናንት ክለቡ ኤሌክትሪክን ሁለት ለአንድ ሲያሸንፍ በአዲሱ ጫማው ጎል አስቆጥሯል። 
Aschalew Girma

ትናንት በተካሄደው የፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ጨዋታ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘገበ ሲሆን ጎሎቹን ያስቆጠሩት አጥቂዎቹ አስቻለው ግርማና ቢኒያም አሰፋ ናቸው። በራምኬል ሎክ ጎል መምራት ችለው የነበሩት የአሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ ልጆች ከእረፍት መልስ አስቻለው ግርማ ባስቆጠረባቸው ጎል አቻ መሆን ሲችሉ በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ደግሞ የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ጎል አግቢነት እየመራ ያለው ቢኒያም አሰፋ ኤሌክትሪክን አሳዛኝ ሽንፈት እንዲጎነጭ አድርጎታል። ድሉን ተከትሎም ቡና ከመሪዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስና ሲዳማ ቡና በአራት ነጥብ ዝቅ ብሎ ከተከታዩ ወላይታ ድቻ ደግሞ በሁለት ነጥብ ላቅ ብሎ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 
Binyam Asfew After Scoring Goal

ትናንት በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ጎል ያስቆጠረው ቢኒያም አሰፋ ባለቀ ሰዓት ጎል በማስቆጠር ቡድኑን ሲታደግ የትናንቱ ለሁለተኛ ጊዜ ሆኗል። ከዚህ በፊት አዳማ ላይ በአዳማ ከነማ ሶስት ለሁለት ይመራ ለነበረው ክለቡ በጨዋታው የመጨረሻ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ጎል አስቆጥሮ ቡድኑን ከሽንፈት የታደገበት ይታወሳል። ትናንት ደግሞ ክለቡ በበርካታ ደጋፊዎቹ ፊት ነጥብ እንዳይጥልና ጫና ላይ ለነበሩት አሰልጣኙ ይበልጥ ጫናው እንዳይበዛባቸው የታደገች ጎል አስቆጥሯል። የትናንቱን ጎል ጨምሮ በዚህ ዓመት በ14 ጨዋታዎች 13 ጎሎችን በማስቆጠር የፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ጎል አግቢነቱን እያጠናከረ ሲሆን ይህም ባለፈው ዓመት በ11 ጎል ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ ካጠናቀቀው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ኡመድ ኡክሪ የበለጠ ጎል ማስቆጠር አስችሎታል። ፕሪሚየር ሊጉ ሊጠናቀቅ ገና 12 ጨዋታዎች የሚቀሩት በመሆኑ በቀጣዮቹ ጨዋታዎች ጎሎችን የሚያስቆጥር ከሆነ በዮርዳኖስ አባይ የተያዘውን 24 ጎል የመስበር እድል ይኖረዋል።

ፕሪሚየር ሊጉን የአዲስ አበባዎቹ ሁለቱ ተቀናቃኝ ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና አንደኛና ሶስተኛ ደረጃን ሲይዙ የደቡብ ኢትዮጵያ ተቀናቃኞች ሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ ደግሞ ሁለተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል። የአማራ ክልሎቹ ዳሽን ቢራ እና ወልድያ ከነማ ደግሞ ከሙገር ሲሚንቶ ጋር የወራጅነት ስጋት ያንዣበበባቸው ክለቦች ሆነዋል። ቢኒያም አሰፋ 13 ጎሎችን በማስቆጠር ስምንት ጎል ካስቆጠሩት ሳሙኤል ሳኑሜ እና ባዬ ገዛኸኝ በላይ ሆኖ ኮከብ ጎል አግቢነቱን ይመራል። 

የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችና የመወዳደሪያ ስታዲየም መቀያየር ሊጉን እየተቆራረጠ እንዲሄድ ያደረገው ሲሆን ትናንትና ከትናንት በሰቲያ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የተካሄዱት ሁለቱ ጨዋታዎች ቀደም ብሎ ፕሮግራም ተይዞላቸው የነበረው በአዲስ አበባ ስታዲየም ነበር። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስታዲየሙ ለክብረ በዓል ማድመቂያ እንደሚፈለግ እያወቀ ቀደም ብሎ የክለቦቹን ጨዋታ ፕሮግራም በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚካሄዱ መግለጹ ስህተት መፍጠሩን የገለጹት ደጋፊዎች “አበበ ቢቂላ ስታዲየም ለትራንስፖርት አመቺ ካለመሆኑም በላይ ለተጫዋቾች ጤንነትም አይመችም። በዚህ የተነሳ  መንግስታዊና ሀይማኖታዊ በዓላት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄዱ ቁጥር ጨዋታዎች ወደ አበበ ቢቂላ ስታዲየም መካሄዳቸው ተገቢ አልነበረም። ጨዋታ ማቋረጥ ብርቅ ያልሆነበት ፌዴሬሽን ጨዋታዎቹን ቢያቋርጥ ይሻል ነበር” ሲሉ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታ ከማካሄድ ጨዋታዎቹ  ቢቋረጡ ይሻል እንደነበረ አንዳንድ ታዛቢዎች ይገልጻሉ ይገልጻሉ። 

 ካሳ ሀይሉ 
ኢትዮ ፉትቦል


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!