የዋልያዎቹና የቡናዎቹ ጨዋታ በቂ ባልሆነ ምክንያት ተሰረዘ
መጋቢት 21, 2007

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነገ ከኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ ይዞ እንደነበር በትናንቱ እለት ማስነበባችን ይታወሳል። ሆኖም ዛሬ ከኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ጥያቄ ምክንያት እንደማይካሄድ ነው። አስተያየቱን በስልክ ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም የሰጠው የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻ ጨዋታው የማይካሄደው ከቅዱስ ጊዮርጊስና ሲዳማ ቡና የተመረጡ ተጫዋቾች ከፌዴረሽኑ ኦፊሻል በደብዳቤ ካልቀረበልን ለብሔራዊ ቡድኑ  እንዲጫወቱ  ተጫዋቾቻቸውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እንደሆነ ከፌዴሬሽኑ ለክለባቸው ስለተገለጸ እንደሆነ ተናግሯል። 
EFF


ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከአምስት ቀናት በፊት ፈረሰኞቹ ከሱዳኑ ኤል ሜሪክ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያካሂዱ ገልጸው የነበረ መሆኑን በድረ ገጻቸው አስነብበው የነበረ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን የሱዳን እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአገር ውስጥ ውድድሩ ኤል ሜሪክን በጨዋታ እንዲደራረብ የሚያደርግ ፕሮግራም በማውጣቱ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ መሰረዙን በትናንትነው እትማችን አስነብበናል። ዛሬ ደግሞ የዋሊያዎቹና የቡናማዎቹ ጨዋታ በመሰረዙ በሳምንት ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች መሰረዛቸው አስገራሚ ሆኗል። 

የቅዱስ ጊዮርጊስና የኤልሜሪክ ጨዋታ በመሰረዙ የፈረሰኞቹ ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድናቸውን ማገልገል የሚገባቸው ቢሆንም ክለባቸው ሊፈቅድላቸው አለመቻሉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ የገለጸ ሲሆን ሲዳማ ቡና በበኩሉ በፕሪሚየር ሊጉ ትናንት ምሽት ጎንደር ላይ ከዳሽን ቢራ ጋር የተጫወተ በመሆኑና ወደ አዲስ አበባ የተመለሰውም ዛሬ በመሆኑ በተጫዋቾቼ ላይ ጉዳት ይደርስብኛል ብሎ በመስጋት እንደከለከለ የሚያሳዩ መላምቶች አሉ። 

ሆኖም ችግሩ ሊከሰት የቻለው በዋናነት ፌደሬሽኑ ወይም አሰልጣኙ  የወዳጅነት ጨዋታውን ለማድረግ  ቀድመው ባለመዘጋጀታቸው ይመስለናል። ጉዳዩን የበለጠ አስገራሚ የሚያደርገው ፌዴሬሽኑ የጨዋታውን መሰረዝ ምክንያት በኢሜይል ያሳወቀበት ሁኔታ ነው። ፌዴሬሽኑ ለጨዋታው መሰረዝ ምክንያት ቅዱስ ጊዮርጊስና ሲዳማ ቡና ኦፊሻል ደብዳቤ ካልደረስን ተጫዋቾቻችንን በአሰልጣኙ ጥያቄ ብቻ አንለቅም ማለታቸው መሆኑ እንዲሁም ፌዴሬሽኑ ደብዳቤውን ለመጻፍ የመብራት መቋረጥን እንደምክንያት ማቅረቡ ነው። ፌዴሬሽኑ ያቀረበው "መብራት መቋረጥ" ምክንያት በፍጹም ተገቢነት ያለው አይመስለንም እንደዚህ አይነት ችግሮች ቀላል በሆነ የቢሮ አስተዳደር ሊፈቱ  የሚችሉ ነበሩ። እንደዚህ አይነት ምክንያት መስጠት ፌዴሬሽኑ ካለበት ከፍተኛ ሀገራዊ ሃላፊነት አንጻር ተቀባይነት አይኖረውም ወደፊት እንደዚህ አይነት ስህተቶች እንማይደገሙ  ተስፋ እናደርጋለን። ሌላው ምንም እንኳን ክለቦች በተጣበበ ሁኔታ በስልክ ብቻ ጥያቄው ቢቀርብላቸውም ለብሄራዊ ቡድኑ የወዳጅነት ጨዋታው አስፈላጊነት በአሰልጣኙ እንዲሁም በፌደሬሽኑ እስከታመነበት ድረስ ቀና ትብብራቸውን ሊነፍጉት አይገባም ነበር። የሀገር ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ክለቦች ሊያውቁት ይገባል።  በመሆኑም የቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም የሲዳማ ቡና ያቀረቡት የደብዳቤ አልደረሰንም የፕሮቶኮል ጥያቄ ጉዳይ ጨዋታውን እስከማሰረዝ መድረስ አልነበረበትም  ምክንያቱም የፕሮቶኮሉን ጉዳይ በዃላ ከፌደሬሽኑ ጋር በተገቢው መንገድ  በመወቃቀስና በመነጋገር ለወደፊቱ እንዲስተካከል  እርማት ለማድረግ ይቻል ነበር። በዚህ ረገድ  ቀሪዎቹ ለብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾችን ያስመረጡ ቡድኖች ለሀገር ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተው የተመረጡ ተጫዋቾቻቸውን በሰአቱ ወደ ልምምድ ስፍራ መላካቸው ተገቢና ቀና ሥራ ሰርተዋል  እንላለን። 

ይህ የተሰረዘው  የብሄራዊ ቡድኑና የኢትዮጵያ ቡና  የወዳጅነት  ጨዋታው ወደ ፊት መካሄድና አለመካሄዱን ለማወቅ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካልንም።  ነገር ግን ፌደሬሽኑ የተከሰቱትን ቀላል አለመግባባቶች አስወግዶ ጨዋታውን በመጪዎቹ ቀናት እንዲካሄድ ቢያደርግ መልካም ነው እንላለን።  

ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!