ሊዲያ ታፈሰ በዓለም ዋንጫ እንድትዳኝ መመረጥ ለአገራችን እግር ኳስ የሚኖረው ፋይዳ
መጋቢት 23, 2007

ዲያጎ ጋርዚያቶ የተባሉ ፈረንሳያዊ አሰልጣኝ የኢትዮጵያን ወጣት ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ እያሰለጠኑ ነው። ቡድኑ በመጀመሪያው ጨዋታ በካሜሩን አቻው አንድ ለባዶ ተሸንፎ ስለነበረ ቀጣዩን ጨዋታ በድል ተወጥቶ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት እንዳለበት ስላመነ ለግብጹ ጨዋታ ከፍተኛ ዝግጅት አድርጓል። በተለይ የአጥቂ መስመሩን ይበልጥ አጠናክሯል። በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ በሜዳውና በደጋፊው ፊት ከግብጽ ወጣት ብሔራዊ ቡድን ዳር  የሚጫወተው የጋርዚያቶ ቡድን ከግብጽ አቻው ጋር ሁለት እኩል በመሆነ ውጤት ጨዋታውን እያስኬደ ነው። 

በጨዋታው መጠናቀቂያ አካባቢ የግብጽ ተከላካዮች በግብ ክልላቸው የሰሩትን ጥፋት ተከትሎ ናይጄሪያዊቷ ዳኛ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፍጹም ቅጣት ምት ሰጠች። በዳኛዋ ወሳኔ የተበሳጩት ግብጻውያን ተጫዋቾችና የቡድን መሪ በዳኛዋ ላይ ጸያፍ ስድብና ምራቃቸውን እሰከመትፋት የደረሰ ከእግር ኳስ ስነ ምግባር የወጣ መጥፎ ባህሪ አሳዩ። ናይጄሪያዊቷ ዳኛም ለደረሰባት ጾታዊና ሞራላዊ ጥቃት አጸፋውን የመለሰችው እምባዋን በማፍሰስ ነበር። 

ከላይ የተጠቀሰው ታሪክ ከተፈጸመ 14 ዓመታትን አስቆጥሯል። ነገር ግን ያኔ ቢበዛ 15 ወይም 16 ዓመት ይሆናት የነበረች ታዳጊ ግብጻውያን ተጫዋቾች በናይጄሪያዊቷ ዳኛ ላይ የፈጸሙትን አሳፋሪ ድርጊት አይታለች። ዛሬ የሊዲያ እድሜም ሆነ ሙያዊ ብቃት አድጎ በአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ ምራቅ የሚተፋባት ዳኛ ሳትሆን በታላቁ የዓለም ዋንጫ ላይ ውድድሮችን በዳኝነት ለመምራት ከአፍሪካ ከተመረጡ ሶስት ዋና ዳኞች አንዷ ሆና ወደ ካናዳ ልትሄድ ከፊፋ እውቅና የያዘ ደብዳቤ ደርሷታል። እኛም በትናንቱ ጽሁፋችን ሴቷ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያታፈሰ በመጭው ሰኔ ካናዳ ላይ የሚካሄደውን የሴቶች ዓለም ዋንጫ በዳኝነት እንዲመሩ በፊፋ ከተመረጡ ዳኞች አንዷ መሆኗን አስነብበን ነበር።

የዳኛዋን መመረጥ አስመልክቶ በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ደስታቸውን የገለጹ ሲሆን ዳኛ ሊዲያ ታፈሰም ብትሆን ለአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙሃን ደስታዋን ገልጻለች። ኢትዮፉትቦል ዶትኮም የሊዲያን ለዓለም ዋንጫ መመረጥ ተከትሎ ለአገራችን እግር ኳስ የሚኖረውን አወንታዊ ፋይዳ ከዚህ በታች ይዳስሳል። ከዚያ በፊት ግን የሊዲያ መመረጥ በየትኛው መመዘኛ ተለክቶ እንደሆነ በአገራችን እግር ኳስ ያሉትን ችግሮች በመጠኑ እንዳስሳለን። 

እግር ኳስ በሌለበት የነገሱ የእግር ኳስ ዳኞች

ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ነብሱን ይማረውና በአንድ ወቅት ጨዋታን ሲመሩ በትክክል ባለመምራታቸው የተነሳ ቅሬታ የሚበዛባቸውን ዳኛ በሬዲዮ ሲገልጻቸው “ሲሮጡ ሳያስቡት ፊሽካ እየነፉ ጨዋታ ያስቆማሉ” ሲል ገለጻቸው። ትችቱን ከቤታቸው ሆነው በሬዲዮ የሰሙት ዳኛ በሌላ ቀን ደምሴ ዳምጤን ስታዲየም ሊገባ ሲል አገኙት። “አንተ የታባህ አየህና ነው ሲሮጥ ፊሽካ ይነፋል ብለህ የሰደብከኝ?” ሲሉ እንዳንባረቁበትና ለድብድብ እንደተገላገሉ ተናግሮ ነበር። አሁን ግን በኢትዮጵያ እንደዚያ አይነት ቀላል ስህተት የሚሰራ ዳኛም ሆነ የዳኞችን የብቃት ደረጃ በሚገነባ ብርዕ የሚተች ጋዜጠኛ እምብዛም ነው ማለት ይቻላል። 

የዳኝነት ችግሮች በመጠኑም ቢሆን እየተቀረፉ ቢሆንም አሁንም ድረስ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲሳሳቱ እና ጨዋታ ሲረበሽ እያየን ነው። ያም ሆነ ይህ ግን በአፍሪካ ዋንጫ ከኢንተርናሽናል ዳኛ ሀይለመላክ ተሰማ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተመርጦ ጨዋታ መምራት ችሏል። በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግና በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽነ ውድድርም ሌሎች ዳኞች በተደጋጋሚ ጊዜ የመዳኘት እድል ሲሰጣቸውና የተጣለባቸውን አደራ በብቃት ሲወጡ አይተናል። አሁን ደግሞ በዓለም ዋንጫው ሴቷ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በውድድሩ ፍትሃዊ ፍርዷን እንድትሰጥ ፊፋ የመረጣት ሶስተኛዋ የአህጉሩ ዳኛ ሆናለች። 

ዳኞቹ ይህን ያህል አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዲመሩ እድል ሲሰጣቸውና በብቃታቸው ሲመረጡ እግር ኳሳችን ከፊሽካ የዘለለ እድገት አለማሳየቱ አስገራሚ ሆኗል። የባምላክንም ሆነ የሊዲያን ለታላላቅ ውድድሮች መመረጥ ለተመለከተና የአገሪቱን እግር ኳስ ደረጃ ለሚያውቅ የስፖርት ቤተሰብ “ዳኞቹ የትኛውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዳኝተው ነው የተመረጡት” ብሎ ቢጠይቅ ሊነቀፍ አይገባውም ባይ ነን። 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾች ፕሮፌሽናል ዲስፕሊን

ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ወደ ኋላ መቅረት ከሚነሱ በርካታ ምክንያቶች መካከል ተጫዋቾች ፕሮፌሽናል ባህሪ የሌላቸው መሆናቸው አንዱ ነው። ተጫዋቾቹ ፕሮፌሽናል ባህሪ ከሌላቸው ደግሞ ውድድሮቹን ለሚመሩ ዳኞችም ሆነ ጨዋታዎቹን ለመመልከት በስታዲየም ለሚታደሙ የስፖርቱ ተመልካቾች አስቸጋሪ ይሆናል። በተለይ ለዳኞች ይበልጥ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል። ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች እንደ ግብጻዊው ተከላካይ በዳኞች ላይ ምራቃቸውን አይትፉ እንጅ ዳኞቹን በተለያዩ መንገዶች መጎንተላቸውና ሙያዊ ስነ ምግባራቸውን በተገቢው ደረጃ እንዳይወጡ ሲያደርጉ ይታያሉ። 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለዳኞች በተለይም ለሴት ዳኞች ምቹ የስራ ከባቢንና ነጻነትን ባለመፍጠሩ ዳኞች በተደጋጋሚ ጊዜ ቅሬታ ሲያቀርቡ ይሰማሉ። ዳኞቹ በተደጋጋሚ ከሚያቀርቧቸው ቅሬታዎች መካከል ለደህንነታቸው አስተማማኝ ጥበቃና የህይወት ዋስትና መድን ያልተገባላቸው መሆኑን ነው። የስታዲየሞች ደረጃ ፕሮፌሽናል ባልሆነበትና የደጋፊዎች ስሜት ሲገነፍል በሚነሱ ብጥብጦች የመጀመሪያው ገፈት ቀማሽ የሆኑት ዳኞች ለሙያቸው የሚከፈላቸው የውሎ አበልም የዚያኑ ያህል ሙያውን ያላከበረ ነው። ሊዲያ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን እንድታጫውት የተመረጠችው ከዚህ ሊግ ነው።   

እግር ኳሱ በደከመበት ዘመን የተገኘ ትልቅ ስኬት

የኢትዮጵያ እግር ኳስ በውጤትም ሆነ በአደረጃጀት ሲለካ በአህጉሪቱ የታችኛውን ደረጃ ከያዙ አገሮች እንደ አንዱ ይቆጠራል። በተለይ በውጤት በኩል ከተመለከትነው በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የወንዶች ብሔራዊ ቡድን እና የሴቶች ብሔራዊ ቡድንን ውጤት ጨምሮ አገራቸውን ወክለው በአህጉራዊ ውድድሮች የሚሳተፉ ክለቦቻችን የሚያስመዘግቡትን ውጤት ማየት በቂ ነው። እግር ኳሱ በተዳከመበት በዚህ ወቅት ዳኞቻችን በፊፋ ሳይቀር ተመርጠው ውድድር እንዲመሩ ሲደረግ አገሪቱ ከእግር ኳስ ተጫዋቾችና አስተዳዳሪዎች ያጣችውን ክብር ከዳኞቿ እያገኘች ነው እንዲባል ያደረገ ሆኗል። የዳኞቹን እድልም በእግር ኳሱ ውድቀት ላይ የተገኘ መጽናኛ ልንለው እንችላለን። 

የአህጉሩ ኮታ 

ፊፋ በዓለም ዋንጫ ውድድሮች የሚዳኙ ዳኞችንም ሆነ የሚሳተፉ ቡድኖችን ሲመድብ ለአፍሪካ የሚሰጠው ኮታ እጅግ ዝቅተኛውን ነው። የአንበሳውንና የነብሩን ኮታ አውሮፓውያንና ላቲን አሜሪካውያን እንዲወስዱ ካደረገ በኋላ የመጨረሻውን የድመቷን ኮታ የሚሰጠው ለአፍሪካ ነው። በዚህ ዓመት ሰኔ ስድስት እ.ኤ.አ የሚካሄደውን የሴቶች ዓለም ዋንጫ እንዲዳኙ ከተመረጡ 22 ዋና ዳኞች፣ ሰባት አጋዥ ዳኞችና 44 ረዳት ዳኞች መካከል አፍሪካ የደረሳት ሶስት ዋና ዳኛ እና አራት ረዳት ዳኛ ብቻ ነው። ይህ የሚያመለክተው ደግሞ ፊፋ አፍሪካን የሚፈልጋት ለፕሬዚዳንትነት ምርጫ ድምጽ እንድትሰጠው እንጅ ለታላቅ ውድድር ብቁ ሆና እንድትሳተፍ እድል የማያመቻችላት መሆኑን ነው። 

ፊፋ ለአፍሪካ የሰጠው ኮታ አነስተኛ መሆኑ ሳያንስ በእግር ኳሱ እድገት ላይ ገና ዳዴ እያለች የምትገኘው ኢትዮጵያ ደግሞ ጠንካራ የውስጥ ሊግ ውድድር ከሚያካሂዱት ደቡብ አፍሪካ፣ ካሜሩን፣ ጋና፣ ናይጀሪያ፣ ኬኒያና የመሳሰሉት አገሮች ለይቶ ሊዲያ የተባለችዋን ኢትዮጵያዊት ዳኛ መረጠ። በመጭው ሰኔ በሚያደርገው የፕሬዚዳንት ምርጫ ድምጼን እሰጦታለሁ ስትል ለወቅቱ ፕሬዚዳንት ሴፕ ብላተር ቃል የገባችው አፍሪካ፤ ከሴፕ ብላተር የተሰጣት የውለታ ድርጎ ግን አሳዛኝ ሆኗል። ፊፋ ሰኔ መጀመሪያ ላይ ለሚያዘጋጀው የሴቶች የዓለም ዋንጫ 53 ዳኞችን ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ሲመርጥ 53 አገሮችን ከያዘችው ከአፍሪካ ግን ሰባት ዳኞችን ብቻ ነው የመረጠው። 

ፊፋ ያዘጋጀው ምቹ አጋጣሚ
Canada Women's World Cup 2015
ውድደሩ እ.ኤ.አ ሰኔ ስድስት ቀን 2015 በካናዳ ከመካሄዱ በፊት የፊታችን ሚያዝያ 18 እስከ 24 በስዊዘርላንድ ዋና ከተማ የፊፋ መቀመጫ ዙሪክ ውድድሩን የሚመሩ ዳኞች ስልጠና ይወስዳሉ። ከዚያ ስልጠና መጠናቀቅ በኋላ ደግሞ ውድድሩ ሊካሄድ አስር ቀናት ሲቀሩት ውድድሩ በሚካሄድባት ካናዳ ቫንኮቨር በተባለች ከተማ የአስር ቀናት ስልጠና ይሰጣቸዋል። ከስልጠናው በኋላ ውድድሩን በዋና ዳኝነት እና በአጋዥ ዳኝነት የሚመሩት እነማን እንደሆኑ ይወሰናል። 
ይህ ስልጠና ደግሞ የዳኛ ሊዲያን ሙያዊ ብቃት ከማሳደጉና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከማስጠበቁ በተጨማሪ ዳኛዋ በስፍራው መገኘቷ በራሱ ለአገሪቱ እግር ኳስ የሚያስተላልፈው አዎንታዊ መልዕክት ከፍተኛ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ዳኛዋ በምትወስዳቸው ከፍተኛ የዳኝነት ስልጠናዎች ብቃቷን ማሳደግ ስለምትችል የአገር ውስጥ ውድድሮችን በምትመራበት ጊዜ ትክክለኛ ፍትህ መስጠት  እንድትችል ያደርጋታል። ይህ ደግሞ ለአገሪቱ እግር ኳስ እድገት የራሱን አስተዋጽኦ ይጫወታል። እንዲሁም ዳኛዋ በስልጠና የምታገኘውን እውቀት ወደ አገሯ ይዛ ስትመለስ ለኢትዮጵያውያን የሙያ አጋሮቿ ማካፈል የምትችል ከሆነ የዳኞችን ብቃት ለማሳደግ ስለሚረዳ የሚመለከታቸው አካላት መድረኩን የሚያመቻቹ ከሆነ መልካም አጋጣሚ ነው። 

የእግር ኳስ ባለሙያዎች በታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረክ ሲካፈሉ ለአገራቸው የሚያበረክቱት ትልቁ ጥቅም በመድረኩ የሚያገኙትን ስልጠናና ልምድ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ለሙያ አጋሮቻቸው ማካፈል ሲችሉ ነው። ኢትዮጵያም በሊዲያ ለመጠቀም ከዳኛዋ ፍላጎት በተጨማሪ የፌዴሬሽኑ ትብብርና መድረኮችን ማመቻቸት አስፈላጊ ነው። ኢትዮፉትቦል ዶትኮምም ለኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ መልካም የውድድርና የስልጠና ጊዜ እየተመኘ የዳኞቻችን በታላላቅ መድረኮች በሙያቸው እንዲያገለግሉ መመረጥ ቀጣይነት እንዲኖረው የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር ያስፈልጋል እንላለን። 

ካሳ ሀይሉ 

...............................................................................................
የኢትዮጵያን እግር ኳስ በተመለከተ ገንቢ የሆኑ አስተያየትና ሃሳብ ያላቸው የስፖርቱ ባለሞያዎችና ጋዜጠኞች  ጽሁፎቻቸውን ቢልኩልን  በድረገጻችን  ጽሁፎቹን ለማስተናገድ ዝግጁ ነን።
...............................................................................................

ኢትዮ ፉትቦል


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!