ከቡና ጋር ያልተሳካለት ቶጎዋዊው ኤዶም ዳሽን ቢራን ከወራጅ ቀጠናው ይታደገው ይሆን?
መጋቢት 24, 2007

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17 ዓመታት ጉዞ ኢትዮጵያ ቡና አንድ ጊዜ ብቻ ዋንጫውን ያነሳ ቢሆንም አጥቂዎቹ ግን ከአምስት ላላነሰ ጊዜ  የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ጎል አግቢነትን ክብር ተቀዳጅተዋል። ታፈሰ ተስፋዬ ሶስት ጊዜ፣ ዮርዳኖስ አባይ አንድ ጊዜ እና የአሁኑ የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ መሳይ ከበደ አንድ ጊዜ በቡና ማሊያ ኮከብ ጎል አግቢ ሆነው ያጠናቀቁ አጥቂዎች መሆናቸው ይታወሳል። ምናልባት ዘንድሮ ሊጉን በኮከብ ጎል አግቢነት እየመራ ያለው ቢኒያም አሰፋ በመሪነቱ የሚያጠናቅቅ ከሆነ ስድስተኛው ተጫዋች ይሆናል ማለት ነው።
Edom  WHile hew was Under Ethiopian Coffee

ቡናዎች እንደዚህ አይነት የአጥቂዎች ሪከርድ ቢኖራቸውም ላለፉት ሶስትና አራት ዓመታት የክለባቸው ሁነኛ ችግር የአጥቂ መስመሩ መሆኑን የተረዱት የክለቡ የቦርድ አመራርና ደጋፊዎች የክለቡን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ባለፈው ክረምት የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት ሲከፈት ቶጓዊውን ኤዶምንና ቤኒናዊውን ሻኪሩን ማዘዋወራቸው ይታወሳል። ሁለቱን ምዕራብ አፍሪካውያን አጥቂዎች ክለቡ  ከልዩ ልዩ ጥቅማጥቅሞች ውጭ በወር ለእያንዳንዳቸው አንድ አንድ ሺህ ዶላር ይከፍላቸዋል። ነገር ግን ሁለቱም አጥቂዎች የክለቡን ፍላጎት ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል መክፈል ባለመቻላቸው ለተደጋጋሚ ትችት ተዳርገው ቆይተዋል። በዚህ የተነሳም ቶጓዊውን ኤዶምን በውሰት ለዳሽን ቢራ ለመስጠት ተገድዷል።
 
የኤዶም ስንብት ምክንያት

ቶጓዊውን አጥቂ “ከሜዳ ላይ ይልቅ ከሜዳ ውጭ ባለው ህይወቱ ተለይቶ እንዲታወቅ የሚፈልግ አይነት ተጫዋች ነው” ይሉታል የልጁን የእለት ከእለት እንቅስቃሴ የሚከታተሉ ሰዎች ሲናገሩ። በተለይ አንድ ጊዜ የክለቡን ስምና ዝና የሚያጎድፍ ድርጊት በመኖሪያ ካምፑ ሲፈጽም ተገኘ። በዚህ ድርጊቱ የተበሳጨው ክለቡ ደግሞ ተጫዋቹን በይቅርታ ማለፍ ባለመፈለጉ ከወር ደመወዙ ግማሹን ቀጥቶታል። ከገንዘብ ቅጣቱ በተጨማሪ ደግሞ ከባድ ማስጠንቀቂያ እንደደረሰውም ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። 
Edom  was unsuccessful in Ethiopian Coffee

ሌላው የቶጓዊው አጥቂ ችግር ሜዳ ላይ የሚያሳየው አቋም ደጋፊውን የማያሳምን ክለቡን ደግሞ የማይጠቅም ሆኖ መገኘቱ ነው። በተለይ ክለቡ ጎል በሚፈልግበት ወቅት የክለቡን ፍላጎት ማሳካት ባለመቻሉ ክለቡ ዝም ብሎ ደመወዝ ከሚከፍለው ለምን ወደ መጣበት አይመልሰውም? የሚሉ አስተያየቶች ተበራክተው ቆይተዋል። በዚያ ላይ ተጫዋቹ ወደ ሜዳ እንዲገባ የሚሰጡት እድሎች አነስተኛ መሆናቸውን አስመልክቶ ቅሬታውን በተደጋጋሚ ጊዜ በማሰማቱ ከአሰልጣኞቹ ጋር ሳይጋጭ እንዳልቀረ ይገመታል። እነዚህ ምክንያቶች ተደማምረው ኤዶምና ቡና ቢያንስ ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት ላይገናኙ ተለያይተዋል። 

ኤዶም  ዋና ክለቡን ኢት.ቡናን  ይገጥማል

ክለቦች የማይፈልጓቸውን ወይም ልምድ እንዲያገኙ የሚፈልጓቸውን ተጫዋቾች ልምድ እንዲያገኙ በውሰት ለሌላ ክለብ ሰጥተው በቋሚነት የሚሰለፉበትን እድል እንዲያገኙ ማድረግ የተለመደ ነው። ታላላቆቹ የአውሮፓ ክለቦችም ይህንን ልምድ ሲተገብሩት ይታያሉ። በውሰት ለሌላ ክለብ ተሰጥተው ወደ ዋና ክለባቸው ሲመለሱ የተሳለ እግራቸውን ይዘው ከተመለሱት የአውሮፓ ተጫዋቾች መካከል የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ የአሁኑ የአርሴናል አጥቂ ዳኒ ዌልቤክ በሰንደርላንድ፣ የአርሴናሎቹ ጃክ ዌልሼርና ፍራንስ ኮክለ በቦልተን ወንደረርስና ቻርልተን አትሌቲክ እንዲሁም የቀድሞው የሪያል ማድሪድና የማንቸስተር ዩናይትድ አማካይ ዴቪድ ቤካም በኖቲንግሃም ፎረስት ያሳለፏቸው የውሰት ጊዜያት በውሰት ወደሰጧቸው ክለቦቻቸው ትልቅ ልምድ ይዘው እንዲመለሱላቸው ማድረጋቸው ይጠቀሳል። 

በሌላ በኩል ደግሞ ቼልሲ ፈርናንዶ ቴሬዝን ወይም አርሴናል ሉካስ ፖዶልስኪን ለኤሲ ሚላንና ለኢንተር ሚላን በውሰት ሲሰጧቸው ልምድ እንዲያገኙ ሳይሆን ለተጫዋቾቹ ቦታ ስለሌላቸው መሆኑን ክለቦቹም ሆኑ ተጫዋቾቹ ተናግረዋል። 

ኤዶም ከኢትዮጵያ ቡና ለቆ ወዳ ዳሽን ቢራ በውሰት ሲዘዋወር ልምድ አግኝቶ እንዲመለስ ሳይሆን በቡና ውስጥ እንደ ቢኒያም አሰፋ፣ አስቻለው ግርማ እና ሻኪሩ አይነት አጥቂዎች ቦታውን በመያዛቸው ለኤዶም የሚሆን ቦታ ባለመኖሩ እንደሆነ ግልጽ ነው። ስለዚህ ኤዶም ከቡና የወጣው ከቡና ጋር የሚያስተሳስረው ሌላ የአብሮነት ገመድ እንደሌለው አውቆ ነው ማለት ይቻላል። 
በውሰት ውል ወደ ሌላ ክለብ በሚሄዱ ተጫዋቾች ባለቤት ክለባቸው ሙሉ በሙሉም  ባይሆንም በተወሰነ ደረጃ የባለቤትነት መብት አላቸው። ይህ መብትም ባለቤት ክለቦች የተዘዋወረው ተጫዋች ከአዲሱ ክለቡ ጋር ሆኖ በውሰት የሰጠውን ክለቡን የማይገጥም መሆኑ ይገኝበታል። የኤዶምና የኢትዮጵያ ቡና ስምምነት ላይ ግን ይህ ውል ባለመካተቱ የፊታችን ሰኞ ኢትዮጵያ ቡና እና ዳሽን ቢራ በሚያደርጉት 17ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ላይ በዳሽን ቢራ ማሊያ ዋና ክለቡን ኢትዮጵያ ቡናን የሚገጥም ይሆናል።  

እንደ ኤዶም አይነት ከእናት ክለባቸው ተገፍተው በውሰት የሚሸጡ ተጫዋቾች ደግሞ በአዲሱ ክለባቸው ማሊያ በቀድሞ ክለባቸው ላይ ጎል ከማስቆጠር ጀምሮ ከፍተኛ አገልግሎት መስጠት ይፈልጋሉ። ይህን ስለሚያውቁም ሳይሆን አይቀርም የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ አለቃ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ወጣትም ሆነ የተገፉ ተጫዋቾቻቸውን በውሰት ሲሰጡ ክለቡ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ሲጫወት ከማንቸስተር ዩናይትድ በውሰት ያገኛቸውን ተጫዋቾች እንዳይጠቀም የሚከለክል ውል የሚያስገቡት።  

ኤዶም ዳሽንን የመታደግ አቅም አለው?

ዳሽን ቢራ በዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ   ነጥብ ሰብስቦ    የጎል እዳ ይዞ 12ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጡ የወራጅ ቀጠናው አድማቂ ሆኗል። ለዚህ ያበቃው ደግሞ የአጥቂ መስመሩ ጎል ማግባት የተሳነው መሆኑ ነው። በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች በአንዱም ጨዋታ ከአንድ ጎል በላይ ማስቆጠር አልቻለም። ይህን ችግሩን የተረዱት አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ እና ካሊድ መሃመድ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያልተሳካለትን  ኤዶምን ከውድቀት እንዲታደጋቸው በቡና የሚከፈለውን ያህል ደመወዝ እየከፈሉ ሊያጫውቱት ጎንደር ወስደውታል። በመጀመሪያ ጨዋታውም አሰልጣኞቹ የሰጡትን አደራ ለመወጣት የሚያስችል ብቃት እንዳለው ያሳየበትን ጎል በፕሪሚየር ሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ላይ በማስቆጠር ማሳየት ችሏል። 

 እድሜው የገፋው መዳኔ ታደሰ እና “የጎል መስመሩን ለይቶ የማያውቀው” የሚባለው ሚኬኤል ጆርጆ ለዳሽን ቢራ የጎል ድርቅ ምክንያት ተደርገው የሚታዩ በመሆናቸው የክለቡን ችግር ኤዶም ይፈታዋል ብለው እንደማያምኑ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም ይናገራሉ። ለአስተያየታቸው ማጠንከሪያ የሚያነሱት ምክንያት ደግሞ ኤዶም በቡና ለስድስት ወራት ቆይታ አድርጎ አንድም ጎል ያላስቆጠረ መሆኑን በማንሳት ነው። ለማንኛውም የኤዶምና የዳሽን ቢራ ጊዜያዊ አብሮነት ውጤተማ መሆንና አለመሆኑን ለመናገር ጊዜው ገና በመሆኑ በመልካምም ሆነ በደካማ ጎኑ መናገር አይቻልም። ያም ሆነ ይህ ግን ዳሽን ቢራ ከመውረድ ለመዳን ኤዶም ደግሞ ከቡና ጋር ሊሳካለት ባይችልም ብቃት እንዳለው ለማሳየት ከሚኖረው  ጉጉት አንጻር ተፈላልገው ተገናኝተዋል ብሎ ማለፉ ይሻላል። 

ካሳ ሀይሉ
>ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!