ብሔራዊ ቡድኑ ከባሬቶ በኋላስ?
መጋቢት 27, 2007

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶን ማሰናበቱን ኢትዮ ፉትቦል ከትላንት በስቲያ ከውስጥ አዋቂ ምንጮች በደረሰው መረጃ መሰረት መዘገቡ ይታወሳል። ቀደም ብሎም አሰልጣኙ ሊሰናበቱ እንደሚችሉ የብዙሃኑ የእግር ኳስ ተመልካች  ግምት ነበር። አሰልጣኙ ብሔራዊ ቡድኑን ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ከአንድ ጨዋታ በላይ ማሸነፍ ባለመቻላቸው ጫና በዝቶባቸው ቆይቶ ስለነበረ የመሰናበታቸው ጉዳይ ተጠባቂ ነበር። በተለይ አሁን አሁን የብሄራዊ ቡድኑን ተደራራቢ ውጤት ማጣት ተከትሎ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ላይ ከተለያየ አቅጣጫ እየደረሰበት ያለውን ውጫዊ ተጽእኖና ጫና ፌዴሬሽኑ መቋቋም ባለመቻሉ ጫና ወደበዛበት አቅጣጫ ማዘንበሉ አልቀረም። ልክ ከዛሬ አንድ ዓመት በፊት አቶ ሰውነትን ለማሰናበት በቻን ያስመዘገቡት ደካማ  ውጤት እንደ ምክንያትነት እንደቀረበው ከትላንት በስቲያ ፌዴሬሽኑ በፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ላይ የወሰደው አቋም ከዚህ የተለየ አይመስልም። ምክንያቱም አሰልጣኙ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡና ስራውን ሲረከቡ “አልጀሪያ ማላዊ ማሊ እና ሱዳንን አሸንፈህ ወደ አፍሪካ ዋንጫ እና መላው አፍሪካ ጨዋታዎች ታደርሰናለህ” የሚል ስምምነት በውላቸው የለም። የቡድኖቹ ስም ባይጠቀስም ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ እንዲያበቁን አልነበረም የተቀጠሩት። 
Bareto with his players


ሌላው ሚስተር ማሪያኖ ባሬቶ የያዙት ቡድን እድለኛ አልነበረም ለማለትም ይቻላል። ምክንያቱም ታላላቆቹን የእግር ኳስ አገሮች ተፋልሞ ለማሸነፍ የአንድ ጀምበር ሥራ ሳይሆን የረጅም ጊዜ የቤት ሥራ የሚጠይቅ ውጤት ነው። ፌዴሬሽኑም አሰልጣኙን ሲያሰናብት ብሄራዊ ቡድኑ ለጊዜው ውጤት አልባ  በመሆኑ  ላይ ብቻ ባተኮረ ትችት ተመስርቶ በደረሰበት የሚዲያና የውጪ ጫና ብቻ ከሆነ ተገቢነት አይኖረውም እንላለን ምክንያቱም አሰልጣኙም የገጠማቸውን ነባራዊ ሁኔታም ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። 
 
ለምሳሌ ባለፈው የዓለም ዋንጫ ብራዚል በደጋፊዋ ፊት በጀርመንና በሆላንድ አይቀጡ ቅጣት ስትቀጣ አሰልጣኟን ማሰናበቷ ይነገራል። ለፍሊፕ ስኮላሪ መሰናበት ምክንያቱ ውጤቱ ሳይሆን ይህ ውጤት ከመመዝገቡ በፊት ብሔራዊ ቡድኑን ቢቀላቀሉ አገራቸውን አንድ ደረጃ ከፍ ማድረግ የሚችሉ ተጫዋቾች እያሉ በአሰልጣኙ ግትርነት ባለመመረጣቸው ውጤቱ ሊከፋ ችሏል ብለው ያምናሉ። ብራዚላውያን ለውጤቱ መጥፋት የተመረጡት ተጫዋቾች ናቸው ብለው ሲናገሩ አገራቸው በርካታ ከዋክብት እንዳላት እየተናገሩ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ግን እንኳን እንደ አልጀሪያና ማሊ አይነት ጠንካራ ቡድኖችን ለመፋለም ይቅርና በአፍሪካ ዋንጫ አዳነ ግርማ እና አስራት መገርሳ ተጎድተው ሲወጡ ቡድኑ ውስጥ የተፈጠረውን ክፍተት አይተናል። በዚያ ጨዋታ አሰለጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚይዙትንና የሚጨብጡትን ያጡት ለቡድናቸው የሚመጥን ተጫዋች ኢትዮጵያ ውስጥ እያለ በግትርነታቸው ሳይመርጡት በመሄዳቸው አይደለም ይልቅ አገሪቱ ውስጥ አማራጭ ተጫዋች በማጣታቸው እንጅ። 
Baretos National Team

ፖርቹጋላዊውን አሰልጣኝም የገጠማቸው ይህ ነው። ሳላዲን ሰይድ ተጎዳ ጌታነህ ከበደ በቀይ ካርድ ወጣባቸው። አገሪቱ ውስጥ ደግሞ አሉ የሚባሉ አጥቂዎች እነዚህ ናቸው። እነዚህን አጥቂዎች በአንድ ጀምበር አጥቶ ጎል መጠበቅ ማለት የዋህነት ነው። ለዚህም በጠንካራዋ አልጀሪያ በደርሶ መልስ አምስት ለሶስት ተሸነፉ በማሊ ደግሞ አራት ለሁለት። ይህ ውጤት ምናልባት እነ ሳላዲን ቢኖሩ ሊጠብ እንደሚችል ግልጽ ነው። ግን እነ ሳላዲንን ብቻ ይዞ ስንት ኪሎ ሜትር መጓዝ ይቻላል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚቻለው የአገራችን ክለቦችም ሆነ አሰልጣኞችና ፌዴሬሽኑ በታዳጊዎች ላይ በመስራት ተተኪዎችን ለብሔራዊ ቡድኑ ሲያቀርቡ ነው። ይህ ባልተፈጠረበት አገር አሰልጣኞችን እንደፈለጉ ማስወጣትና ማስገባት ለውጤት መጥፋት መፍትሔ ይሆናል ተብሎ አይታመንም። የአሰልጣኞችን ወርሃዊ ደመወዝ መጨመርም ሆነ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ማቅረብ ለአሰልጣኞች የስራ የተነሳሽነትን ይፈጥር ይሆናል እንጅ ያልተሰራበትን ውጤት ሊያስገኙ አይችሉም። 

የእጩዎቹ ማንነት

ፌዴሬሽኑ ማሪያኖ ባሬቶን ለመተካት አራት እጩችን ማቅረቡን  ከውስጥ አዋቂ ምንጮች መረጃ ታውቋል። ከአራቱ እጩዎች መካከል ሶስቱ በክለብ ስራ ላይ የሚገኙ ሲሆን ምናልባት ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሳህሌ ኮንትራታቸው በሰኔ የሚጠናቀቅ ይሆናል። አሁን በእርግጠኝነት ከክለብ ስራ ነጻ የሆኑት አቶ ሰውነት ቢሻው ብቻ ናቸው። ስለ እጩነታቸው የሁሉንም አሰልጣኞች መልስ ማግኘት ባንችልም የክለብ ስራቸውን አቋርጠው ወደ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ማምራት የሚፈልጉ ከሆነ ከክለባቸው ጋር የሚኖራቸው ኮንትራት አሳሳቢ ነው። ምክንያቱም ፌዴሬሽኑ አሁንም ምን ሊወስን እንደሚችል ስለማይታወቅ አሰልጣኞቹ ተደላድለው ከያዙት የክለብ ስራቸው ለቀው ብሔራዊ ቡድኑን ለማሰልጠን ቢስማሙና ፌዴሬሽኑ ደግሞ ነገ የፊፋ ባለሙያ ወይም የጋዜጠኞች ጩኸት ቢበረክትበት ከስራቸው ሊያሰናብታቸው ስለሚችል በእርግጠኝነት የመስራት ነጻነት ስለማይኖራቸው የፌዴሬሽኑን ጥያቄ በይሁንታ ላይቀበሉት ይችላሉ ተብሎ ይገመታል። በመሆኑም ፌዴሬሽኑ መጨነቅና በይበልጥ መወያየት ያለበት በአሰልጣኝ ምርጫው ላይ ብቻ ሳይሆን ለሚመርጠው አሰልጣኝ ስለሚሰጠው የሥራ ነጻነት እንዲሁም ሃላፊነትና ግዴታ ጭምር ነው። ፌደሬሽኑ የሀገሪቷ እግር ኳስ ያለበትን ደረጃ  ባገናዘበ መልኩ ከአሰልጣኙ የሚጠበቀውን በጊዜ የተገደበ የሥራ ውጤት በግልጽና በዝርዝር አንድ ሁለት ብሎ ማስቀመጥ ይኖርበታል እንላለን። ይህን ማድረግ ከተቻለ ፌዴረሽኑ ወደፊት ለሚወስዳቸው እርምጃዎች መሰረት ይሆኑታል። በስራው ላይ እንቅፋት ከሚፈጥሩ አላስፈላጊ ትችትና ጫናም ነጻ እንዲሆን ይረዱታል።

ወደ እጩ አሰልጣኞቹ ያሉበት ሁኔታ ስንመለስ የአሰልጣኝነቱን ቦታ ለመረከብ በህዝቡ ካላቸው ተቀባይነትና አሁን ደግሞ ከክለብ ሥራ ነጻ በመሆናቸው አቶ ሰውነት ቢሻው የሚረከቡት ይመስላል። አቶ ሰውነት በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫና በ20ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያዎች ቡድኑን ወደ ተሻለ ደረጃ አድርሰውታል ተብለው የሚታመንባቸው አሰልጣኝ ሲሆኑ በተጫዋቾች አያያዝ በኩልም ጥሩ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። ነገር ግን አቶ ሰውነት ከጠንካራ ጎናቸው ጋር አብሮ የሚነሳው ድክመታቸው ተጫዋቾቻቸውን ፕሮፌሽናሊዝም እንዲላበሱ አያደርጉም የሚባለው እና በክለብ ስራቸው ውጤታማ አለመሆናቸው ነው። በተለይ አራቱን ክለቦች ማለትም መብራት ኃይልን ትራንስ ኢትዮጵያን ጉና ንግድንና ኒያላን ከላይኛው ሊግ ወደ ታችኛው ሊግ እንዲወርዱ ምክንያት በመሆናቸው ይተቻሉ። 

የተረሱት አሰልጣኞች

በእጩነት ከቀረቡት አሰልጣኞች ካላቸው ውጤትና የሙያ ምስክር ወረቀት አኳያ ስናየው ተመጣጣኝ የስራ ልምድና ብቃት ያላቸው አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ እና ስዩም ከበደ የተዘነጉ ይመስለናል። ምንም እንኳ የቀድሞው የአቶ ሰውነት ምክትል ስዩም ከበደ በየመን በክለብ ሥራ ላይ ቢገኝም ውሉን አቋርጦ ለመምጣት የሚከብደው አይመስለንም። ከራሱ እቅድ ውጭ የባለስልጣናት ጣልቃ ገብነትን አጥብቆ የሚቃወመው አስራት ኃይሌም ቢሆን አሁን በክለብ ስራ የተጠመደ ባለመሆኑ እና የኢትዮጵያን እግር ኳስ ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ ከእጩዎች ዝርዝር ውስጥ ሊካተት ይገባው ነበር እንላለን።

ካሳ ሀይሉ
ለኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
girma sahlle [983 days ago.]
 hi brother i give one advice for changing the football ethiopia you must work on under age 7-9 and 9-11and 11 -13and 14-15 if you make like this we have a good result after 3-5 years not change the coach we need also a coach of kids it is not the the same a coach of adult thx for now

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!