ሥለኢትዮጵያ እግ.ኳስ.ፌዴሬሽን አንዳንድ ነጥቦች
መጋቢት 29, 2007

በዚህ እጅግ ሰፊ ጽሁፍ ሊወጣው በሚችል ርዕስ ላይ አጠር ያለ ጽሁፍ ማዘጋጀት በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም በዛሬው ምልከታችን ዋና ዋና የሚባሉትን  እንዳስሳቸዋለን። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከዋልያዎቹ በተጨማሪ ሌሎች ብሔራዊ ቡድኖችንም የሚቆጣጠርና ሌሎች ተጨማሪ ሀገራዊ አደራዎች የተጣሉበት ነው። ነገር ግን ፌዴሬሽኑ በብዛት የሚተቸውም ሆነ የሚወደሰው በአብዛኛው በወንዶች ብሔራዊ ቡድን ውጤትና ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በመመርኮዝ ብቻ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ ሁኔታ ደግሞ ፌደሬሽኑን እድለኛ እንዳይሆን አድርጎታል። 

የአንድ አገርም ሆነ ክለብ ደረጃ የሚለካው በሚያስመዘግበው ውጤት መሆኑ ይታወቃል።  የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚመራውን የወንዶች ብሔራዊ ቡድን ውጤት ስናይ ፍጹም አንገት ባያስደፋም ልብን ሞልቶ የሚያስነግር ሁኔታ ላይ አይገኝም። በዚህ ምክንያትም ይመስላል ፌዴሬሽኑ በለተያየ ጊዜ የሰራቸው ሊጠቀሱ የሚችሉ የስኬት ስራዎቹ ተሸፍነው ሳይገለጡ ሲቀሩ የምናየው። 

ፌዴሬሽኑ በስኬት ያስመዘገባቸው ስራዎች አሉት ስንል ግን ፌዴሬሽኑ ችግሮች የሉበትም ለማለት ፈልገን እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በተለይ እንደኛ አይነት በበርካታ ውስብስብ ሁኔታዎች ውስጥ ያለፈና እያለፈ ያለን  ፌዴሬሽን ችግር የለበትም ብሎ መናገር አይቻልም። ባይሆን ከችግሮቹ በዘለለ ሊደነቁለት የሚገቡ ስራዎችንም እናውሳ ለማለት ነው። 

በሴቶች እግር ኳስ

ፌዴሬሽኑን ሊመሰገን ይገባዋል ከሚያስብሉት መልካም ስራዎቹ መካከል በሴቶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች ላይ የወሰደው መልካም ስራ ነው። በተለይ በአሁኑ ሰዓት ሜዳ ላይ የሚጨበጥ አንዳችም ውጤት በሌለው የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ላይ አሰልጣኝ ሲቀጠር ከባድ ፈተና የሚጠይቅ ቢሆንም ፌዴሬሽኑ ግን ለአሰልጣኞች ከድሮው በተሻለ ዳጎስ ያለ ወርሃዊ ክፍያ በመክፈል ቀጥሯል። አዲስ የተቀጠሩት አሰልጣኞች ሁለቱም ሴቶች መሆናቸው አንድ ስኬት ሲሆን ለዋና አሰልጣኟ በወር 50 ሺህ ብር ደመወዝ ለመክፈል መወሰኑ በራሱ ዘርፉን ትኩረት እየሰጠው መሆኑን ያሳያል። ቀደም ሲል ይህን ያህል ደመወዝ ይከፈላቸው የነበሩ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው ብቻ እንደነበሩ ይታወቃል። ለዚያውም አቶ ሰውነት ይህንን ያህል ደመወዝ የተከፈላቸው በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ቡድኑን ከመጨረሻዎቹ አስር ምርጥ የአፍሪካ ቡድኖች ውስጥ ካስገቡ በኋላ ነበር። 

ይህ ለሴቶች እግር ኳስ ፌደሬሽኑ የሰጠው ትኩረት በዘላቂነት እንዲጓዝ ግን ፌዴሬሽኑ ትኩረት ሰጥቶ ያልተንቀሳቀሰበት ሁኔታም እንዳለ እንረዳለን። ይኸውም ለወንዶች ብሔራዊ ቡድን በዓመት 14 ሚሊዮን ብር የሚያስገኝ የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ከዋልያ ቢራ ጋር ሲፈራረም ለሴቶች ብሔራዊ ቡድን ግን የገበያ ስራ አልተሰራም። በዚህ በኩል ጥያቄ የተነሳበት ፌደሬሽኑ በምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ተክለወይን ተስፋዬ በኩል በአንድ ወቅት መልስ ሰጥቷል “ከአንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር እየተነጋገርን ነው። ስምምነቱ ከዳር ሲደርስ ይፋ እናደርጋለን” በማለት። የምክትል ፕሬዚዳንቱ መልስ ትክክል ከሆነ ፌዴሬሽኑ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ስፖንሰር ማፈላለግ ሥራ ላይ የታየበትን  ክፍተቱን መድፈን ቻለ ማለት ነው። 

የህዝብ ግንኙነት 

ፌዴሬሽኑ ባለፉት 14 ወራት ውስጥ ከሰራው ጠንካራ ስራ ውስጥ አንዱ ሊወደስበት የሚገባው የህዝብ ግንኙነት አሰራሩን ማሻሻል መቻሉ ነው። ቀደም ሲል ፌዴሬሽኑ መረጃዎችን እንደ ግል ንብረቱ ያያቸዋል እየተባለ ይታማ በነበረበት ዘመን ስለ አገሪቱ እግር ኳስ መረጃ የሚፈልግ ጋዜጠኛ ከአንዳንድ የፌዴሬሽኑ ሰራተኞች ጋር በመሞዳሞድ ብቻ የተወሰነ ነበር። ባለፉት 14 ወራት ያስተዋልነው ግን ይህ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ በአወንታዊ መልኩ መቀየሩን ነው። በየቀኑ የሚካሄዱ የፌዴሬሽኑ እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ  እግር ኳሱን የተመለከቱ መረጃዎችን ለጋዜጠኞች በማድረስ በኩል ፌደሬሽኑ ስኬታማ አመትን አሳልፏል ለማለት ይቻላል። በዚህ ረገድ ፌዴሬሽኑ የሰየማቸው አዳዲሶቹ የህዝብ ግንኙነት የሥራ ሃላፊዎች አስተዋጽዎ በግልጽ ታይቷል። መረጃዎችን ለአንባቢያን ለማድረስ በሚጥሩ ጋዜጠኞች ዘንድ ሥራቸው የተወደደላቸው ከመሆኑም በላይ ፌዴሬሽኑን ከህዝብ ጋር ቅርበት እንዲኖረው  አስችለዋል ማለት ይቻላል። 

የዳኞች ጥያቄና የብሄራዊ ሊግ ውድድር

ባብዛኛው በተደራራቢ ውስብስብ ችግሮቹ ዙሪያ ለትችት የተጋለጠው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከላይ ከተጠቀሱት ውጤታማ ሥራዎቹ በተጨማሪ ለብሔራዊ ሊግ እና ፕሪሚየር ሊግ ዳኞች የውሎ አበል ማሻሻያ ማድረግ ችሏል። በዚህ የተነሳም ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያሰሙ የነበሩ ዳኞችን ጥያቄ በመመለሱ እንደ ስኬት ሊታይለት የሚገባ ነጥብ ነው።

በብሔራዊ ሊግ የሚወዳደሩ ክለቦችን ቁጥር በማብዛቱም በኩል ጥሩ ውጤት አስመዝግቧል። ሁሉም ክልሎች በውድድሩ ተሳታፊ የሚሆኑበትን ሁኔታ አመቻችቷል። ይህ መሆኑ ደግሞ በተለይ ወጣት ተጫዋቾች የመጫወት እድልን በየአካባቢያቸው እንዲያገኙ ስለሚያስችል ተጠቃሚ ይሆናሉ። ስንቶቹ እድሉን ተጠቀሙበት ስንቶቹ ታላላቅ ክለቦችስ የብሔራዊ ሊግ ውድድሮችን ተመልክተው ለክለባቸው ተስማሚ የሆኑ ተጫዋቾችን አገኙ? የሚሉትን ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ፌዴሬሽኑ የሚገደድበት አይመስለንም። ምክንያቱም ፌዴሬሽኑ መንገዱን ካስተካከለ በተስተካከለው መንገድ የመጓዝ ድርሻ የሌሎች ነው። ባይሆን ፌዴሬሽኑ ሊጠየቅ የሚገባው የውድድሩ አካሄድ ምን ያህል ስኬታማና ውጤታማ ነው የሚሉትን ጥያቄዎች ነው። ክትትል ያደርጋል ወይ ተብሎ ሊጠየቅ ይገባዋል እንጅ ምን ያህል ተጫዋቾችን ለብሔራዊ ቡድን አበቃህ ተብሎ ሊሆን አይገባም። ይህን በማድረጉም ፌዴሬሽኑ ከሰራቸው ጠንካራ ስራዎች መካከል እንዲካተት አድርጎታል። 

ማስታወሻ፦ ከላይ ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያለፉት 15 ወራት ጠንካራ ስራዎች ስንጠቅስ በእነዚህ ጊዜያት ፌዴሬሽኑ ደካማ ጎኖች አልነበሩትም ለማለት ፈልገን እንዳልሆነ ይታወቅልን። ቀደም ሲልም እንደገለጽነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ስናነሳ ከውድቀቱና ድክመቱ ላይ ብቻ አተኩረን ስለምንነሳ ፌዴሬሽኑ በተለያየ ሁኔታ ያለበትን ሀላፊነት ለመወጣት የሰራቸውን አንዳንድ ጥሩ ጥሩ ሥራዎችን እንዘነጋለን ይህ ሁኔታ ደግሞ ፌዴሬሽኑ ለመልካም ሥራ እንዳይተጋ እንቅፋትን ይፈጥራል ብለን እናምናለን። በዚህ ምክንያትም ፌዴሬሽኑ ከሰራቸው እጅግ በጣም ውስን ጠንካራ ስራዎቹ መካከል መርጠን እንድናቀርብ ወደድን። አንባቢያንም መልካም አስተያየታችሁና ጥቆማችሁን እንድትሰጡን በድጋሚ እንጋብዛለን። 

መልካም ጊዜ ለእግር ኳሳችን!! 

ካሳ ሀይሉ
ኢትዮ ፉትቦል


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!