ፕሪሚየር ሊጉ በሁለተኛ ዙር
መጋቢት 28, 2007

 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንደኛው ዙር ተጠናቆ ሁለተኛውም ከተጀመረ አራት ሳምንታትን አስቆጥሯል። በመጀመሪያው ዙር ከ13 ጨዋታዎች 27 ነጥብ የሰበሰበው ሲዳማ ቡና በሁለተኛው ዙር ግን በአራት ጨዋታ ስምንት ነጥብ  መሰብሰብ ችሏል። ይህ አኃዝ የሚያመለክተው ደግሞ ክለቡ በአማካይ ሁለት ነጥብ መሰብሰቡን ሲሆን በዚህ አካሄዱ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር መቀናቀን የሚያስችለው አካሄድ መሆኑን ነው። 

ፕሪሚየር ሊጉን ለ11 ጊዜያት በማንሳት ሃያልነቱን ያስመሰከረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በውድድር ዓመቱ 17 ጫዋታዎችን ቢያደርግም ከአራት ጎል በላይ የሚያስቆጥርለት አጥቂ ሊያገኝ አልቻለም። ቀደም ባሉት ዓመታት የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ጎል አግቢነት ደረጃ መቆጣጠር ችለው የነበሩት የክለቡ አጥቂዎች እንደ አሸናፊ ሲሳይ፣ ስንታየሁ ጌታቸው ቆጬ፣ አዳነ ግርማ፣ ኡመድ ኡክሪና የመሳሰሉት አጥቂዎችን በማፍራት የሚታወቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ የውድድር ዓመት የክለቡን ከፍተኛ ጎል አግቢዎች ደረጃ የያዙት አዳነ ግርማ እና ምንተስኖት አዳነ ሲሆኑ እነሱም እያንዳንዳቸው አራት አራት ጎል ብቻ ነው ያስቆጠሩት። 
ሁለቱ የፈረሰኞቹ አጥቂዎች ያስቆጠሯቸው ጎሎች ድምር ውጤትም ከንግድ ባንኩ አጥቂ ፊሊፕ ዳውዝ  ብቻውን ካስቆጠራቸው ጎሎች ያነሰ ነው። ክለቡ ባለፈው ቅዳሜ አመሻሽ ላይ ከመከላከያ ጋር ያደረገው ጨዋታ የአጥቂ ችግር እንዳለበት ጥሩ ማሳያ ነበር ማለት ይቻላል ። አጥቂዎቹ ጥሩ የጎል ሙከራ እንኳን ሊያደርጉ አለመቻላቸው ደጋፊውን ጭምር ያበሳጨ ነበር።  ለአጥቂዎች የጎል ድርቅ ምክንያቱ ፈረሰኞቹ ኳስ አስጣይ እንጅ ኳስ አቀባይ የአማካይ መስመር ተጫዋች የሌላቸው መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። በቅዳሜ ምሽቱ ጨዋታም ብቸኛው ጨዋታ አቀጣጣዩ አማካይ ምንያህል ተሾመ በቅጣት አለመሰለፉ ክለቡን ዋጋ እንዳስከፈለው የሚናገሩት ደጋፊዎች፤ በምንያህል ደረጃ እና የጨዋታ ሚና የተቃኘ ተጫዋች በክለቡ አለመኖሩ ደግሞ ችግሩን እንዳባባሰው ይናገራሉ። ፈረሰኞቹ በአሁኑ ሰዓት የአማካይ ተከላካይ ተጫዋቾችን በብዛት በመያዝ ከፕሪሚየር ሊጉ ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ አዲስ ከተገዛው ፋሲካ አስፋውና ከህመሙ አገግሞ መሰለፍ ከጀመረው ተስፋዬ አለባቸው ጨምሮ በአጠቃላይ ከሰባት የማያንሱ ተጫዋቾች በቦታው ይገኛሉ። 

የበርካታ ደጋፊ ባለቤት የሆነው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሰባት ነጥብ መሰብሰብ ቢችልም በአንደኛው ዙር መሰብሰብ ከነበረበት 39 ነጥብ ውስጥ 21 ብቻ በመሰብሰቡ አሁን የነጥብ ድምሩ 28 ላይ ቆሟል። በተለይ ትናንት ምሽት ከዳሽን ቢራ ጋር ባደረገው ጨዋታ በድል ጨርሶ የነጥብ ድምሩን ወደ 30 ከፍ በማድረግ ከመሪዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስና ሲዳማ ቡና ጋር ማቀራረብ ይችላል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ሆኖም 90 ደቂቃ ሙሉ ተጫውቶ አንድ ጎል እንኳ ማስቆጠር ተስኖት ባዶ ለባዶ በመለያየቱ ፈረሰኞቹ እና ሲዳማ ቡና የሚጥሉትን ነጥብ ተመልክቶ በእድሉ መጠቀም ሳይችል ቀርቷል። 

ከኢንተርናሽናል ውድድር ርቆ የቆየው ኢትዮጵያ ቡና በዚህ የውድድር ዓመት የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ወደ ኢንተርናሽናል ውድድር ይመለሳል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም ከዋንጫ ፉክክሩ ወዳ ኋላ እየተንሸራተተ ይመስላል። በርካቶች ለቡና ውጤት ማጣት የአሰልጣኙን አጨዋወት ቢተቹም ሌሎች ደግሞ ቡናም እንደ ፈረሰኞቹ በአንድ ቦታ ላይ የሚሰለፉ በርካታ ተጫዋቾችን መያዙ በአማራጭ እንዲቸገር አድርጎታል ብለው ይናገራሉ። ቅዱስ ጊዮርጊስ በአማካይ ተከላካይ ተጫዋቾች የተሞላውን ያህል ቡና ደግሞ በኳስ አቀባይ ወይም አቀጣጣይ አማካይ ተጫዋቾች ብዛት ከፕሪሚየር ሊጉ ቀዳሚዎቹ ናቸው። ክለቡ በአጠቃላይ 14 በአጥቂ አማካይ መሰመር የሚሰለፉ ተጫዋቾችን የያዘ ሲሆን ይህም ለፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ለእያንዳንዳቸው አንድ አንድ ይደርሳቸዋል ማለት ነው።
ሌላው የክለቡ ድክመት የተባለው ደግሞ ክለቡ ጎሎችን የሚጠብቀው ከአንድ ቢኒያም አሰፋ ብቻ መሆኑ ነው። ቢኒያም  13 ጎሎችን በማስቆጠር የሊጉን ከፍተኛ ጎል አግቢዎች ደረጃ እየመራ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም እሱን ሊያግዝ የሚችል አጥቂ ክለቡ ያለው አይመስልም። እንደ ሻኪሩ አይነት ፈጣን እና ጉልበት ያለው አጥቂ ክለቡ ቢይዝም በአንድ አጥቂ ብቻ የሚጫወት በመሆኑ ክለቡ ጎል ለማግኘት የቢኒያም ጥገኛ አድርጎታል። 

በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር በተካሄዱ አራት ሳምንታት ጨዋታዎች ሁሉንም ጨዋታዎች በማሸነፍ ግዴታውን በሚገባ የተወጣው ብቸኛ ክለብ የጸጋዬ ኪዳነማሪያሙ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው። ንግድ ባንክ በመጀመሪያው ዙር በ13 ጨዋታዎች 16 ነጥብ ብቻ ሰብስቦ የነበረ ቢሆንም በሁለተኛው ዙር ግን በአራት ጨዋታዎች 12 ነጥብ በመሰብሰብ የነጥብ ድምሩን 28 በማድረስ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነጥብ ተስተካክሎ በጎል ክፍያ ደግሞ በልጦ ከሲዳማ ቡና ቀጥሎ ያለውን ደረጃ ይዟል። ሲዳማ ቡና በ35 ነጥብ የሚመራውን ፕሪሚየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሶስት ነጥብ ዝቅ ብሎ ይከተላል።  ከፈረሰኞቹ ቀጥሎ ያለውን ክፍት ቦታም ንግድ ባንክ መያዝ ችሏል። 

በሁለተኛው ዙር ከንግድ ባንክ ጥንካሬ ጀርባ አጥቂው ፍሊፕ ዳውዝ እየተወደሰ ይገኛል። አጥቂው በአራት ጨዋታዎች አራት ጎሎችን በማስቆጠር የጎል ድምሩን 11 በማድረስ ከቢኒያም አሰፋ በሁለት ጎል ብቻ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃን እንዲይዝ አስችሎታል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ከክለቡ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ክለቡ ለተጫዋቾቹ ማበረታቻ ስልጠናዎችን መስጠቱ ታውቋል።  ይህ መሆኑ ደግሞ ተጫዋቾቹ እንዲነሳሱ ሳያደርጋቸው እንዳልቀረ ይታመናል።

ወላይታ ድቻ ፕሪሚየር ሊጉን ከተቀላቀለ ገና ሁለተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኝ ክለብ ቢሆንም እያሳየ ያለው አቋም ግን በፕሪሚየር ሊጉ ለረጅም ዓመታት እንደተጫወተ ነው የሚመስለው። በየዓመቱ የሚካሄደውን የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ቡናን ሁለት ለአንድ አሸንፎ በመብላቱ በዚህ ዓመትም የዋንጫው ተጋባዥ ሆኖ ኤሌክትሪክን ገጥሞ ከፍጹም የጨዋታ ብልጫ ጋር ሁለት ለባዶ አሸንፎ ዋንጫውን ማንሳቱ ይታወሳል። ያንን ጨዋታ ጨምሮ በአጠቃላይ በውድድር ዓመቱ አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ በፕሪሚየር ሊጉ አንጸባርቆ መውጣት የቻለ ተጫዋች ሆኗል። ከብሔራዊ ሊጉ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ አድጎ በመጀመሪያ ዓመት ውድድሩ ምርጥ ብቃቱን እያሳየ ያለው ባዬ ለወለይታ ድቻ ጥንካሬ ተጠቃሽ ሲሆን ሌላው አጥቂ አላዛር   ደግሞ ክለቡን ወደ ታላቅነት እየመራው ይገኛል። የአጥቂዎቹ ጥምረት እና የቡድኑ ውህደት ያለው ጨዋታ ክለቡን ለዋንጫ ከታጩ አምስት ክለቦች አንዱ እንዲሆን አስችሎታል። 

ካሳ ሀይሉ 
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
tekalign [983 days ago.]
 o yaa yaa baye+ashe+alazar=champion

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!