አልጄሪያና ኢትዮጵያ በድጋሚ ተገናኙ
ሚያዚያ 01, 2007

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን በግብጽ ርዕሰ መዲና ካይሮ አካሂዷል። የዓለም አቀፉ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ሴፕ ብላተር እና አዲሱ ተቀናቃኛቸው የ2001 የዓለም ኮከብ ተጫዋቹ ሉይስ ፊጎ በተገኙበት የተካሄደው የካፍ ጠቅላላ ጉባዔ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ አገርን መምረጥ እና በውድድሩ ተሳታፊ የሚሆኑ አገሮችን የማጣሪ የምድብ ድልድል ይፋ ማድረግ ነው። በዚሁ መሰረት የ2012ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ከኢኳቶቶሪያል ጊኒ ጋር በጣምራ ያዘጋጀችውን ጋቦንን ከሁለት ዓመት በኋላ የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ እንድታዘጋጅ አደራውን ሰጥቷታል። 

ቀደም ሲል ውድድሩን ለማዘጋጀት ሰሜን አፍሪካዊቷ ሊቢያ ተመርጣ የነበረ ቢሆንም በአገሪቱ ያለው የጸጥታ ጉዳይ እንኳን 15 የአፍሪካ አገሮችን ለማስተናገድ ለራሷም በሰላም ውላ ማደሯ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ “ውድድሩን ማዘጋጀቱ ይቅርብኝ” ስትል በጊዜ መናገሯ ይታወሳል። ይህን ከግምት ውስጥ ያስገባውና ያለፈው ዓመት የሞሮኮ ስህተት እንዲደገም ያልፈለገው ካፍ የሊቢያን እድል ለማን ልስጥ ብሎ ሲያስብ የሊቢያ ጎረቤት አልጄሪያ እና ጎረቤታማቾቹ ጋቦንና ጋና እኛ አለንልህ ብለው ከተፍ አሉለት። በመጨረሻም አልጄሪያንና ጋናን ለጊዜው አታስፈልጉኝም ሲል ጋቦንን መርጦ አደራውን ሰጥቷታል። ጋቦንም ምስጋና ለሊቢያ ብጥብጥ ይግባና በአምስት ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ታላቁን የአህጉሪቱን የስፖርት ውድድር ልታዘጋጅ እድሉን አግኝታለች። 
Ethiopia The Walyas

ጋቦን ከመመረጧ በፊት የሶስቱም እጩ አገሮች እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተወካዮች እድሉን ቢያገኙ በውድድሩ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ገለጻ አድርገው ነበር። እጣው ከወጣ በኋላ ደግሞ የጋቦኑ ተወካይ “እመኑኝ በ14 ወራት ውስጥ ስታዲየሞቻችንን ለውድድር ብቁ አድርገን እንጠብቃችኋልን” ሲሉ ባለፈው ወር ተካሂዶ የነበረው የኢኳቶሪያል ጊኒው ስህተት እንደማይደገም ማረጋገጫ ሰጥተዋል። 

ካፍ የአዘጋጅ አገር ምርጫን ከመለሰ በኋላ ቀጣዩ ጉዳይ የሚሆነው በመድረኩ የሚካፈሉ 15 እንግዳ ቡድኖችን ለመለየት የማጣሪያ ውድድር ለማድረግ የምድብ ድልድል ማውጣት ስነ ስርዓት ነበር። ከ54 የካፍ አባል አገሮች መካከል ሶማሊያ እና ኤርትራ ብቻ የማይሳቱበት የምድብ ድልድሉ ይፋ ሲሆን ኢትዮጵያ በምድብ አስር ከአልጄሪያ ሌሴቶ እና ሲሸልስ ጋር ተደልድላለች።

የ2015ቱን የአፍሪካ ዋንጫ እንድታዘጋጅ አደራ ተሰጥቷት በኢቦላ ምክንያት አላዘጋጅም ብላ ካፍን አሻፈረኝ ያለችው ሞሮኮ ካፍ በቀጣዮቹ ሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች እንዳላይሽ ቢላትም በዓለም አቀፉ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት ካፍን በማሸነፏ ማጣሪያውን እንድትካፈል ተፈቅዶላታል። በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ቱኒዚያ ሲጫወቱ የእለቱ ዳኛ በፈጸሙት አሳፋሪ ውሳኔ የተበሳጩት የቱኒዚያ ተጫዋቾችና ቡድን መሪዎች ዳኛውን ካልገደልን ብለው ሲያሳድዱት ታይተዋል። ካፍም ቱኒዚያውያንን “ጋጠ ወጥ ተግባር ነው የፈጸማችሁት” ሲል በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ድርሽ እንዳትሉ ብሎ ቢወስንባቸውም የአገሪቱ መንግስት ሳይቀር ካፍን ይቅርታ ጠይቀውት “አንጀቱ አልችል” ብሎ ካፍ ቱኒዚያን በማጣሪያው እንድትካፈል ፈቅዶላታል። 

በዚህም መሰረት ቱኒዚያ በምድብ አንድ ከቶጎ ላይቤሪያ እና ጅቡቲ ጋር ስትደለደል ሌላዋ እምቢተኛ ሞሮኮ ደግሞ በምድብ ስድስት ከኬፕ ቨርዴ ከጎረቤቷ ሊቢያ እና ሳኦ ቶሜ ከምትባለው አገር ጋር ተደልድላለች። በማጣሪያው ምድብ ድልድል የሞት ምድብ የሚል ስያሜ የተሰጠው ናይጄሪያን ግብጽን ቻድንና ታንዛኒያን ያገናኘው ምድብ ሰባት ነው። ሌላው የምድቡ አስገራሚ ደግሞ አስተናጋጇ ጋቦን ለውድድሩ ማለፏን ቀድማ ብታውቅም በምድብ ማጣሪያው መደልደሏ ነው። በምድብ ዘጠኝ ከኮትዲቯር ሱዳን እና ሴራሊዮን ጋር እንድትጫወት ካፍ ምድብ ድልድል አውጥቶላታል። ከ13ቱ ምድቦች አንደኛ የሚወጡት አገሮች በቀጥታ የሚያልፉ ሲሆን ምርጥ ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁ ሁለት አገሮች ደግሞ ሌሎቹ የውቅድድሩ ተሳታፊ ይሆናሉ። ጋቦን አስተናጋጅ በመሆኗ ተሳታፊነቷን በጊዜ አውቃ የተቀመጠች አገር ሆናለች። 

ካሳ ሀይሉ 
ኢትዮ ፉትቦል
ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Ahmed Yimer [1016 days ago.]
 ይሣካላቸው

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!