ፈረሰኞቹ ወደ ላይ ቡናማዎቹ ወደታች የተጓዙበት ሳምንት
ሚያዚያ 05, 2007

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት እና ተስተካካይ ጨዋታዎች ባሳለፍናቸው ሶስት ቀናት አርብ፣ ቅዳሜና እሁድ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ተካሂደዋል። በሶስቱ ቀናት በተካሄዱ አራት ጨዋታዎች አስር ጎሎች ሲቆጠሩ ሶስቱ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው። በእነዚህ አራት ጨዋታዎች ጎል ማስቆጠር ያልቻለው ብቸኛው ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ሲሆን የተሸነፈውም አንድ ለባዶ ነው በአርባ ምንጭ ከነማ። ኢትዮፉትቦል ዶት ኮም እነዚህን አራት ጨዋታዎች ከተለያዩ የመረጃ ምንጮቹ የሰበሰባቸውን እውነታዎችና ጠቃሚ ነጥቦች ከዚህ በታች እንዲህ ያሰፍራቸዋል። 

Addis Ababa Stadium

የአህጉራዊ ውድቀቱን ያስረሳለትን ውጤት ያስመዘገበው ደደቢት

ደደቢት እግር ኳስ ክለብ በኢንስትራክተር ዮሃንስ ሳህሌ እየተመራ ካካሄዳቸው ጨዋታዎች አብዛኞቹን ማሸነፍ ችሏል። ቡድኑ ካሸነፋቸው ወሳኝ ጨዋታዎች መካከል በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የሲሸልሱን ኮት ዲ ኦርን በደርሶ መልስ አምስት ለሁለት ያሸነፈበት ትልቁ ውጤቱ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ወልድያ ከነማን አንድ ለባዶ በማሸነፍ ደረጃውን ያሻሻለበት ውጤትም ተጠቃሽ ነው። ነገር ግን ክለቡ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ሁለተኛ ጨዋታው በናይጄሪያው ዎሪ ዎልቭስ ክለብ በደርሶ መልስ ሁለት ለባዶ ተሸንፎ ከውድድሩ መውጣቱ መጥፎ ውጤት ሆኖ ተመዝግቦበታል። 

ከአህጉራዊ ውድድር በጊዜ በመሰናበቱ “በቡድኑ ተጫዋቾች የራስ መተማመን ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፣ በአገር ውስጥ ውድድሮች ላይም በተከታታይ ነጥብ ሊጥል ይችላል” ተብሎ የተሰጋ ቢሆንም ደደቢት ግን ወደ ወላይታ ተጉዞ ጠንካራውን ወላይታ ድቻን በሜዳው ሁለት ለአንድ አሸንፎ ተመልሷል። ሶስቱም ጎሎች በፍጹም ቅጣት ምት በተቆጠሩበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ለእንግዳው ቡድን የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስና የመብራት ኃይሉ አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሜ ሲያስቆጥር ለባለሜዳዎቹ ደግሞ ባዬ ገዛኸኝ አስቆጥሯል። ሁለቱ አጥቂዎች በእለቱ ያስቆረጠሯቸው ጎሎች በሊጉ የኮከብ ጎል አግቢዎች ፉክክር ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል። ሳኑሜ በአስር ጎል ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ባዬ ደግሞ በዘጠኝ ጎል አራተኛው ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ ይከተላል። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ ጨዋታቸው አዲስ አበባ ላይ ደደቢት ሶስት ለሁለት ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን ለደደቢት ከተቆጠሩት ሶስት ጎሎች ሁለቱን ሳሙኤል ሳኖሜ ማስቆጠሩ ይታወሳል። 

መሪነቱን ያስመለሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ

“ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቅና 12ኛ ሆኖ መጨረስ ልዩነት የለውም” የቅዱስ ጊርጊስ ደጋፊዎች። የፈረሰኞቹ ደጋፊዎች ቡድናቸው ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ማየት የማይፈልጉት ነገር ነው። በተደጋጋሚ ዋንጫ እየበላ የሚያስደስታቸው ክለባቸው በአህጉራዊ ውድድር ባይሳካለት እንኳ በአገር ውስጥ ፉክክር ዘውዱን ማንም እንዲቀማው አይፈልጉም። በዚህ ዓመትም ክለባቸው የሊጉን ዋንጫ ለማግኘት ጠንካራዎቹ ኢትዮጵያ ቡና፣ ደደቢትና ሃዋሳ ከነማ ተዳክመው የታዩበት ዓመት በመሆኑ የድሉን አክሊል በቀላሉ ይቀዳጃል ተብሎ ቢጠበቅም ከወደ ሲዳማ ዞን ሲዳማ ቡና የተባለ ያልታሰበ ቡድን ፈረሰኞቹን ጉድ ሊያደርጋቸው ተቃረበ። ሊጉ ሊጠናቀቅ ስምንት ጨዋታዎች እየቀሩትም ከፈረሰኞቹ በሶስት ነጥብ ላቅ ብሎ ከላይ ሆኖ ያስከትላቸው ጀመር። ለዚህም ነው የክለቡ ደጋፊዎች ቡድናችን ሁለተኛ ሆኖ ከሚያጠናቅቅ ከሊጉ ሳይወርድ 12ኛ ሆኖ ቢጨርስ ይሻላል ሲሉ የተደመጡት። 

ከእለተ ትንሳኤ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በዋዜማው ፈረሰኞቹ የደቡብ ኢትዮጵያውን አዲሱን ተቀናቃኛቸውን በአዲስ አበባ ስታዲየም አስተናገዱ። በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ እንግዳው ቡድን በፍጹም የጨዋታ ብልጫ ፈረሰኞቹን መፈተን ቻለ። ሶስት የመሃል ተከላካዮችን ይዞ የገባው ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ እንደ ተስፋዬ አለባቸው፣ አሉላ ግርማ፣ ዘካሪያስ ቱጂ እና ምንተስኖት አዳነ ያሉትን ተፈጥሯዊ ተከላካይ አማካይ ተጫዋቾችን ይዞ በመግባት በእለቱ ካሰለፋቸው አስር የሜዳ ላይ ተጫዋቾች መካከል ሰባቱ የተከላካይ ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ነበር። በዚህ የተነሳም የፈረሰኞቹ አጥቂዎች ኳስ ለማግኘት የግድ የበሃይሉ አሰፋን እግር ብቻ እንዲጠብቁ አድርጓቸው ታዩ። 

ከእረፍት መልስ የተጫዋች ለውጥ በሁለቱም ክለቦች በኩል ባይደረግም በፈረሰኞቹ በኩል ግን የአጨዋወት ለውጥ አድርገው ነበር የገቡት። ከእረፍት በፊት በግራ አማካይ መሰመር ተሰልፎ የነበረውን ዘካርያስ ቱጂን ወደኋላ በመመለስ ለአማካዩ በሀይሉ አሰፋ የበለጠ የመጫወት ነጻነት ሰጥተው በመግባታቸው ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ደጋግመው መቅረብ ቻሉ። ሙከራቸው ፍሬ አፍርቶም አጥቂዎቹ አዳነ ግርማ እና ካሜሩናዊው ብሪያን ለፈረሰኞቹ ወሳኝ የማሸነፊያ ጎሎችን አስቆጥረዋል። ሲዳማ ቡና በበኩሉ የፈረሰኞቹ ተከላካዮች የሰሩትን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን ቅጣት ምት አንጋፋው ኤሪክ ሙራንዳ ወደ ጎል ቀይሮለታል። ለኤሪክ ጎል መቆጠር የፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ ቸልተኝነት አስተዋጽኦ አድርጓል። ድሉን ተከትሎም ቅዱስ ጊዮርጊስ የመሪነት ደረጃውን በድጋሚ መቆጣጠር ችሏል። 

ክልል ላይ ማሸነፍ የተሳነው ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡና ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ዥዋዥዌ የሚጫወት ክለብ ሆኖ ታይቷል። ቡድኑ በአምስት ጨዋታዎች ማግኘት ከነበረበት 15 ነጥብ ውስጥ ስምንቱን ሜዳ ላይ በትኗል። ከጣላቸው ስምንት ነጥቦች መካከል አምስቱን አዲስ አበባ ላይ ሲሆን ቀሪዎቹን ሶስት ነጥቦች ደግሞ ወደ አርባ ምንጭ ተጉዞ ትናንት በአርባ ምንጭ ከነማ የተሸነፈበት ጨዋታ ነው። የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ጎል አግቢ ደረጃ የሚመራውን ቢኒያም አሰፋን እና 14 አማካይ አጥቂዎችን የያዘው ኢትዮጵያ ቡና ወደ አርባ ምንጭ ተጉዞ ያደረገውን ጨዋታ ጎል ማስቆጠር ተስኖት አንድ ለባዶ ተሸንፎ ተመልሷል። በሳምንቱ ከተካሄዱ አራት ጨዋታዎችም ጎል ያላስቆጠረ ብቸኛው ክለብ ሆኗል። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ ዙር ጨዋታቸው አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ሲጫወቱ ኢትዮጵያ ቡና ሶስት ለአንድ ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን በእለቱ ለአሸናፊው ክለብ ሶስቱን ጎሎች ያስቆጠሩት ቢኒያም አሰፋ ሁለት እና ቀሪዋን ደግሞ ጥላሁን ወለዴ ነበሩ። 

ክልል ላይ ሲጫወት ማሸነፍ አይችልም እየተባለ የሚተቸው ኢትዮጵያ ቡና በትናንቱ ጨዋታም ደካማ ሪከርዱን ማሻሻል ተስኖት ተመልሷል። በዚህ ዓመት እንኳ ክልል ላይ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንዱን ብቻ ነው ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራን። ከዚያ ጨዋታ ውጭ ያሉትን ግን ቢበዛ አንድ ነጥብ ይዞ ከመመለስ የዘለለ ገድል የለውም። 

የሁለተኛው ዙር ግኝት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁለተኛው ዙር የፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብር አዲስ ግኝት ሆኖ የቀረበ ክለብ ሆኗል። በሁለተኛው ዙር ተጫዋች ታዘዋውራለህ ወይ? ተብሎ ተጠይቆ “በሁለተኛው ዙር የሚገዙ ተጫዋቾች በብዛት ከአዲሱ ክለባቸው ጋር በቀላሉ ስለማይዋሃዱ መግዛት አልፈልግም ባሉኝ ተጫዋቾች ብቻ እቀጥላለሁ።” ብሎ ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማሪያም ተናግሮ  ነበር።  አሰልጣኙ እንደተናገረውም በያዛቸው ተጫዋቾች ብቻ ሁለተኛውን ዙር ቢጀምርም አምስቱንም ተጋጣሚዎቹን ያሸነፈ ብቸኛው ክለብ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ሆኗል። ንግድ ባንክ በአምስት ጨዋታዎች 15 ነጥብ መሰብሰብ በመቻሉ ደረጃውንም ከመሪዎቹ በአራት ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ ሶስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አስቸሎታል። 

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትናንት በእለተ ትንሳኤው ወደ ጎንደር ተጉዞ ሙሉ ሶስት ነጥብ ከዳሽን ቢራ ካዝና ዘንቆ የተመለሰ ሲሆን ለንግድ ባንክ አሸናፊነት ወሳኝ የሆኑትን ሁለት ጎሎች ያስቆጠሩት የክንፍ አጥቂዎቹ ኤፍሬም አሻሞ እና ሲሳይ ቶላ ናቸው። በባዶ ከመሸነፍ የዘለለ ሚና ያልነበራትን የዳሽን ቢራ ብቸኛ ጎል ያስቆጠረው ደግሞ አንጋፋው መዳኔ ታደሰ ነው። ዳሽን ቢራ በ18 ጨዋታዎቹ ከአንድ ጎል በላይ ያስቆጠረበት ጨዋታ የለም። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ ዙር ግጥሚያቸው አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ዳሽን ቢራ በይተሻ ግዛው ብቸኛ ጎል አሸንፎ መመለሱ አይዘነጋም። 

ከጨዋታው በኋላ ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም በስልክ አስተያየት የሰጠው የንግድ ባንኩ አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማሪያም “ወሳኝ ነጥብ በማግኘታችን ደስተኛ ነኝ። ተጫዋቾቼ በተለይ የመስመር አጥቂዎቹ በደንብ መግባባት በመቻላቸው ቡድናችን በየጨዋታው እንዲያሸንፍ አስችሎታል” ሲል ተናግሯል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጀመሪያው ዙር የሊጉ መርሃ ግብር 13 ጨዋታዎችን አካሂዶ የሰበሰበው 16 ነጥብ ብቻ ነበር። በሁለተኛው ዙር ግን በአምስት ጨዋታዎች 15 ነጥቦችን በመያዝ ስኬታማ ጊዜ እያሳለፈ ሲሆን አጥቂው ፍሊፕ ዳውዝ በበኩሉ 11 ጎል በማግባት ከመሪው ቢኒያም አሰፋ በሁለት ጎል ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ ይከተላል።  

ካሳ ሀይሉ 
ኢትዮ ፉትቦል


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
mebrate markos [977 days ago.]
 ካሳ ሀይሉ ...gin min aynet keshim gazetegna neh...yethiopia premierlegue nna yebeheraw budin backbone yekilil cluboch nachew betley yedebub(southern) ante keshim...tnish betam tinish ayimiro yizehal..zeregna backward person....

tom [977 days ago.]
 bemitsetut match report lay sle addis ababa budinoch tadalalachu.... lemisale eth bunna ke a.minch.... bunna bichawun yetechawete yimesil sle bunna bicha awerachu... goal agbiwn enkuan altekesachum.... mizanawi hunu guys

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!