አዳማ ከነማ በሜዳው ያለመሸነፍ ሪከርዱን አስጠበቀ
ሚያዚያ 07, 2007

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎች ትናንት በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ተካሂደዋል።  አዲስ አበባ ላይ ደደቢት እና መከላከያ ሊያካሂዱት የነበረው ጨዋታ የመከላከያው አማካይ ተክለወልድ ፈቃዱ በድንገተኛ አደጋ ህይወቱ በማለፉ ምክንያት ለግንቦት 21 መተላለፉ ይታወሳል። ከዚህ ጨዋታ ውጭ ያሉት ቀሪዎቹ ሶስት ጨዋታዎች አዲስ አበባ ስታዲየም፣ አዳማ ላይ እና ወልድያ ላይ ተካሂደዋል። አዳማ ላይ በተካሄደው የአዳማ ከነማ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ባለሜዳው አዳማ ከነማ አንድ ለባዶ አሸንፏል። ለአዳማ ከነማ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኘችዋን ብቸኛ ጎል አጥቂው በረከት አዲሱ አስቆጥሯል።
Adama City

በጨዋታው አዳማ ከነማ በመስመር አጥቂው ታከለ አለማየሁ አማካኝነት ሁለት ያለቀላቸው የጎል እድሎችን አግኝተው የነበረ ቢሆንም ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል። እንግዳዎቹ ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው በሀይል በመጫወትና የመሃል ክፍሉን በመቆጣጠር የተሻሉ እንደነበሩ የኢትዮፉትቦል ዶትኮም ምንጮች ከአዳማ ገልጸዋል። ከጨዋታው በኋላ የሁለቱም ክለብ አሰልጣኞች  በሰጡት ቃለ ምልልስ “ተጋጣሚዎቻችን ከእኛ በተሻለ ወደ ጎል በመቅረባቸውና በሜዳቸው የተጫወቱ በመሆናቸው ውጤቱ ይገባቸዋል” ሲል የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ሲናገር የአዳማ ከነማው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በበኩሉ “ቡድናችን በእለቱ ጥሩ አልነበረም በተለይ በመሃል ክፍሉ። ከእነ ድክመታችንም ቢሆን ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘን በመውጣታችን ደስተኛ ነኝ” ሲል ተናግሯል። አዳማ ከነማ በዚህ ዓመት በሜዳው ያደረጋቸውን ሁሉንም ጨዋታዎች በድል እና በአቻ ውጤት ያጠናቀቀ ሲሆን በሜዳው አንድም ጊዜ የሽንፈትን ጽዋ አልተጎነጨም። መረጃውን ያገኘነው ከኦሮሚያ ቴሌቪዥን ነው። 

ወልድያ ላይ በወልድያ ከነማ እና በሐዋሳ ከነማ መካከል የተካሄደው ጨዋታ ደግሞ በወልድያ ከነማ ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል። የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ባለመሳካቱ ተጨማሪ መረጃ ማቅረብ አልቻልንም። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ ግንኙነታቸው ሐዋሳ ላይ ሃዋሳ ከነማ ሁለት ለአንድ አሸንፎ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በትናንቱ ጨዋታ ወልድያ ቀደም ሲል ደርሶበት የነበረውን ሽንፈት ማወራረድ አስችሎታል። 

ውጤቱን ተከትሎ ወልድያ ከነማ ከነበረው ስድስት ነጥብ ላይ ሶስት በመጨመር የነጥብ ድምሩን ዘጠኝ ቢያደርስም የደረጃውን ግርጌ እንዳስጠበቀ ነው። ሃዋሳ ከነማ በበኩሉ ከነበረበት ሁለት የጎል እዳ ላይ አንድ በመጨመር የጎል እዳውን ወደ ሶስት አሳድጎ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ደረጃ ብቻ ከፍ ብሎ ከሙገር ሲሚንቶ፣ ከኤሌክትሪክና ከወልድያ ከነማ ከፍ ብሎ 11ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። 
አዲስ አበባ ላይ ከአመሻሹ 11 ሰዓት የተካሄደው የኤሌክትሪክና የሙገር ሲሚንቶ ጨዋታ አንድ እኩል በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ሁለቱ ክለቦች እኩል የወጡባቸውን ጎሎች ሁለት የውጭ አገር ተጫዋቾች ማለትም የሙገሩ 10 ቁጥር ጌዲዮን እና የኤሌክትሪኩ 28 ቁጥር ፒተር አስቆጥረዋል።    

ፕሪሚየር ሊጉን ፈረሰኞቹ በ35 ነጥብና በ13 ተጨማሪ የጎል ክፍያ ሲመሩ ሲዳማ ቡና በተመሳሳይ ነጥብ በስምንት የጎል ክፍያ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ዙሩ ሲጀመር ጀምሮ የተካሄዱትን አምስቱንም ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ31 ነጥብና 11 ተጨማሪ የጎል ክፍያ የነሃስ ሜዳሊያውን ደረጃ የዟል። አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻን ያሰናበተው ኢትዮጵያ ቡና በ28 ነጥብ እና በስድስት ተጨማሪ የጎል ክፍያ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ንግድ ባንክ ከሰበሰበው 31 ነጥብ በተጨማሪ 11 ንጹህ የጎል ክፍያ ሲኖረው አጥቂው ፍሊፕ ዳውዝ ደግሞ 11 ጎሎችን በስሙ በማስመዝገቡ ከኢትዮጵያ ቡናው ቢኒያም አሰፋ በሁለት ጎሎች ተበልጦ ሁለተኛ ሆኖ ይከተላል። 

ፕሪሚየር ሊጉ የፊታችን ቅዳሜ፣ እሁድና ሰኞ የሚቀጥል ሲሆን የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም እሁድ ከቀኑ አስር ሰዓት ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ነው። በደቡብ ደርቢ ወላይታ ድቻ እና ሐዋሳ ከነማ የሚያደርጉት ጨዋታም ተጠባቂ ነው። 

ካሳ ሀይሉ 

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!