የአሰልጣኞች ስንብት ምንጩ ምንድን ነው?
ሚያዚያ 07, 2007

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሚወዳደሩ 14 ክለቦች መካከል ስድስቱ ክለቦች አሰልጣኞቻቸውን አሰናብተዋል። ከስድስቱ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ሃዋሳ ከነማ ደግሞ ጭራሽ በዓመት ሁለት ጊዜ አሰልጣኞችን ያሰናበተ ክለብ ሆኗል። ለመሆኑ ክለቦች አሰልጣኞቻቸውን ለማሰናበት ምክንያታቸው ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ይኖርብናል። 

ራሳቸው ባልገነቡት ቡድን የተሰናበቱት ዶሳንቶስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ እንደተለመደው አንድ የውጭ አገር አሰልጣኝ መቅጠሩ ይታወቃል። ክለቡ በአህጉራዊ ውድድሮች የተሻለ ርቀት ለመጓዝ ብሎም የአገሪቱን እግር ኳስ ደረጃ ለቀሪው የአህጉሩ ክፍል ለማስተዋወቅ ካለው ራዕይ የተነሳ በተለያዩ ጊዜያት ክለቡን በውጭ አገር አሰልጣኞች ሲያሰለጥን ታይቷል። ክለቡ በዚህ የውድድር ዓመት መባቻ ጀምሮም  ኔይደር ዶሳንቶስ የተባሉ ብራዚላዊው አሰልጣኝ ቀጥሮ የነበረ ቢሆንም ብራዚላዊውን አሰልጣኝ ዓመት እንኳ ሳያሰለጥኑ ከስራቸው አሰናብቷቸዋል። 
Dosantos

ለአሰልጣኙ ስንብት ከተነሱ ምክንያቶች መካከል ክለቡ ሜዳ ላይ እያስመዘገበ ያለው ውጤት አመርቂ አለመሆንና የጨዋታ ሚናውም ያልታወቀ ዝብርቅርቁ የወጣ በመሆኑ ነው ሲል የክለቡ ልሳን የሆነው ልሳነ ጊዮርጊስ ማስነበቡ ይታወሳል። 

ነገር ግን ክለቡ አሰልጣኙን ከማሰናበቱ በፊት በውድድር ዓመቱ ይዘው የሚቀርቡትን ቡድን አሰልጣኙ በራሳቸው መንገድ እንዲገነቡ እድሉን ሰጥቷቸው ነበር ወይ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለናል። ምክንያቱም አሰልጣኝ ኔይደር ዶሳንቶስ ፈረሰኞቹን ከመረካቸው በፊት ክለቡ የተለያዩ ተጫዋቾችን ገዝቶ ነው የጠበቃቸው። አንዳንድ ተጫዋቾቹን ደግሞ ለምሳሌ እንደ አበባው ቡታኮ ዑመድ ኡክሪና የመሳሰሉት ተጫዋቾች አሰልጣኙ ሳያውቃቸው የተሰናበቱ ተጫዋቾች ናቸው። ክለቡ ባለፈው ዓመት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሳም ሆነ በጥሎ ማለፉ የፍጻሜ ተፋላሚ ሲሆን የተጠቀሱት ተጫዋቾች የነበራቸው ሚና ከፍተኛ እንደነበረ ይታወሳል። ስለዚህ ቅዱስ ጊዮርጊስ የአሰልጣኙን ስንብት በችኮላ የወሰነ ይመስለናል። በነገራችን ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ትናንት ይፋ እንዳደረገው ሆናልዳዊ አሰልጣኝ መቅጠሩ ታውቋል። 

የዳሽን ነገር

ዳሽን ቢራ እግር ኳስ ክለብ መቀመጫውን በአገሪቱ ታላቁ ተራራ ስር ቢያደርግም እያስመዘገበ ያለው ውጤት ግን ከሁሉም ክለቦች ስር እንዲሆን እያስገደደው መጥቷል። ለክለቡ ወጤት መጥፋት በተደጋጋሚ ጊዜ አሰልጣኞች ላይ እጣት ቢቀሰርም የተለየ መፍትሔ ሊገኝለት አልቻለም። ባለፈው ዓመት እንዳደረገው ሁሉ ዘንድሮም ሊጉ ሊጠናቀቅ ስምንት ጨዋታዎች እየቀሩት አሰልጣኝ ሳምሶን አየለን ማሰናበቱን አስታውቋል። ክለቡ ሳምሶን አየለን ከማሰናበቱ ውጭ “ለተሰናባቹ አሰልጣኝ የከፈለው የካሳ ክፍያ እና በምትኩ የቀጠረውን ካሊድ መሃመድን የደመወዝ ማሻሻያ ማድረግ ወይም አለማድረጉን” ይፋ አላወጣም። 
Samson Ayele

ክለቡ በዚህ ዓመት ሳምሶን አየለን ካሰናበተ በኋላ የሳምሶንን ወንበር በጊዜያዊነት እንዲቀመጥበት ምክትል አሰልጣኝ የነበረውን ካሊድ መሃመድን መርጧል። ካሊድ መሃመድ በተጫዋችነት ዘመኑ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ስሙ ተያይዞ የሚነሳ ሲሆን በአሰልጣኝነት የስራ ዘመኑም በይበልጥ ጎልቶ የሚጠቀሰው ኢትዮጵያ ቡናን ከአሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማሪያም ጋር ሆኖ በምክትልነት ሲመራ ነው። ወጣቱ አሰልጣኝ በ2005 ዓ.ም የውድድር ዘመን ኢትዮጵያ ቡናን በምክትልነት ሲመራ ቆይቶ አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማሪያም ወደ ሃንጋሪ ለትምህርት መሄዱን ተከትሎ የክለቡ ተጠባባቂ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ መስራቱ ይታወሳል። ባለፈው የውድድር ዓመትም አሁን የሚያሰለጥነው ዳሽን ቢራ ዋና አሰልጣኙን ካሰናበተ በኋላ በድጋሚ የክለቡ ተጠባባቂ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ መስራቱና ክለቡንም ከወራጅ ቀጠናው ማትረፉ ይታወሳል። በዚህ ዓመት ደግሞ ለሶስተኛ ጊዜ ተጠባባቂ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ የሚሰራበትን እድል አግኝቷል። 

ዳሽን ባለፈው ዓመት በታዕምር ከወራጅ ቀጠናው እንደተረፈው ዘንድሮስ ከመውረድ ይድናል?

የሚፋጀው የቡና ወንበር

ኢትዮጵያ ውስጥ ለአሰልጣኞች ስራ ከባድ ከሆኑ ክለቦች መካከል ፈረሰኞቹና ቡናማዎቹ ቀዳሚዎች ናቸው። ሁለቱም ክለቦች የበርካታ ደጋፊ ባለቤት በመሆናቸው እነዚህ ደጋፊዎች ደግሞ ከቡድኖቻቸው ተጨባጭ ውጤት ማየት ስለሚፈልጉ ክለቦቹን የሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች ቀላል ፈተና አይጠብቃቸውም። 
ለአብነት ያህል አንድ ሁለት ምሳሌዎችን ብናነሳ እንኳ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ስምንት ዓመታት ቅዱስ ጊዮርጊስን የዋንጫ ባለቤት ያደረገው አስራት ኃይሌ በ1992 የውድድር አጋማሽ ላይ ከፈረሰኞቹ ጋር እንዲለያይ የተደረገበት መንገድ አስገራሚ ነበር። አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማሪያም ኢትዮጵያ ቡናን እንዲለቅ የተደረገው የምፈልጋቸውን ተጫዋቾች አታሰናብቱብኝ በማለቱ ነው። 

ከላይ የገለጽናቸው አሰልጣኞች ከተጠቀሱት ክለቦች ጋር እህል ውሃቸው ሲቋረጥ የተሰጣቸው ምክንያት አስገራሚ ነው። በዚህ ዓመት ደግሞ ሁለቱም ክለቦች በተመሳሳይ ወቅት አሰልጣኞቻቸውን አሰናብተዋል። ፈረሰኞቹ ብራዚላዊውን አሰልጣኛቸውን ካሰናበቱ ከሁለት ሳምንታት ቆይታ በኋላ ቡናም ጥላሁን መንገሻን ትናንት አሰናብቶታል። ከኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ቦርዱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ባለፉት ሳምንታት ክለቡ እያስመዘገበ ያለው ደካማ ውጤት ነው። 
Tilahun Megesha

አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻ ኢትዮጵያ ቡናን ከዚህ ቀደምም የማሰልጣን እድል አግኝቶ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን በዚያ ጊዜም በተመሳሳይ በስንብት ነበር ከክለቡ ጋር የተለያየው። ትናንት ከቡና የተሰናበተውን ጥላሁን መንገሻን  እንዲተካ የተመረጠው ደግሞ ምክትል አሰልጣኝ ሆኖ ሲሰራ የነበረው የቀድሞ አማካዩ አንዋር ያሲን ነው። ታላቁ አንዋር በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀው አንዋር ያሲን ትናንት ተጠባባቂ ዋና አሰልጣኝ ተብሎ መሾሙን ተከትሎ በፕሪሚየር ሊጉ ከሚያሰለጥኑ 14 አሰልጣኞች መካከል በቡና ማሊያ ተጫውተው ካለፉ በኋላ አሰልጣኝ የሆኑትን አሰልጣኞች ቁጥር ከፍ አድርጎታል። ታላቁ አንዋርም የሚፋጀውን የቡናን አሰልጣኝነት ወንበር ሊቀመጥበት አደራውን ተቀብሏል። 

ከላይ ከተጠቀሱት ሶስት ክለቦች በተጨማሪ በዚህ ዓመት አሰልጣኞቻቸውን ያሰናበቱ ክለቦች ወልድያ ከነማ ንጉሴ ዓለሙን አሰናብቶ ሰብስቤ ይባስን ተክቷል፤ ደደቢት አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታን አሰናብቶ ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሣህሌን፤ ሐዋሳ ከነማ ታረቀኝ አሰፋን ሸኝቶ ውበቱ አባተን ተቀብሏል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በስራቸው ላይ ቢጫ መብራት የበራባቸው አሰሰልጣኞች መኖራቸውን የኢትዮፉትቦል ዶትኮም ምንጮች ገልጸዋል። እንደ ምንጮቻችን መረጃ በስራቸው ላይ ስጋት ያንዣበባቸው አሰልጣኞች የኤሌክትሪኩ አጥናፉ ዓለሙና የአርባምንጭ ከነማው ጥላሁን ይገኙበታል። የወላይታ ድቻው መሳይ ተፈሪም ቡድኑ በዚህ ውጤቱ የሚቀጥል ከሆነ ለስንብት ባይዳረግ እንኳ ወንበሩ መነቃነቅ እንደሚጀምር ይጠበቃል። 

ክለቦች አሰልጣኞችን ሲቀጥሩም ሆነ ሲያሰናብቱ ምክንያታዊና ፕሮፌሽናል ናቸው ወይስ በአሰልጣኞቹ ስራ ላይ እጃቸውን እያስገቡ የሚበጠብጡ ናቸው? የሚለውን ጥያቄ ከአንባቢያን ጋር ልንወያይበት አቅርበነዋል። 

ካሳ ሀይሉ 
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!