ከአሸዋ ሜዳ እስከ አርጀንቲና
ሚያዚያ 08, 2007

የአሸናፊ ግርማን የእግር ኳስ ታሪክ የሚዳስስ  “ከአሸዋ ሜዳ እስከ አርጀንቲና” ፊልም ትላንት በዋቢሸበሌ ሆቴል ተመርቋል።  በዝግጅቱ ጥሪ የተደረገላቸው  የስፖርት ባለስልጣናት፣ አሰልጣኞች፣ ተጫዋቾች፣ እንዲሁም በርካታ የስፖርቱ ቤተሰቦችን ጨምሮ የቡና እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ዝግጅቱን አድምቀውት አምሽተዋል። ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም ከስፖርት ኮሚሽን የተጋበዙ እንግዶች የመግቢያ ንግግር አድርገዋል። ይህ በኢትዮጵያ በእግር ኳስ ተጫዋቾች ታሪክ ዙሪያ ከተሰሩ ስራዎች በአይነቱ የመጀመሪያ ነው የተባለለት  ፊልም ለሌሎች እስፖርተኞችም ታሪክን መዝግቦ የማስቀመጥ ልምድ እንዲቀስሙ በአርአያነት ሊወሰድ የሚገባው እንደሆነ ሁሉም ተናጋሪዎች ተስማምተውበታል። ፊልሙ አንድ ሰአት ከ14 ደቂቃ የሚፈጅ ሲሆን በዝግጅቱ ለተገኙ ታዳሚዎች በ100ብር ለሽያጭ ቀርቧል። ለህዝብ የሚቀርብበት ዋጋ 30ብር ብቻ ይሆናል።

Ashena Girma


የታሪኩ ባለቤት አሸናፊ ግርማ በበኩሉ ባደረገው ንግግር ከ250ሺ ብር በላይ ወጪ የተደረገበትን ፊልሙን ለማዘጋጀት የረዱትን የተለያዩ ወገኖች አመስግኗል። በጨዋታ ዘመኑ ካሳለፋቸው መልካም ጊዜዎች በኢትዮጵያ ቡና  ያሳለፈው ጊዜ ከልቡ እንደማይጠፋና በእግር ኳስ ህይወቱ ወደከፍተኛ ደረጃ እንዲደርስ የረዳው ክለብ መሆኑን ገልጿል። በተለይ ለአሰልጣኝ ስዩም አባተ ያለውን አክብሮትና አድናቆት ለእሱ ወደተሻለ ደረጃ መድረስ የነበረውን አስተዋጽዎ በማስታወስ ምስጋናውን አቅርቦለታል። 

Aschalew Girma


አሸናፊ በንግግሩ አያይዞም አሁን በመጫወት ላይ ላሉ ተጫዋቾች ካሳለፈው የእግር ኳስ ተመክሮው ተነስቶ  ምክሩን ለግሷል። ተጫዋቾች አሰልጣኞቻቸውን መስማት እንዳለባቸው ትእግስት እንዲኖራቸው አፍለኛነታቸውን ገርተው ወደተሻለ ደረጃ ለመድረስ ከቡድን አጋር ተጫዋቾች እንዲሁም ከመላው የቡድናቸው አባላት ጋር ተስማምተው ተደማምጠው በዲሲፕሊን መስራት ቡድናቸውን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስንም ወደተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል የሚያስችል እንደሆነ ምክሩን ሰጥቷል። በንግግሩ መጨረሻም ለዚህ ክብር ያበቃውን ፈጣሪው እግዚአብሄርን እንዲሁም  የፈጣሪውን እናት ድንግል ማርያምን ከትቢያ ያነሳችኝ እሷ ናት በማለት እንባ እየተናነቀው በማመስገን ንግግሩን ጨርሷል።

ለዝግጅቱ ታዳሚዎች ፊልሙ ከመታየቱ በፊት አርጀንቲና ላይ ለብሶት የተጫወተበትን ማሊያ ለጨረታ ቀርቦ ከብዙ የዋጋ ፍልሚያ በኋላ አቶ ወርቅሸት በቀለ በ50ሺ ብር ጨረታውን አሸንፈው ወስደውታል። አቶ ወርቅሸት በቀለ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ቡና እያስገነባ ባለው የስፖርት አካዳሚ 130ሺ ብር በማውጣት አንድ የተጫዋቾች ማረፊያ ክፍል በስሙ እንዲገነባና እንዲሰየምለት ማድረጋቸው ይታወሳል። 

ጨረታውን ተከትሎ ለፊልሙ ስራ መሳካት አስተዋጽዎ ላደረጉ ሰዎች የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል። ከምስክር ወረቀት ከተሰጣቸው ተጫዋቾች የቀድሞና የአሁን ተጫዋቾች ዮርዳኖስ አባይ፣አሰግድ ተስፋዬ፣ዳዊት እስጢፋኖስ እንዲሁም አዳነ ግርማ ይገኙበታል።ከአሰልጣኞች ስዩም አባተ፣አስራት ሀይሌና የድሬዳዋው ጥላሁን የምስክር ወረቀቱ ሲሰጣቸው ከጋዜጠኞች በኢትዮጵያ ስለቀደምት እግር ኳስ ታሪክ ብዙ እውቀት ያለው  ገነነ መኩሪያ ሊብሮ፣ በልዩ የትረካ ችሎታው የሚታወቀው ፍቅር ይልቃል እንዲሁም  የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ከሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ የመረጃ ቋት እየተባለ የሚታወቀውን ደበበ እንግዳወርቅውን የጨመረ ነበር። ምስጋናው   የቡና እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊስ አስጨፋሪዎችን አዳነንና አቼሎንም አካቷል። ከደጋፊዎች ታዋቂውን የእግር ኳስ ተመልካች የኤሌክትሪክ ደጋፊ የሆነውን በቀለ ኮረንቲንም ጨምሯል። በተጨማሪም ለፊልሙ መሳካት አስታዋጽዎ ያደረጉ ሌሎች በርካታ ድርጅቶችና ግለሰቦችም የምስጋና የምስክር ወረቀቱ ደርሷቸዋል።

በመጨረሻም ፊልሙ ከመታየቱና የፊልም ምረቃው ሥነስርአት ከመጠናቀቁ በፊት ቀደም ብሎ አሸናፊ ግርማ ያዘጋጀውን ልዩ የዋንጫ ሽልማት ለአሰልጣኝ ስዩም አባተና ድሬዳዋው አሰልጣኙ ለነበረው  ጥላሁን መገኒሾ አበርክቷል። ለአሰልጣኝ ስዩም አባተ ሽልማቱ ሲሰጥ በዝግጅቱ የታደመው የስፖርት ቤተሰብ በሙሉ  ከመቀመጫው በመነሳት አድናቆቱን ገልጾለታል። ለአሸናፊ ግርማ በበኩሉ አሁን እያሰለጠነው በሚገኘው የአበበ በቂላ የጤና ቡድን የ7ሺ አምስት መቶ ብር ስጦታ ተበርክቶለታል።

ኢትዮ ፉትቦል


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
girmasahle [974 days ago.]
 it is a good work this is the first job for all ethiopian football history we hav not a vidio former footballer hisory thx ashanafi and others

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!