የግብ ጠባቂው ተደጋጋሚ ስህተት ንግድ ባንክን ዋጋ አስከፈለው ነጥብ ተጋርቶ ወጣ
ሚያዚያ 10, 2007

የዛሬውን ጽሁፋችንን ከዓመታት በፊት በተነገረ ታሪካዊ አነጋገር እንጀምረዋለን። “ምርጥ በረኛ ካለህ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን የማንሳት እድልህ 50 በመቶ ከፍ ይላል” ስኬታማው የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ የነበሩት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በ2003 እ.ኤ.አ ከሪያል ማድሪድ ጋር በሜዳቸው ተጫውተው አራት ለሶስት ሲያሸነፉ የተናገሩት። በወቅቱ የእንግሊዙ ክለብ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ መውጣት ቢችልም ግብ ጠባቂው ፋቢያን ባርቴዝ በሰራቸው ግልጽ ስህተቶች የተነሳ ብራዚላዊው ሮናልዶ ሉይስ ናዛሪዮ ዴሊማ በማንቸስተር ዩናይትድ መረብ ላይ ያሳረፋቸው ሶስት ጎሎች ማንቸስተር ዩናይትድን ወደ ግማሽ ፍጻሜው እንዳያልፉ ያደረጉ ነበሩ። 
የግብ ጠባቂያቸው ምህረት አልባ ስህተት አንጀታቸውን ያሰረረባቸው ሰር አሌክስ በጊዜው የወሰዱት እርምጃ ፈረንሳያዊውን ቀዥቃዣ ግብ ጠባቂ አሰናብተው አሜሪካዊውን ግብ ጠባቂ ቲም ሃዋርድን ማስፈረም ነበር። አሜሪካዊው ግብ ጠባቂም የላንክ ሻየሩን ክለብ እንደተቀላቀለ በእንግሊዝ ኮምዩኒቲ ሼልድ ዋንጫ ከአርሴናል ጋር በተደረገው ጨዋታ ክለቡን የዋንጫ ባለቤት ማድረግ ቻለ። ወዲያውኑ ስኮትላንዳዊው አሰልጣኝ “አምና በክለባችን ቋሚ ብረቶች መሃል ቲም ሃዋርድ ቢቆም ኖሮ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ማንም አይወስድብንም ነበር” ሲሉ ተናገሩ። 
Comercial Bank

ከላይ የተቀመጠውን ታሪካዊ ንግግር እንድንጠቀም ያስገደደን ክስተት የተፈጠረው ትናንት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አርባ ምንጭ ከነማን እስከ 75ኛው ደቂቃ ሁለት ለባዶ እየመራ በ15 ደቂቃ ውስጥ ሁለት ጎል እንዲቆጠርበት ምክንያት የሆነው ግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ የሰራው ስህተት ነው። ማራኪ ጨዋታን የሚጫወት ቡድን በመገንባት ተለይቶ የሚታወቀው አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማሪያም የቡድኑን ተጫዋቾች ድካም የሚያገናዝብ ግብ ጠባቂ ኖሮት አያውቅም ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያው ዙር ውድድር በ13 ጨዋታዎች 16 ነጥቦችን ብቻ መሰብሰቡ ይታወሳል። ለዚህ ደካማ ውጤቱ ተጠቃሹ ደግሞ ግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ ሲሆን በተለይም ቡድኑ በአንድ ወይም ሁለት ጎሎች ልዩነት ተጋጣሚውን የሚመራ ከሆነ ሰዓት በማባከን ውጤት አስጠብቆ ጨዋታውን ለመጨረስ የሚያደርገው ሙከራ በተደጋጋሚ ጊዜ ዋጋ ሲያስከፍል ይታያል። በተለይ ንግድ ባንክ በአዲስ አበባ ስታዲየም አዳማ ከነማን አንድ ለባዶ እየመራ በ94ኛው ደቂቃ አቻ የሆነበት ጨዋታ ተጠቃሽ ነው። 

በአዳማ ጨዋታ የሰራው ስህተት ዋጋ ከማሰከፈሉ በፊት የእለቱ ዳኛ ከተደጋጋሚ ሰዓት የማባከን እርምጃው እንዲታረም ቢነግሩትም አልሰማ በማለቱ የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ አሳይተውት ነበር። ከዚያ ጨዋታ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ እና ከአዳማው ጨዋታ ቀጥሎ ባሉት ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ጠባቂው በተመሳሳይ ስህተት ቡድኑን ዋጋ ሲያስከፍልና በግሉም የማስጠንቀቂያ ካርድ ሊመለከት ችሏል። 

በሁለተኛው ዙር የፕሪሚየር ሊግ ውድድር መርሃ ግብር ግን ክለቡ በተከታታይ አምስት ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ በመታየቱ ቡድኑ ካለፉት ስህተቶቹ የተማረ መስሎ ነበር። ሆኖም በትናንቱ የአርባምንጭ ከነማ ጨዋታ በፍሊፕ ዳውዝ ተከታታይ ጎሎች መምራት ቢችልም በ15 ደቂቃዎች ውስጥ እንግዳው ቡድን በአማኑኤል ጎበና እና ተሾመ ታደሰ ጎሎች ነጥብ ተጋርተው ሊወጡ ችለዋል። ለአርባምንጭ ከነማ ነጥብ ተጋርቶ መውጣትም የንግድ ባንኩ ግብ ጠባቂ ዳዊት አሰፋ ተጠያቂ ሆኗል። 

ዳዊት አሰፋ የቱንም ያህል ስህተት በመስራቱ ቡድኑን አሸናፊ እንዳይሆን አድርጓል ተብሎ ቢተችም በእለቱ ያሳየው ብቃት ግን የሚያስወድሰው እንደነበር የሚናገሩ ደጋፊዎች አሉ። ሆኖም ግን ብቃትና ችሎታው ሳያንሰው በቸልተኝነትና ሰዓት ለማባከን በሚያደርገው ያልተገባ ተደጋጋሚ ጥረት በቡድኑ ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳረፍ እስካላቆመ ድረስ የንግድ ባንክ ለዋንጫ መፎካከር የማይታሰብ ይመስላል። በግብ ጠባቂው ስህተት ዋጋ የከፈለው ንግድ ባንክ በ32 ነጥብና 11 ተጨማሪ ጎሎች ሶስተኛ ደረጃን ሲያስጠብቅ በዕለቱ ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረው አጥቂው ፍሊፕ ዳውዝ ደግሞ በሁለተኛው ዙር ውድድር አንድም ጎል ማስቆጠር ካልቻለው ቢኒያም አሰፋ እኩል በ13 ጎል የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ጎል አግቢነት ደረጃን መምራት ችሏል። 

በመጀመሪያው ዙር የሊጉ መርሃ ግብር አርባ ምንጭ ላይ ንግድ ባንክን ሁለት ለአንድ አሸንፎ የነበረውና ትናንት ከመሪነት ተነስቶ ሁለት እኩል የወጣው አርባምንጭ ከነማ በ25 ነጥብና በሁለት ንጹህ ጎል ሰባተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። ሊጉ ዛሬም ቀጥሎ ሲውል መከላከያ ከአዳማ ከነማ ከቀኑ አስር ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ። ነገ ደግሞ ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ደደቢትን ሲያስተናግድ አሰላ ላይ ደግሞ ሙገር ሲሚንቶ ዳሽን ቢራን ይገጥማል። ታላቁ የደቡብ ደርቢ የወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከነማ ጨዋታ ሰኞ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ሶዶ ላይ ይካሄዳል። የመውረድ ስጋት ያንዣበበባቸው ወልድያ ከነማ እና ኤሌክትሪክ ደግሞ ወልድያ ላይ ሰኞ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት እንደሚጫወቱ የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል። 

የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገ ከቀኑ አስር ሰዓት ካምቦሎጆ ላይ የሚያካሂዱ ይሆናል። የሊጉ መሪዎችና ያለፈው ዓመት አሸናፊዎቹ ፈረሰኞቹ የ80ኛ ዓመት የምስረታ በዓላቸውን ለማክበር እየተዘጋጁ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ታላቁን ደርቢ ማካሄዳቸው ውጤቱን አጥብቀው እንዲፈልጉት ያደርጋቸዋል ተብሏል። 

ካሳ ሀይሉ 
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Biniam [973 days ago.]
 your article is not true b/c yesterday i was there, watching the game Arbamnch is best team in all ascpect CBE is not good at all, but Philip Douzi the only man at filed best on taking deadly chances , so why the goal keeper is the only one who blame for the result kasesh? CBE is not playing best football at all only they want to win the coach also need that never in my life he playing for beautifully football ok.

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!