ለዳኝነቱ ችግር ተጠያቂው ማነው ?
ሚያዚያ 12, 2007

በተወዳጅ እግር ኳስ ጨዋታም ሆነ በሌሎች ውድድሮች የዳኞች ውሳኔ ለውጤት ማማርና በሰላም መጠናቀቅ ወሳኝ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ 
Referee who is responsible

በተለይ በእግር ኳስ ጨዋታ የውድድሩን ውጤት በመወሰን እና ጨዋታውን ለማሳመር የዳኞች ውሳኔ አሰጣጥ ትልቁን ድርሻ ይወጣል፡፡ 

በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ውስጥ አወዳዳሪዎቹ አካላት የዳኞችን ብቃት ለማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ የተሻለ ውድድር ለማየት እና አወዛጋቢ ነገሮችን ለመቀነስ ተግተው ይሰራሉ፡፡ ለሊጉ ማማር እና የተከታይ ቁጥር ለማብዛት ዋናው መንገድ የዳኝነት ጉዳይ መሆኑን በማወቅ ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ፡፡ ለምሳሌ የእንግሊዝ እግር ኳስ ማኅበር ለእያንዳንዱ ዳኛ ትኩረት በመስጠት ከአሰልጣኞች፣ ከተመልካቾች፣ ከሚዲያ ለሚደርስባቸው ጫና ከጎናቸው በመቆም ይከላከላል እርምጃ መውሰድ ካስፈለገም ይወስዳል፡፡ ሲያጠፉም ቆንጠጥ የሚያደርግ ቅጣት ይቀጣል ይህም ሆኖ ከሙያው ክብደትና ፈጣን ውሳኔ ከመጠየቁ አንፃር አልፎ አልፎ ስህተቶች አይሰሩም ማለት አይደለም፡፡ 

New Referee Dressing Style

ወደሀገራችን ስንመለስ በተለያዩ ጊዜያት ዳኞች የውድድሮችን ውጤት ይቀይራሉ ለውዝግብና ለረብሻ ምክንያት ይሆናሉ ያጠፋውን ትተው ያላጠፋውን ይቀጣሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ከፍ ያለ ቅጣት የሚጣልባቸው ተመልካች በብዛት በሚገባባቸው ታላላቅ ደርቢዎች ብቻ ነው፡፡ 
 
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከረጅም ዓመታት ጀምሮ ዳኞችን ለመቅጣትም ሆነ ለመሸለም የሚዲያውን እና የተመልካችን ጩኸት በማዳመጥ እንጂ የራሱ የሆነ ወጥ አሰራር ያለው አይመስልም፡፡ ለዳኞቹም ቢሆን የሚሰጠው ከለላ የለም በርካታ ዳኞች በሚደርስባቸው ዘለፋ፣ ማስፈራራት፣ በቤተሰባቸው ላይ በሚደርሰው ዛቻ፣ በማህበራዊ ህይወታቸው ላይ በደረሰው ተፅዕኖ ከሙያው ራሳቸውን አግለዋል፡፡

ለሙያው ካላቸው ፍቅር እና እንደተጨማሪ ሥራ ያዩት ጥቂት ዳኞችም ቢሆኑ በተለያዩ መድረኮች የአበል ጭማሪ እና ሌሎች ችግሮቹን ሲያነሱ እንጂ ከሙያው ውጪ የሆኑ ጓደኞቻቸውን ችግር በማንሳት ነገ ለኔ ሲሉ አላስተዋልንም እውነታው ግን ውድድር ዳኝተው ከጨረሱ በኋላ ተደብድበው በአካላቸው ላይ ከፍተኛ እና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው እርም ዳኝነት ብለው ሲያቆሙ ፌዴሬሽኑም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ከጎናቸው አልቆሙም የሙያ አጋሮቻቸውን ድጋፍም አላገኙም ታዲያ ዳኞቻችን ታላላቅ ደርቢዎችን እናጫውትም ቢሉ ሲወሰንባቸው ለአምላካቸው ፈጣሪ አውጣኝ እነዚህን ቡድኖች እኩል ለእኩል አስወጣልኝ እስከ ማለት ቢደርሱ ጨዋታውን ቢያበላሹ የማይሰጥ ሪጎሬ ሰጥተው በሚቀጥለው ጨዋታ ለማካካስ ሪጎሬ ቢከለክሉ የጨዋታውን ውጤት ቢቀይሩ ሜዳ ውስጥ እና ከሜዳ ውጪ አምባጓሮ ቢያስነሱ ተጠያቂው ማነው? ከጨወታው በፊት እና ከጨዋታ በኋላ አጥንት የሚሰብር ስድብ የሚሰድባቸው ተመልካች ነው? ሜዳ ውስጥ የሚገፈትሯቸው እና ደጋፊ የሚያነሳሱባቸው ተጨዋቾች እና አሰልጣኞች ናቸው? ትምህርት፣ ድጋፍ፣ ስልጠና፣ በቂ ክፍያ፣ ጥበቃና ከለላ የማይሰጣቸው ፌሬዴሽን ነው? ልክ እደኔ ለተወሰኑ ጨዋታዎች ትኩረት በመስጠት ችግራችሁ ምንድን ነው ሳይል የሚወርድባቸው ሚዲያ ነው? ብቃታቸውን ካለማሻሻል፣ ሆን ብለው ውጤት ለመቀየር፣ የደጋፊውን ጫና መቋቋም ባለመቻል፣ ቂም በቀል እና ድጋፍ ይዘው በመግባት፣ ጨዋታውን የሚቀይሩ ዳኞች ናቸው? ለመሆኑ ለሀገራችን የእግር ኳስ ዳኝነት ተጠያቂው ማነው? 

ፈለቀ ደምሴ 
ለኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም 

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!