በሃይሉ አሰፋ-ቱሳ- ኮከብ በሆነበት ጨዋታ ለፈረሰኞቹ ድልን አስገኘ
ሚያዚያ 12, 2007

ሚያዝያ 11 በእለተ ዳግሚያ ትንሳዔ ብቸኛውና አንጋፋው አዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ ሰባት ሰዓት በፊት ጀምሮ በበርካታ ወጣቶች ተከቧል። ለወጣቶቹ ካምቦሎጆን መክበብ ምክንያቱ ደግሞ የአገሪቱ ታላቁ ደርቢ ከቀኑ አስር ሰዓት ላይ የሚካሄድ መሆኑ ነው። በእለቱ ሁለቱ ሃያላን ክለቦች የፕሪሚየር ሊጉን 19ኛ ሳምንት መርሃ ግብራቸውን ለማካሄድ በተያዘላቸው ቀነ ቀጠሮ መሰረት ቡድናቸውን አደራጅተው ሰዓቱን እየተጠባበቁ ነው። ከጨዋታው በፊት ግን ዛሬም ምፍትሔ ያልተገኘለት የስታዲየም መግቢያ ጉዳይ እስከ ቀኑ 9፡30 እና ከዚያ በላይ ሲያወዛግብ ቆይቶ ካምቦሎጆ መያዝ የሚችለውን ያህል ተቀብሎ መያዝ አልችል ያላቸውን ደግሞ ስለተፋቸው በሩ ተዘጋ። በግምት ከአንድ ሺህ በላይ ተመልካች የስታዲየም መግቢያ ቦታ ጠፍቶ ወደ መጣበት ሲመለስ ሁለቱ ክለቦች ሲገናኙ ለጸጥታ ሲባል በካታንጋ በኩል የሚተወው ባዶ ቦታ ግን መፍትሔ ጠፍቶለት ከ200 የማያንሱ ወንበሮች ትናንትም የእለቱን ጸሀይ ሲሞቁ ታይተዋል።  

Coffee Vs St.George


ቅድመ ጨዋታ

አሁንም ትክክለኛውን አኃዛዊ መረጃ በማስረጃ አስደግፎ ማቅረብ አስቸጋሪ በመሆኑ በግምት ለመናገር እንገደዳለን። በግምት ከ30 ሺህ በላይ የሚሆን የአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ነዋሪ የፈረሰኞቹንና የቡናማዎቹን ጨዋታ ለመመልከት ስታዲየም ገብቶ የጨዋታውን መጀመር ይጠባበቃል። የደጋፊዎች ህብረ ዜማ እና አንደኛው ሌላኛውን የሚተነኩስበት ተንኳሽ ቃላት እንዳሉ ሆኖ ቡድኖቻቸውን ማበረታታታቸው እየተሰሙ ቀጠለ። በዚህ መሃል በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክለው በዳኝነት የተመረጡትና ካሜሩንና ጋቦን ያካሄዱትን ጨዋታ የመሩት ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ከእነረዳቶቻቸው የሜዳውን ለጨዋታ ብቁ መሆን ለማረጋገጥ ከመልበሻ ክፍል ወጡ። ልክ አውሮፓውያን ሊጎችን ስንመለከት የጨዋታው ዳኞች በሙሉ ልብስ “ሽክ” ብለው ሜዳውን እንደሚዞሩት የእነ ባምላክ ጉብኝትም ያልተለመደና አስገራሚ ነበር ማለት ይቻላል። 
Referee With New Dressing Code

ተመሳሳይ ሙሉ ልብስ ለብሰው የቅድመ ዳኝነት ስራቸውን ያከናወኑት አራቱ ዳኞች ከስታዲየም የጠበቃቸው አጸፋዊ መልስ ግን የተዘበራረቀ ነበር። ከስድስት ወራት በፊት ሁለቱ ታላላቅ ክለቦች ሲጫወቱ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የሰጡትን  ፍጹም ቅጣት ምት ያስታወሱት የቡና ደጋፊዎች ዳኛውን ከጸያፍ ስድብ እስከ ተቃውሞ የደረሰ አቀባበል ሲያደርጉላቸው በተቃራኒው የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ደግሞ ዳኛውን በእልልታና በጭብጨባ ነበር የተቀበሏቸው። 

ሁለቱም ቡድኖች በእለቱ የሚጠቀሙባቸውን ተጫዋቾች ሜዳ ላይ አስገብተው ልምምድ ከሰሩ በኋላ ወደ ጨዋታ ሲገቡ 22ቱም ተጫዋቾች ከጀርባው “ስምንት ቁጥር” የተጻፈበትና ከፊት ለፊት ደግሞ የሰው ምስል የተለጠፈበት ማሊያ ለብሰው ገቡ። የሁለቱም ቡድኖች ቋሚ ተሰላፊዎች ለብሰውት የገቡት ማሊያ በቅርቡ በድንገተኛ የመኪና አደጋ ህይወቱ ያለፈውን የመከላከያውን ተክለወልድ ፈቃዱን ለማሰብ የተዘጋጀ የሀዘን መግለጫ ማሊያ ነበር። ቁጥሩ ተጫዋቹ በተጫዋችነት ዘመኑ ለመከላከያ ሲጫወት የሚለብሰው ቁጥር ነበር። 

Teklewold Fekadu Remembered


ይህ ድርጊት በተለይ በስፖርታዊ ሜዳዎች ላይ መታየቱ “እውነትም እግር ኳስ የሰላም ሜዳ ነው” የሚባለው አባባል ትክክል መሆኑን ያሳየ በመሆኑ ዝግጅቱን ያስተባበሩ አካላትን ማመስገን ፈለግን። ዝግጅት ክፍላችንም ለተክለወልድ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም የክለብ አጋሮቹ መጽናናትን እንመኛለን። 

ጨዋታው ተጀመረ

የመስመር ተከላካዩን ዴቪድ በሻህን በጉዳት ያጣው ኢትዮጵያ ቡና በሶስት ተከላካዮች ብቻ የገባ ሲሆን በአንጻሩ የሊጉ መሪዎች በቀደመው አራት ሶስት ሶስት አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን አምበላቸውን ደጉ ደበበን ተቀያሪ ወንበር ላይ አስቀምጠው ነበር ሜዳ የገቡት። ሁለቱ ክለቦች ሲገናኙ የመፈራራት ስሜት ስለሚያድርባቸው ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመቅረብ ይፈራራሉ እየተባሉ ቢተቹም ጨዋታው በተጀመረ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የቡናዎቹ መስዑድ መሃመድና አስቻለው ግርማ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር። 

በፈረሰኞቹ በኩል በቅርቡ ቡድኑን የተቀላቀለው ዩጋንዳዊው አጥቂ ብሪያን በቡና ተከላካዮች ላይ ያደረገው ጫና ደጋፊ ማጣቱ እንጅ በርካታ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ የጎል እድልችን መፍጠር ችሎ ነበር። በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም በኩል ለጎል የቀረቡ እድሎችን ፈጥረው የነበረ ቢሆንም በተለይ የቡናዎቹ ተከላካዮች አህመድ ረሽድና ኤፍሬም ወንድወሰን የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂዎችን ተደጋጋሚ የጎል ሙከራ በማክሸፍ ስራ በዝቶባቸው ታይተዋል። ለወትሮውም በጥንካሬው የሚታወቀው የቡና አማካይ መስመር በትናንቱ ጨዋታም በተጋጣሚው ላይ የበላይነትን መውሰድ ችሎ ታይቷል። 

ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሲጀመር በቡና በኩል አስቻለው ግርማ በጉዳት ተቀይሮ ሲወጣ ተከላካዩ ሮቤል ግርማ ቦታውን እንዲረከብ ሲደረግ በፈረሰኞቹ በኩል ደግሞ ተከላካዩ አሉላ ግርማ በደረሰበት ከባድ ጉዳት ወደ ህክምና በመወሰዱ ቦታውን አለማየሁ ሙለታ እንዲረከብ በማድረግ ነበር የተጀመረው። ከአስቻለው መውጣት በኋላ ፍጥነቱ የቀነሰው የቡና አጥቂ መስመር በቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካይ ክፍል በቀላሉ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል። በአንጻሩ በበሀይሉ አሰፋ የሚመራው የጊዮርጊሶች አጥቂ መስመር በተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ዙሪያ ሲፈነጩበት ታይተዋል። 

“የነብርን ጅራት አይይዙም ከያዙም አይለቁም” እንዲሉ አንዴ የጀመሩትን የማጥቃት እንቅስቃሴ አጠናክረው የቀጠሉት የፈረሰኞቹ ፊት አውራሪዎች በዩጋንዳዊው ብሪያን አማካኝነት የመጀመሪያ ጎላቸውን አስቆጠሩ። 
ብሪያን ጎሏን ሲያስቆጥር “የኢትዮጵያውያን ግብ ጠባቂዎች የስራ ድርሻ ምንድን ነው?” የሚለው ተደጋጋሚ ጥያቄ በቡናው ጌቱ ተስፋዬ ላይ የሚያስነሳ ነበር። ብሪያን ኳሷን ከበሀይሉ አሰፋ ስትሻገርለት ነጻ ሆና ቢያገኛትም ወደ ጎሉ ሲልካት ግን የቡናውን በረኛ እንድትፈትን አስቦ አልነበረም ማለት ይቻላል። ማንኛውም ግብ ጠባቂ በቀላሉ ሊይዛት የምትችለዋ ኳስ ከጌቱ ጀርባ የተወጠረው መረብ ብቻ ነበር ሊይዛት የቻለው። 

ከመጀመሪያዋ ግብ መቆጠር በኋላ ይበልጥ ተጭነው የተጫወቱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሁለተኛ ጎላቸውን ለማግኘት በርካታ ደቂቃዎችን መጠበቅ አላስፈለጋቸውም ነበር የተጋጣሚዎቻቸውን ተከላካይ ክፍል ድክመት እንጅ። ድሮም ለስህተት ቅርብ የሆነው የቡናማዎቹ የተከላካይ ክፍል በትናንቱ ጨዋታ ደግሞ በተለይም በበሀይሉ አሰፋ ወይም ቱሳ ይበልጥ ከባድ ፈተና በዝቶበት አምሽቷል። በእለቱ ኮኮብ ሆኖ ያመሸው በሀይሉ አሰፋም ለቡድኑ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥሯል። 

Behailu Assefa Celebrating his Goal


የቡና የተከላካይ ክፍል በተለይ ኤፍሬም ወንድወሰንና ወጣቱ አህመድ ረሽድ ወይም ሽሪላው በእለቱ ጠንካሮች ሆነው ቢያመሹም በተለይ ተቀይሮ የገባው ሮቤል ግርማ እና ግብ ጠባቂው ጌቱ ተስፋዬ የሚሰሩትን የማያውቁ ሆነው ነበር ያመሹት። 

ውጤቱን ለመቀየር ከፍተኛ ጉጉት የነበረው አዲሱ የቡና አሰልጣኝ አንዋር ያሲንም መስዑድ መሃመድን እና ኤሊያስ ማሞን አስወጥቶ ሚኬኤል በየነን እና ጥላሁን ወልዴን ቢያስገባም በሩዋንዳዊው ሮበርት ኦዶንካራ የታጠረውን የፈረሰኞቹን የጎል ድንበር አሳልፎ ጎል የሚያስቆጥርለት አጥቂ ባለማግኘቱ ጎምዛዛውን የደርቢ ሽንፈት ሊጎነጭ ተገድዷል። 

የእለቱ ምርጦች

በአገራችን በየጨዋታዎቹ የሚካሄዱ አኃዛዊ መረጃዎችን የሚያጠና ቴክኖሎጅ የለም። በዚህም ምክንያት በጨዋታዎች የሚታዩ ድክመቶችንና ጥንካሬዎችን ለማሳየት የምንጠቀመው ተጫዋቾቹ በእለቱ የሰሯቸውን ስራዎች በማየት ብቻ ነው። በትናንቱ ጨዋታ ከታዩት እንቅስቃሴዎች መካከል በሁለቱም ቡድኖች በኩል ለክለቦቻቸው ከፍተኛ ግልጋሎት የሰጡትን ተጫዋቾች ለማሳየት እንሞክራለን። 

በፈረሰኞቹ በኩል የመስመር አጥቂው በሀይሉ አሰፋ ለተጋጣሚ ተከላካዮች ራስ ምታት ሆኖ ማምሸቱ እንዳለ ሆኖ ቡድኑ ላስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ሚና ተጫውቷል። በዚያ ላይ የፍጹም ቅጣት ምት ተከለከለ እንጅ የቡናውን ተከላካይ ሚሊዮን ወንድሙን ዘርሮት አልፎ ለቡድኑ ፍጹም ቅጣት ምት አስገኝቶ ነበር። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ በሙሉ 90 ደቂቃው ያለውን ሁሉ ለክለቡ ሲሰጥ ያለምንም መሳሳት ነበር። በዚህ ምክንያት የእለቱ ኮከብ ተብሎ ቢመረጥ የሚገባው እንጅ የሚበዛበት አይሆንም። 

ከቱሳ በተጨማሪ ደግሞ አማካይ ተከላካዩ ተስፋዬ አለባቸው የቡናዎችን የመሃል ሜዳ የበላይነት በቀላሉ መሰበር የቻለ የቡድኑ ጀግና ሆኖ ነው ያመሸው። ጉልበተኛውና ግልፍተኛው አማካይ ተከላካይ በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ከቡናው አምበል ዳዊት እስጢፋኖስ ጋር የፈጠረው አላስፈላጊ ውዝግብና አተካሮ ለቢጫ ካርድ እስከዳረገው ደቂቃ ድረስ ቡድኑን በሙሉ አቅሙ ሲያገለግል ታይቷል። ሮበርት ኦዶንካራ ምንጊዜም ቢሆን ከነሙሉ ብቃቱ ፈረሰኞቹን የሚያገለግል የጎሉ ታማኝ ዘበኛ ነው። በትናንትናው እለትም ከቡናዎች በኩል በተለይ ከእረፍት በፊት የደረሱበትን የጥቃት ሙከራዎች በንቃት ሲያመክን አምሽቷል። 

በቡና በኩል ተከላካዮቹ አጅመድ ረሽድና ኤፍሬም ወንድወሰን የሚያግዛቸው ማጣታቸው እንጅ ቡድናቸው መረቡን ሳያስደፍር መውጣት እንዲችል ያደረጉት ጥረት የሚያስወድሳቸው ነው። ሁለቱም የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች ኳስን ወደመጣችበት ከመጠለዝ ይልቅ ተረጋግተውና መሬት አስይዘው የሚጫወቱ ከመሆናቸውም በላይ በተጋጣሚ ቡድን አጥቂዎች በቀላሉ አይታለፉም። በተለይ ሽሪላው በማጥቃቱ በኩል ቡድኑን የሚረዳ ሲሆን ፍጥነቱ ደግሞ የሚገርም ነበር። ከጉዳት ጋር የሚታገለው አምበሉ ዳዊት እስጢፋኖስ እንደተለመደው የፍጥነት ችግር ያለበት ቢሆንም ቡድኑን በማረጋጋትና የተመጠኑ ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ በማድረስ በኩል የተሳካለት ነበር። 

ከሶስቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ አማካይ ተከላካዩ ጋቶች ፓኖም ሙሉውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ጋር ሲላፋ ያመሸ ሲሆን ተጨማሪ ጎሎች ቡድናቸው እንዳያስተናግድ የከፈለው መስዋዕትነትም የሚያስመሰግነው ነው። ወጣቱ አማካይ ተከላካይ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊሱ አቻው ተስፋዬ አለባቸው ሀይልን ቀላቅሎ የሚጫወት በመሆኑ ተደጋጋሚ ፋዎሎችን ሲሰራ ቢያመሽም እስከ ጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ድረስ ቢጫ ካርድ ሳያይ መቆየቱ እድለኛ አስብሎታል። 

የዳኛው ስህተቶች 

ኢንተርናሽናል ባምላክ ተሰማ አገሪቱ ውስጥ ካሉ ዳኞች መካከል የተሻለ ችሎታ አላቸው ከሚባሉት አንዱ ናቸው። የሶሽዮሎጅ ምሁሩ ባምላክ ተሰማ በእለቱ ጨዋታውን በሚገባ መምራት የቻሉ ቢሆንም ከሁለት ጊዜ በላይ ከባባድ ስህተቶችን ሲፈጽሙ ታይተዋል። የእለቱ የዳኛው ትልቁ ስህተት ሆኖ የተመዘገበው የቅዱስ ጊዮርጊሱ በሀይሉ አሰፋ የቡናውን ተከላካይ ሚሊዮን ወንድሙን አታሎ በማለፍ ጎል ሊያስቆጥር ሲሞክር ተጠልፎ ቢወድቅም ዳኛው ግን ሆን ብሎ ፍጹም ቅጣት ምት ለማግኘት የወደቀ መስሏቸው ለበሀይሉ ቢጫ ካርድ ሰጥተውታል። በዚህ ውሳኔያቸው ከተመልካች ከባድ ተቃውሞ አስተናግደዋል።

በጨዋታው የፈጸሙት ሌላው ስህተት ደግሞ በተደጋጋሚ ተጫዋቾች ተጎድተው ሲወድቁ ጨዋታዎችን ማስቆም ሲገባቸው እሳቸው ግን ጨዋታው እንዲቀጥል ያደርጉ ነበር። በተለይ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተከላካይ አሉላ ግርማ ተጎድቶ በወደቀበት ሰዓት ከአንድ ደቂቃ በላይ ጨዋታው እንዲቀጥል ማድረጋቸው ልጁ ህክምና ቶሎ እንዳያገኝ አድርገዋል። ሌሎች ጥቃቅን ስህተቶቻቸው ግን በማንኛውም ዳኛ የሚከሰቱ በመሆናቸው በዚህ ጽሁፍ ማንሳት አልፈለግንም። 

ከዚህ በተረፈ ግን ለዳኞች ምንም አይነት ከለላ በማያደርግ ፌዴሬሽን ውስጥ እንደዚህ አይነት ከባድ ጨዋታዎችን በብቃት መርቶ በማጠናቀቃቸው የእለቱ ዳኞች በሙሉ ሊመሰገኑ የሚገባቸው ናቸው ማለት እንችላለን። ተመልካቾችም የራሳቸውን ቡድን የሚጎዳ የሚመስል ውሳኔ ሲተላለፍ በዳኞች ላይ ያልተገባ የስንፍና ቃል ወይም ስድብ ከመጠቀም ቢታቀቡ መልካም ነው ማለት እንሻለን።
   
ካሳ ሀይሉ 
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!