ሃዋሳ ከነማ ወደ ሽንፈት ኤሌክትሪክ ወደ ድል የተመለሱበት 19ኛው ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ
ሚያዚያ 13, 2007

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየምና ሶዶ ሁለገብ ስታዲየም ተካሂደዋል። ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት የተካሄደው የደቡብ ደርቢ ጨዋታ ወላይታ ድቻ ከተከታታይ ሽንፈት ያገገመበትን ሙሉ ሶስት ነጥብ አስመዝግቧል። ለመሳይ ተፈሪ ቡድን ከሶስት ጨዋታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ ሶስት ነጥብ ያስገኘችዋን ብቸኛ ጎል ያስቆጠረው አጥቂው አላዛር ፋሲካ ነው። ከሶዶ በደረሰን መረጃ እንደተረዳነው ጨዋታው ጥሩ የኳስ ፍሰት የታየበትና ለመሸናነፍ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ነበር። ድሉን ተከትሎ ወላይታ ድቻ ከነበረው 25 ነጥብ ላይ ሶስት በመጨመር አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሀዋሳ ከነማ ደግሞ ከነበረበት 13ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል። 
ELPA up Hawassa Down in the table rank

በጨዋታው አንድም ቀይ ካርድ የተመለከተ ተጫዋች ባይኖርም ቁጥሩ በርከት ያለ ቢጫ ካርድ ለተጫዋቾች መታደሉን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። የቢጫ ካርድ ከተመለከቱ ተጫዋቾች መካከል የወላይታ ድቻው ተከላካይ አዲስ ተስፋዬ ይገኝበታል። አዲስ የትናንቱን ጨምሮ አምስት ቢጫ ካርዶችን የተመለከተ በመሆኑ በቀጣዩ ሳምንት ክለቡ ከ ወልዲያ ከነማ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ በቅጣት አይሰለፍም። 

ሀዋሳ ከነማ በሁለተኛው ዙር አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ከቀጠረ በኋላ ሁለት ጨዋታዎችን በተከታታይ በማሸነፉ ቡድኑ መነቃቃት አሳይቶ የነበረ ቢሆንም ከአዳማ ከነማ ጋር አቻ  1ለ1 ከተለያየ በኋላ ግን ወደ ቀድሞ የሽንፈት ሃንጎቨሩ ተመሷል። በ18ኛ ሳምንት ጨዋታው “የግርጌው ንጉስ” ወልድያ ከነማ ሁለት ለአንድ ያሸነፈው ሲሆን ትናንት ደግሞ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን በተሸነፈው ወላይታ ድቻ አንድ ለባዶ ተሸንፎ ወደ 13ኛ ደረጃ በመመለስ ከሙገር ሲሚንቶ፣ ዳሽን ቢራ እና ኤሌክትሪክ በታች ሊቀመጥ ተገድዷል።  

በሌላ ጨዋታ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ከወልድያ ከነማ ጋር ያደረጉት ጨዋታ በኤሌክትሪክ ሁለት ለባዶ ተጠናቋል። ከሊጉ ለመውረድ ከገደሉ አፋፍ ላይ የነበረው ወልድያ ከነማ ትናንት በኤሌክትሪክ የደረሰበት ሽንፈት ለመውደቅ እንዲንደረደር አድርጎታል ማለት ይቻላል። ኤሌክትሪክ በሁለተኛው ዙር ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ ሶስት ነጥብ ያገኘባቸውን ሁለት ጎሎች ናይጄሪያዊው ፒተር እና ፍቅረየሱስ ተለብርሃን አስቆጥረዋል። ድሉን ተከትሎም የአጥናፉ ዓለሙ ቡድን ከነበረው 18 ነጥብ ላይ ሶስት በመጨመር 21 አድርሶ በስድስት የጎል እዳ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ወልድያ ከነማ በመጀመሪያው ዙር “የግብ ጠባቂ ችግር አለብኝ” ብሎ የብሔራዊ ቡድኑን ሲሳይ ባንጫን ከደደቢት አስኮብልሎ ቢወስድም “ከምን ቤት ምን ገባበት” ሆኗል። በተለይ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ቡድኑ በአራቱ ሲሸነፍ የሲሳይ ባንጫ እርዳታ ከምንም የሚቆጠር አልሆነም። ምክንያቱም ክለቡ የተቆጠሩበት ጎሎች አብዛኞቹ የግብ ጠባቂው ስህተትና እንዝህላልነት የታየባቸው ናቸውና። ትናንት ፒተር ያስቆጠረው የመጀመሪያ ጎልም ከሲሳይ ባንጫ በስጦታ የተበረከተች ናት ማለት ይቻላል። 

ፕሪሚየር ሊጉ ከተጀመረበት እለት ጀምሮ የደረጃውን ግርጌ የያዘው ወልድያ ከነማ አንድም ጊዜ ወደ ላይ ከፍ ሳይል በነበረበት እንደረጋ ወደ 20ኛው ሳምንት ደርሷል። በቀሪዎቹ ሰባት ጨዋታዎች ሁሉንም አሸንፎ ሌሎቹ የወራጅ ስጋት ያንዣበበባቸው ጓዶቹ ካልተሸነፉለት ወደመጣበት የታችኛው ሊግ መመለሱ የማይቀር ይሆናል። አሁን እያሳየ ካለው አቋም እና የተጫዋቾች ስነ ልቦና አኳያ ከታየ ግን የመውረዱ ነገር ቢዘገይ እንጀ የሚቀር አይመስልም። 

ካሳ ሀይሉ 
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!