ክፍል አንድ: ለጋቦኑ ጉዞ ዝግጅቱ አሁን ቢጀመርስ?
ሚያዚያ 15, 2007


Walia What Next
የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ካፍ ሁለት ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ጋቦን ላይ  የአህጉሪቱን ትልቁን የእግር ኳስ ውድድር ያካሂዳል። በዚያ ውድድር ላይ አስተናጋጇን ጋቦንን ጨምሮ 16 አገሮች የሚሳተፉ ሲሆን እስካሁን ከአስተናጋጇ አገር ውጭ ያሉት ቀሪዎቹ 15 ተሳታፊ አገራት አልታወቁም። ነገር ግን በውድድሩ ተሳታፊ ለመሆን አገራት በ13 ምድብ ተከፍለው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታቸውን እንዲያካሂዱ ከፊታችን ሰኔ አጋማሽ ጀምሮ ቀነ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል። በየምድቡ አንደኛ የሚወጡ አገራት ወደ ውድድሩ ቦታ በቀጥታ ሲያመሩ ቀሪ ሁለት አገሮች ደግሞ ከ13ቱ ምድቦች የተሻለ ውጤት ያላቸው ተመርጠው ለአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ያመራሉ። 

የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በምድብ አስር ከአልጄሪያ፣ ሲሸልስና ሌሴቶ ጋር ተደልድሏል። ብሔራዊ ቡድኑ ተጋጣሚ አገሮቹን ቀድሞ ያወቀ ቢሆንም የሚያሰለጥኑትን አሰልጣኞች ግን ማወቅ አልቻለም። ፌዴሬሽኑ አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶን ከሀላፊነታቸው ማንሳቱን ይፋ ካደረገ የቀየ ቢሆንም የርሳቸውን ቦታ ተረክቦ ሀላፊነቱን የሚወስደውን ሰው ማንነት እስካሁን አላሳወቀም። የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ቅጥር ከዚህ በላይ የሚዘገይ ከሆነ ግን በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የተሰራውን ስህተት የሚደገም በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ዝምታውን ሰብሮ የአሰልጣኝ ቅጥር በአስቸኳይ እንዲያካሂድ በርካታ ወገኖች እየወተወቱ ይገኛሉ። 

ከፕሪሚየር ሊጉ መጠናቀቅ በፊት የአሰልጣኝ ቅጥር ቢጠናቀቅ

በ2015 ሞሮኮ ልታዘጋጀው አስባ “በኢቦላ ተከብቤ ውድድር አዘጋጅቼ ራሴን ለአደጋ አላጋልጥም” በማለቷ ውድድሩን ትንሿ አገር ኢኳቶሪያል ጊኒ ማዘጋጀቷ የሚታወስ ነው። በዚያ ውድድር ለመሳተፍ ብሔራዊ ቡድኑ በምድብ ማጣሪያው ስድስት ጨዋታዎችን ቢያካሂድም አምስት ነጥብ ብቻ በመሰብሰቡ ከውድድሩ ውጭ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ዋልያዎቹ ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ እንዳይሄዱ ያደረጋቸው ቡድኑ በምድብ ማጣሪያው የእግር ኳስ ደረጃቸው ከፍ ያሉ አገሮች ስለደረሱት ነው ተብሎ ቢነገርም አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ግን ለዝግጅት በቂ ጊዜ ባለማግኘታችን ነው ማለታቸው አይዘነጋም። 

አንድ ቡድን በተለይም እንደ እኛ አገር ያለ የእግር ኳስ ደረጃው ዝቅተኛ የሆነ አገር ለምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ሲዘጋጅ በቂ ጊዜ ወስዶ መሆን አለበት። ለምሳሌ የአገሪቱ ትልቁ ሊግ ሊጠናቀቅ ሰባት ሳምንታት ብቻ ይቀሩታል። የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ በዚህ ጊዜ ተቀጥሮ የሊጉን ጨዋታዎች ተከታትሎ ቡድኑን ካላዋቀረ መቼ ተቀጥሮ መቼ ተጫዋቾችን ሊመርጥ ይችላል? የሚል ጥያቄ በስፖርት ቤተሰቡ የሚነሳ ጥያቄ ነው። የአገራችን እግር ኳስ ደረጃው ካለማደጉም በላይ የጨዋታዎች ቀሪ ምስል በተፈለገው ጊዜ የማይገኝ መሆኑ አሰልጣኞች የትኞቹ ተጫዋቾች ዓመቱን ሙሉ የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገዋል ብለው እንዳይመርጡ እንቅፋት ይሆንባቸዋል።

 ከዚህም በላይ ግን የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች በፕሪሚየር ሊጉ የሚደረጉ ጨዋታዎችን በስታዲየም ታድመው የሚከታተሉ አዲስ አበባ የሚካሄዱትን ብቻ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ በተደጋጋሚ የብሔራዊ ቡድኑን ምርጫ እድል በብዛት የሚያገኙት የአዲስ አበባ ክለቦች ተጫዋቾች ሲሆኑ ይታያል። ለዚህ ሁሉ ስህተት በር ለመዝጋት ፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ምርጫውን በጊዜ ቢያከናውን መልካም ይመስለናል። 

የብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ታሪኩ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 30 ጊዜ ከተካሄደው የአህጉሩ ታላቁ ውድድር በዘጠኙ ተሳታፊ መሆን ችሏል። ቡድኑ በዘጠኙ ተሳታፊ ሲሆን ሶስቱን አስተናጋጅ በመሆኑ በቀጥታ በማለፉ ሲሆን  ከዚህ በተጨማሪም የውድድሩ መስራች በመሆኑ በቀጥታ ያለፈባቸው ጊዜያትም አሉ። ለምሳሌ በአንደኛውና በሁለተኛ በቀጥታ ሲያልፍ፤ ሶስተኛውን ዋንጫ በማንሳቱ አራተኛውን ያለማጣሪያ በቀጥታ የለፈበት ጊዜ ነበር። ሶስት ጊዜ ደግሞ በደርሶ መልስ በሚደረግ ጨዋታ በሚሰበስበው የጎል ክፍያ ብልጫ ነው። 

ብሔራዊ ቡድኑ በሶስት ውድድሮች በደርሶ መልስ ማጣሪያ ማለፉ የሚነገር ሲሆን በተለይ በ13ኛው የሊቢያ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍና በ29ኛው የደቡብ አፍሪካው አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የተደረጉ ጨዋታዎች በእግር ኳስ ቤተሰቡ የማይዘነጉ ናቸው። ለ13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የመሃመድ ሚግ የግንባር ጎል አስፈላጊው ስትሆን ለደቡብ አፍሪካው ጉዞ መሳካት ደግሞ የአዳነ ግርማ የግንባር ጎል እና የሳላሃዲን ሰይድ ጎል እጅግ ወሳኝ ነበሩ። 

ከዚህ ውጭ ብሔራዊ ቡድናችን በምድብ ማጣሪያ ተደልድሎ ከምድቡ የበላይ ሆኖ በማጠናቀቅ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የሆነበት ጊዜ የለም። ለዚህ ደግሞ በተደጋጋሚ ጊዜ የተለያዩ ምክንያቶች ይቀርባሉ። በአንድ ወቅት አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ሲናገር “ብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ የሚቀጠርለት ቢበዛ ለሁለት ወር አለዚያ ለአንድ ወርና ለሁለት ሳምንት እንዲሁም ለአንድ ሳምንት ጊዜ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ አሰልጣኞች ተረጋግተን ስራችንን እንዳንሰራ ያደርገናል” ብሎ ተናግሮ ነበር። የአስራት ሀይሌን ሃሳብ የተጋራ የሚመስለው የእነ አቶ ሣህሉ ገብረወልድ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለአቶ ሰውነት ቢሻው የሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ መስጠቱ ይታወሳል። 

በእነዚህ ጊዜያት አቶ ሰውነት ምን ያህል ውጤታማ ሆነዋል ብሎ ፍርዱን የሚሰጠው የእግር ኳስ ቤተሰቡ ቢሆንም ቢያንስ ግን አሰልጣኙ ተረጋግተው ስራቸውን መስራት ችለው እንደነበር ግልጽ ነው። አቶ ሰውነት በተለይ ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ከቤኒን ጋር ሲጫወቱ የነበረባቸውን ክፍተት አይተው በርካታ አስተያየት ሰጭዎች በአሰልጣኙ ቡድን ላይ የተወሰነ ለውጥ እንዲደረግ በመጠየቃቸው አሰልጣኙ በአስቸኳይ ለውጦችን ማድረጋቸው ይታወሳል። በለውጡ ተጠቃሚ የሆነውም ብሔራዊ ቡድኑ ነበር። ምክንያቱም አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ አንድ ጎል ማስቆጠር የተሳነው ቡድን በቤኒን ሜዳ ላይ አንድ ጎል ከማስቆጠሩም በላይ በቀጣዩ የማጣሪያ ጨዋታ እምዱርማን ላይ ሶስት ጎል ማስቆጠር የቻለ ቡድን የተሰራበት ጊዜ በመሆኑ ነው። 

ይቀጥላል... 

ካሳ ሀይሉ
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!