ክፍል ሁለት: ለጋቦኑ ጉዞ ዝግጅቱ አሁን ቢጀመርስ?
ሚያዚያ 17, 2007


የቡድኑ ተስፋና ፈተናዎች

ከላይ በተጠቀሰው ንዑስ ርዕስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ ድልድሉ የበላይ ሆኖ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈበት ጊዜ እንደሌለ ተገልጿል። ብሔራዊ ቡድኑ ለ31 ዓመታት ከመድረኩ ርቆ ወደ መድረኩ የተመለሰውም በደርሶ መልስ ብዙ ባገባ በሚለው የፊፋ ህግ መሆኑ ተገልጿል። ብሔራዊ ቡድኑ በ2017 እ.አ.አ በጋቦን ለሚካሄደው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በምድብ ድልድል መካተቱ ይታወሳል። ታዲያ ዋልያዎቹ በዚህ የምድብ ድልድል ተስፋቸውና ፈተናቸው ምንድ ነው? የሚለውን ጥያቄ አብረን እንመልከት። 

Waliya


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለፉት አራት ዓመታት በእግር ኳስ ደረጃቸው ከፍ ካሉ አገሮች ጋር ተጫውቶ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት የቻለው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው። አንዱ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ደቡብ አፍሪካን ሁለት ለአንድ አሸንፎ ሲሆን ሌላው ደግሞ ባማኮ ላይ ማሊን ሶስት ለሁለት አሸንፎ ነው። በቀሪዎቹ ታላላቅ ጨዋታዎች በቀላሉ እጁን የሚሰጥ ቡድን መሆኑን በቀላሉ ማረጋገጥ የሚቻለው ቡድኑ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ከናይጄሪያ ጋር አራት ጊዜ ተጫውቶ በአራቱም መሸነፉ ነው። ከዚህ ውጭ በአልጄሪያም ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። 

ከታላላቅ የእግር ኳስ አገሮች ጋር ሲጫወት በቀላሉ “ወገቤን” የሚለው ብሔራዊ ቡድናችን ያም ሆኖ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በተወሰነ መልኩ መሻሻል እያሳየ ይገኛል። ይህም ከሜዳው ውጭ ከታላላቆቹም ጋር ሆነ ከታናናሾቹ ጋር ሲጫወት ቢያንስ ጎል ማስቆጠር ችሏል። ከዚህ በተጨማሪ በእግር ኳስ ደረጃ ከዋልያዎቹ በታች የሆኑትን አገሮች ከሜዳው ውጭ ተጫውቶ ማሸነፍ ችሏል። እነዚህ ነጥቦች በዘንድሮው የምድብ ማጣሪያ የቡድኑ ተስፋዎች ናቸው። 

ሌላው የብሔራዊ ቡድኑ ትልቁ ተስፋው የምድቡ ተፋላሚ አገሮች የእግር ኳስ ደረጃ ነው። ዋልያዎቹ ከአልጄሪያ፣ ሌሴቶና ሲሸልስ ጋር መደልደሉ በብዙ መልኩ እድለኛ ያስብለዋል። ከአልጀሪያ ውጭ ያሉት ሁለቱ አገሮች የእግር ኳስ ደረጃቸው ከዋልያዎቹ በእጅጉ ዝቅ ያለ ነው። ይህ ደግሞ ቡድኑ በምድብ ማጣሪያው ከሚያካሂዳቸው ስድስት ጨዋታዎች ቢያንስ አራቱን የማሸነፍ እድል እንዲያገኝ ያደርገዋል። ቡድኑ ከሲሸልስና ሌሴቶ ጋር የሚያደርጋቸውን የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በቀላሉ በሰፊ የጎል ልዩነት ማሸነፍ ያስችለዋል። በተለይ ከሲሸልስ ጋር መጫወት እንደ ስጦታ የሚያስቆጥረው መሆኑን በቅርቡ ደደቢት እግር ኳስ ክለብ ኮት ዲ ኦር ከሚባል የአገሪቱ ክለብ ጋር ባደረገው የደርሶ መልስ ጨዋታ ያስመዘገበው የአምስት ለሁለት አጠቃላይ ውጤት ማሳያ ነው። 

ደደቢት በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እያሳየ ያለው አቋም አሳማኝ አለመሆኑ እየታየ ነው። ይህ ቡድን ነው እንግዲህ የሲሸልሱ ክለብ ላይ አምስት ጎሎችን አስቆጥሮ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈው። እንዲያውም በመጀመሪያው ጨዋታ አራት ምዕራብ አፍሪካውያን ተጫዋቾቹን በቪዛ ምክንያት እንዲሁም የተወሰኑትን የቡድኑን ቋሚ ተሰላፊዎች በጉዳት ሳያሰልፍ ያደረገው ጨዋታ መሆኑን ከግምት ሲገባ የሲሸልሱ ኮት ዲ ኦር ደረጃው ምን ያህል ዝቅ ያለ መሆኑን እንረዳለን። ዋልያዎቹም በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው የሚገጥሙት የኮት ዲ ኦርን አገር መሆኑ በቀላሉ ማሸነፍ የሚኖርባቸው ጨዋታ እንደሆነ ያሳያል። ብሔራዊ ቡድናችን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከሜዳው ውጭ ማሸነፍና ጎል ማስቆጠር እየለመደ መጥቷል ከተባለ ከአልጄሪያ ጋር የሚደርጋቸውን ሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታዎችም ቢያንስ አንድ ነጥብ የማግኘት ተስፋ ሊይዝ የሚገባው ይሆናል።

ከላይ የተጠቀሰውን ያህል በብሔራዊ ቡድኑ የምድብ ማጣሪያ ጉዞ ላይ ሰፊ ተስፋ ቢኖርም የቡድኑ ትልቁ ስጋት ግን ከአሁኑ ዝግጅት አለማድረጉ ነው። ኢትዮፉትቦል ዶትኮምም ሆነ የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ብሔራዊ ቡድኑ ከአሁኑ ተሰባስቦ ሆቴል ገብቶ ይቀለብ የሚል እምነት የላቸውም። ነገር ግን ፌዴሬሽኑ ቀጣዩን የአገሪቱ አሰልጣኝ እንዲሆን የሚፈልገው የአገር ውስጥ አሰልጣኝ ከሆነ እና በክለብ ስራ ላይ የሚገኝ ከሆነ ቶሎ ከኮንትራት ነጻ ሆኖ ስራውን እንዲጀምር ማድረግ አለበት። የውጭ አገር አሰልጣኝ የሚቀጥር ከሆነም አዲሱ አሰልጣኝ በጊዜ ተመርጦ ስራውን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መጀመር ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ግን የጨዋታ ጊዜ እየቀረበ ሲመጣ ለብሔራዊ ቡድኑ የሚመረጡ ተጫዋቾችን ጨምሮ እስከ ቡድን መሪና ረዳት አሰልጣኞች ምርጫ ችኮላ የሚበዛበት ስለሆነ ጥራት ያለው አሰራር ላይኖር ይችላል የሚል ስጋት አለን። 

ሌላው የቡድኑ ትልቁ ስጋት የሚመነጨው ግን ከተጫዋቾች ምርጫ ይሆናል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንደታየው አንዳንድ የክለብ አመራሮችና የፌዴሬሽን ሀላፊዎች በብሔራዊ ድን ተጫዋቾች ምርጫ እጃቸውን ሲያስገቡ የታዩ ሲሆን ይህ ድርጊታቸው ደግሞ በቡድኑ ላይ ውድቀትን ሲያስከትል ቆይቷል። ይህ የተለመደ ይትባህል በቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያም የሚደገም ከሆነ እግር ኳሱን ከድጡ ወደ ማጡ ያወርደዋል። ለዚህ ደግሞ ፌዴሬሽኑም ሆነ አዲሱ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቁርጠኛ ውሳኔ የሚያስተላልፉ መሆን አለባቸው። 

የተጋጣሚ አገሮች ፖለቲካዊ ሁኔታ አስተማማኝ ካልሆነና ቡድኖቹ ጨዋታቸውን በገለልተኛ ሜዳ የማያካሂዱ ከሆነ በብሔራዊ ቡድኑ ውጤት ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ውጤት ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ ነው። ለምሳሌ በአንድ ወቅት የላይቤሪያ ፖለቲካዊ ቀውስ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውጤት ላይ ያሳደረው ተጽእኖ አይዘነጋም። ብሔራዊ ቡድኑ በገለልተኛ ሜዳ እንዲጫወት የወቅቱ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ የፌዴሬሽኑን ስራ አስፈጻሚ ደጋግሞ ጠይቆ የነበረ ቢሆንም የአሰልጣኙ ጥያቄ አለመመለሱ ብሔራዊ ቡድኑ ጥይት እየተተኮሰበት በመጫወቱ ተሸንፎ ከአፍሪካ ዋንጫ ውጭ መሆኑ ይታወሳል። 

በ2014 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ዋልያዎቹ በአንድ ተጫዋች ሁለት ቢጫ ካርድ ምክንያት ሶስት ነጥብ ተቀንሶባቸው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ገጠመኝ ነው። የተቀነሰው ነጥብ ብሔራዊ ቡድኑን በቀጣዩ ጨዋታው የግድ አሸናፊ መሆን እንዳለበት የሚያስገድደው ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ቡድኑ የመጨረሻ ጨዋታውን ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር ለማድረግ ሲዘጋጅ በወቅቱ አገሪቱ ላይ ተከስቶ የነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ እንዲሆን አስገድዷል። በገለልተኛ ሜዳ ጨዋታው መካሄዱ ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑ ሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክን በቀላሉ እንዲያሸንፍ አስችሎታል።  

በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድል ጨዋታም የዋልያዎቹ ተጋጣሚ አገራትን ፖለቲካዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ጨዋታዎች የሚካሄዱባቸውን ሜዳዎች በማስወሰን ፌዴሬሽኑ የቤት ስራ አለበት። ለዚህ ደግሞ ቅድመ ዝግጅቱን ከአሁኑ እንዲጀምር አስተያየታችንን እናስተላልፋለን። ምክንያቱም ከሁለት ዓመት በፊት ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ብሔራዊ ቡድኑ ቀላል ተጋጣሚ አገሮች ደርሶት እድሉን እንደተጠቀመበት ሁሉ በዚህ ዓመትም በተመሳሳይ ቀላል የሚባሉ ጨዋታዎችን የሚያደርግ በመሆኑ እድሉን ማበላሸት የለበትምና ነው። 

ካሳ ሀይሉ
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!