ካምቦሎጆ ዛሬና ነገ ሁለት ታላለቅ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል
ሚያዚያ 17, 2007

 በአዲስ አበባ ስታዲየም ዛሬ ከቀኑ አስር ሰዓት ተከታታይ የሽንፈት ጽዋ የተጎነጨው ኢትዮጵያ ቡና ከደደቢት ይጫወታሉ። ሁለቱ ክለቦች በዚህ ዓመት በተለያዩ ውድድሮች ሁለት ጊዜ ተገናኝተው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና በሁለቱም ግንኙነቶች በበላይነት ማጠናቀቅ ችሎ ነበር። በመጀመሪያ ግንኙነታቸው በአዲስ አበባ ዋንጫ ሲሆን ቢኒያም አሰፋ የዓመቱን የመጀመሪያ ሶስታ ያስቆጠረበትና ቡና ሶስት ለባዶ ያሸነፈበት ሲሆን በፕሪሚየር ሊጉ ግንኙነታቸው ደግሞ በድጋሚ ኢትዮጵያ ቡና ሁለት ለባዶ ማሸነፍ ችሎ ነበር። ደደቢት በቡና ከደረሰበት ሽንፈት በኋላም አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታን አሰናብቷል። 

ተደጋጋሚ ሽንፈት ሰለቸን ተደጋጋሚ ሽንፈቱ የክለባችንን ደረጃም አይመጥንም ያለው ኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻን አሰናብቶ በምክትሉ አንዋር ያሲን እየተመራ ባለፈው ሳምንት የምንጊዜም ተቀናቃኙን ቅዱስ ጊዮርጊስን ገጥሞ ሁለት ለባዶ ተሸንፏል። ክለቡ ውስጥ መረጋጋትና አንድነት የለም እየተባለ የሚነገርበት ኢትዮጵያ ቡና ዛሬ ደደቢትን ማሸነፍ ካልቻለ ይበልጥ ቀውስ ውስጥ የሚገባ በመሆኑ ለጨዋታው ልዩ ትኩረት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። 

በቅርቡ አሰልጣኙን ዮሃንስ ሣህሌን ለብሔራዊ ቡድኑ አሳልፎ ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቀው ደደቢት በበኩሉ ባለፈው ሳምንት በሲዳማ ቡና የሁለት ለአንድ ሽንፈት ደርሶበት ከይርጋዓለም መመለሱ የሚታወስ ሲሆን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ በናይጄሪያው ወሪ ዎልቭስ ተሸንፎ ከውድድሩ ውጭ ሆኗል። በጥሎ ማለፉም በጊዜ የተሰናበተ መሆኑ አይዘነጋም። እንዲሁም ክለቡ በዚህ የውድድር ዓመት ከታላላቅ ክለቦች ጋር ሲገናኝ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት አልቻለም። ከታላላቅ ክለቦች ጋር በሚያደርገው ጨዋታ የዓመቱን የመጀመሪያ ሙሉ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ዛሬ ይጫወታል ተብሏል። በሁለቱም ክለቦች በኩል የቡድኖቻቸውን ወቅታዊ መረጃዎች ማግኘት አልቻልንም። 

ከደደቢትና ቡና ጨዋታ ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ቡና ታዳጊ ቡድን ከአዲስ አበባ ከነማ ታዳጊዎች ጋር እንደሚጫወቱ ፌዴሬሽኑ ገልጿል። 

ነገ ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይገናኛሉ። የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ የሚል ስያሜ የተሰጠው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የሚመዘገበው ውጤት የሊጉን ዋንጫ ማረፊያ ይጠቁማል ተብሎ ይጠበቃል። ፈረሰኞቹ ድል ከቀናቸውና ነገ አዳማ ላይ አዳማ ከነማ ከሲዳማ ቡና በሚያደርጉት ጨዋታ የሚመዘገበው ውጤት ፈረሰኞቹን ተጠቃሚ የሚያደርግ ከሆኑ ፈረሰኞቹ የዋንጫውን አንድ ጆሮ እንደያዙ ይቆጠራል። ውጤቱ በተቃራኒው ከሆነና በተለይም ሲዳማ ቡና ደግሞ አዳማ ከነማን ማሸነፍ ከቻለ ፈረሰኞቹ የዋንጫውን አንገት ለመጨበጥ ዳጋት ይሆንባቸዋል። በዚህም ምክንያት ጨዋታው ከባድ ፉክክርና ትልቅ ትኩረት የሚካሄድበት እንደሚሆን ይጠበቃል። 

አትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጀመሪያው ዙር የሊጉ ጨዋታዎች ወጥ አቋም ማሳየት ተስኖት በ13 ጨዋታ 16 ነጥብ ብቻ ሰብስቦ ማጠናቀቁ የሚታወስ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ግን በስድስት ጨዋታዎች 16 ነጥብ በመሰብሰብ ከሊጉ ጠንካራ ክለቦች አንዱና የመጀመሪያው አድርጎታል። ይህ ጥንካሬውም ነገ ለፈረሰኞቹ ፈተና እንደሚሆን ሲጠበቅ ፈረሰኞቹ በበኩላቸው ብራዚላዊውን አሰልጣኝ ካሰናበቱ በኋላ በተከታታይ ያደረጓቸውን ጨዋታዎች በማሸነፍ የሊጉን መሪነት መቆናጠጥ ችለዋል። ታላላቆቹን ኢትዮጵያ ቡና እና ሲዳማ ቡናን በማሸነፍም የታላላቅ ጨዋታዎች አሸናፊነትን የተላበሰ ቡድን እንደገነቡ አሳይተዋል። 

ካሳ ሀይሉ 
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
ALEX barca [966 days ago.]
 vamos ethio coffie

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!