ኢትዮጵያ ቡና ከተከታታይ ሽንፈቱ መውጣት አልቻለም
ሚያዚያ 18, 2007

20ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ትናንት በአንድ ጨዋታ ቀጥሎ ውሏል። ተከታታይ ሶስት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ተስኖት የቆየው ኢትዮጵያ ቡና ትናንትም በደደቢት ከጨዋታ ብልጫ ጋር ሶስት ለባዶ ተሸንፏል። ሳሙኤል ሳኖሜ አልያዝና አልጨበጥ ብሎ ባመሸበት ጨዋታ በቅርቡ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ለማሰልጠን የተመረጡት የደደቢቱ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሣህሌ ጣፋጭ ድል ያስመዘገቡበትን ድል አግኝተዋል። ለደደቢት ጎሎቹን ከእረፍት በፊት ሳሙኤል ሳኖሜ ሁለት ሲያስቆጥር ቀሪዋን አንድ ጎል ደግሞ ተቀይሮ የገባው ዳዊት ፈቃዱ አስቆጥሯል። ሳኖሜ ላስቆጠራት ሁለተኛዋ ጎል የቡናው ተከላካይ ሚሊዮን ወንድሙ እና ግብ ጠባቂው ሙሴ ገብረኪዳን ውለታ ውለውለታል። 

ደደቢት ባለፈው ሳምንት ወደ ይርጋዓለም ተጉዞ ሁለት ለአንድ ተሸንፎ የተመለሰ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን ትናንት ምሽት ግን በኢትዮጵያ ቡና ላይ የተቀዳጀው ድል ተስተካካይ ሶስት ጨዋታዎች እየቀሩት ነጥቡን  ወደ 25 ማድረስ ችሏል። ደረጃውን ደግሞ  ወደ 9 አሻሽሏል። የደደቢቱ ሳሙኤል ሣኖሜ ትናንት ቡና መረብ ላይ ያሳረፋቸው ሁለት ጎሎች በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ወደ 12 ከፍ ማድረግ አስችለውታል። በዚህም ምክንያት ከመሪዎቹ ቢኒያም አሰፋ እና ፍሊፕ ዳውዝ በአንድ ጎል ተበልጦ እየተከተለ ይገኛል።        

ባለፈው ሳምንት በፈረሰኞቹ ሁለት ለባዶ ተሸንፎ የነበረው ቡና ትናንት የተወሰኑ ተጫዋቾችን ቀይሮ በመግባት ውጤት ይዞ ለመውጣት ቢሞክርም ይበልጥ በተጋጣሚው ተበልጦ ታይቷል። ሙሉ የጨዋታውን ጊዜ ከተወሰኑ ተጫዋቾችና ከጋቶች ፓኖም ውጭ ክለባቸውን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የታየ ተጫዋች አልነበረም ማለት ይቻላል። በተለይ ወጣቶቹ ሳሙኤል ወንድሙ፣ ሚኬኤል በየነ እና ሀብታሙ ረጋሳ ያገኙትን የመሰለፍ እድል በአግባቡ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። 

  ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ክለቡ ለተከላካዩ ኤፍሬም ወንድወሰን አሁንም ሁነኛ አጣማሪ ለማግኘት የተቸገረ መሆኑን ነው። ኤፍሬም በተፈጥሮው ተረጋግቶና ሳይረበሽ የሚጫወት ተጫዋች ቢሆንም አብሮት የሚሰለፉት ተጫዋቾች ድካሙን ሊያግዙት ባለመቻላቸው ክለቡ ዋጋ ሲከፍል ታይቷል። በትናንቱ ጨዋታም ኤፍሬም ድካሙን ሊያግዘው የሚችል ተጫዋች ያገኘው በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ አህመድ ረሽድ ተቀይሮ ከገባ በኋላ ነው።

 ከቡድናቸው የሚጠብቁትን ውጤትና ውበት ያለው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እንደፍላጎታቸው ማግኘት ያልቻሉት የቡና ደጋፊዎች  ውጤቱ ሽንፈት እንደሆነ ጨዋታው ብዙ ደቂቃዎች እየቀሩት በግልጽ በታየበት በትላንቱ ጨዋታ ቡድናቸው አልፎ አልፎ ያደርግ የነበረውን ጥሩ እንቅስቃሴ  ሙሉውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከስታዲየሙ ሳይወጡ የክለባቸውን ተጫዋቾች ሲያደንቁና ሲያበረታቱ ታይተዋል።  እንደዚህ አይነት የቡድን ፍቅር ይበልጥ ይቀጥል በሁሉም ተመልካች ዘንድ ይለመድ የሚያስብል ነው። ምክንያቱም ጨዋነትንና በሳልነትን  ከማሳየቱም በላይ ተጫዋቾችን ለቡድናቸውና ለደጋፊያቸው ታማኝ  እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው። የእግር ኳስ ጨዋታ እንደሚታወቀው አንድ ቡድን ሲያሸንፍ ብቻ መጨፈር ሳይሆን  ሲሸነፍም ቡድኑን ለሚቀጥለው ጨዋታ ዝግጁ ሆኖ እንዲቀርብ ማበረታታትን ይጠይቃል። ትላንት   በስታዲየሙ ተገኝተው የነበሩ የቡና ደጋፊዎች ይህንኑ ነበር ያደረጉት።  ለዚህም ተግባራቸው አድናቆታችንን ሳንገልጽ አናልፍም።

 በሌላ በኩል ፕሪሚየር ሊጉ ዛሬም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን በአዲስ አበባ ስታዲየም የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ የሚል ስያሜ በተሰጠው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይገናኛሉ። አዳማ ላይ አዳማ ከነማ ከሲዳማ ቡና፣ ሐዋሳ ላይ ሐዋሳ ከነማ ከመከላከያ እንዲሁም ወልድያ ላይ ወልድያ ከነማ ከወላይታ ድቻ ሲገናኙ ጎንደር ላይ ደግሞ ዳሽን ቢራ ከኤሌክትሪክ ጋር ይገናኛሉ። አሰላ ላይ ደግሞ ሙገር ሲሚንቶ ከአርባ ምንጭ ከነማ ይጫወታሉ። ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስና ሲዳማ ቡና በእኩል 38 ነጥብ በጎል ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ይመሩታል። 

ካሳ ሀይሉ 
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!