ፈረሰኞቹ ደረጃውን ተረጋግተው መምራት ጀመሩ
ሚያዚያ 19, 2007

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 20ኛው ሳምንት መርሃ ግብር ትናንት እና ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ተካሂደዋል። የሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በደደቢትና በኢትዮጵያ ቡና መካከል ተካሂዶ በደደቢት ሶስት ለባዶ አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሉን ተከትሎም ደደቢት በ17 ጨዋታ የነጥብ ድምሩን 25 አድርሶ ደረጃውን ሲያሻሽል ቡና በተከታታይ አራተኛ ነጥብ አልባ ጉዞው ሆኗል። ኢትዮጵያ ቡና በሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች አንድም ጎል ማስቆጠር ያልቻለ ብቸኛው ክለብ ሲሆን በሶስቱ ተከታታይ ጨዋታም አንድ ነጥብ ማግኘት አልቻለም። የፕሪሚየር ሊጉ 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ወልድያ ከነማ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ስድስት ነጥብ በማግኘት ከቡና የተሻለ ሆኖ ተገኝተዋል። 
StGeorge fans

ትናንት በተመሳሳይ ሰዓት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ አምስት ጨዋታዎች ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ተካሂደዋል። በተከታታይ ሶስት ጨዋታዎችን ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት ተስኖት የተቆየው ሐዋሳ ከነማ መከላከያን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ወደ አሸናፊነቱ ተመልሷል። ደረጃውንም ከ13ኛ ወደ 12ኛ ከፍ በማድረግ ከወራጅ ቀጠናው በመጠኑም እፎይ ማለት ችሏል። ሌላው የደቡብ ኢትዮጵያው ክለብ አርባምንጭ ከነማ በሜዳው ሙገር ሲሚንቶን አስተናግዶ አንድ ለባዶ አሸንፎ ሸኝቶታል። አርባምንጭ ከነማ ባለፈው ሳምንት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ባደረገው ጨዋታ ከሁለት ለባዶ ተመሪነት አንሰራርቶ ሁለት እኩል መውጣቱ ይታወሳል። 

በሜዳው የሽንፈት ጽዋን ተጎንጭቶ የማያውቀው አዳማ ከነማ ሲዳማ ቡናን ሶስት ለአንድ በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር የሊጉ መርሃ ግብር ይርጋዓለም ላይ ባደረጉት ጨዋታ አዳማ ከነማ ሁለት ለባዶ ማሸነፉ የሚታወስ ነው። ሲዳማ ቡና በበኩሉ በዓመቱ ካካሄዳቸው 20 ጨዋታዎች በደርሶ መልስ ሁለት ጊዜ የተሸነፈ ሲሆን በሜዳው በቅዱስ ጊዮርጊስና በአዳማ ከነማ ተሸንፎ የነበረ ሲሆን ከሜዳው ውጭ ከሁለቱ ቡድኖች ጋር ተጫውቶ በድጋሚ ተሸንፏል። አዳማ ከነማ በበኩሉ በሜዳው አስር ጨዋታዎችን አካሂዶ በአንዱም ሳይሸነፍ በመጓዝ የመጀመሪያውና ብቸኛው ክለብ ሆኗል። አዳማ ከነማ ነጥቡን 31 በማድረስ ከንግድ ባንክ በሁለት ነጥብ ብቻ ተበልጦ አራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።  

ከመደበኛ ስታዲየሙ የጎንደሩ ፋሲለደስ ስታዲየም ወደ ባህር ዳር ተጉዞ በባህርዳር ሁለገብ ብሔራዊ ስታዲየም ኤሌክትሪክን የገጠመው ዳሽን ቢራ ሁለት ለአንድ አሸንፏል። ዳሽን ቢራ ከሊጉ የመውረድ ስጋቱን በመጠኑም ቢሆን እፎይ ያለበትን ሙሉ ሶስት ነጥብ እንዲያገኝ ሁለቱን የማሸነፊያ ጎሎች ያስቆጠሩት ከኢትዮጵያ ቡና በውሰት የተዘዋወረው ቶጓዊው ኤዶም እና ይተሻ ግዛው ናቸው። ዳሽን ቢራ በዚህ የውድድር ዓመት በአንድ ጨዋታ ሁለት ጎል ያስቆጠረበት የመጀመሪያው ጨዋታም ሆኗል። ድሉን ተከትሎ ዳሽን ቢራ ነጥቡን 22 በማድረስ 10ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ሲያስችለው በሙገር መሸነፍ ደረጃው እንዳይወርድ የተጠቀመው ኤሌክትሪክ በ21 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን እንደዘገበው ከጨዋታው በኋላ አስተያየቱን የሰጠው የዳሽኑ ተጠባባቂ ዋና አሰልጣኝ ካሊድ መሃመድ “ሜዳው ለጨዋታ ምቹ ስለሆነልን በፈለግነው መንገድ እንድንጫወት አስችሎናል። በምንፈልገው መንገድ በመጫወታችንም ልናሸንፍ ችለናል። ቀጣይ ጨዋታዎቻችንን በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው መውጣት እንችላለን” ሲል የተናገረ ሲሆን ትናንት ድል ባደረጉበት ስታዲየም ከአዳማ ከነማ ጋር በድጋሚ እንደሚጫወቱም ተናግሯል። የተሸናፊው የኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ በበኩላቸው “ጨዋታው ጥሩ ነበር። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ያገኘናቸውን የጎል እድሎች መጠቀም ባለመቻላችን ለሽንፈት ተዳርገናል። ሁለቱም ጎሎች የተቆጠሩብን በራሳችን ተከላካዮች ስህተት ነው” ሲሉ ተናግረዋል። 

ሌላው የአማራ ክልሉ ክለብ ወልድያ ከነማ በዓመቱ ለሶስተኛ ጊዜ ሙሉ ሶስት ነጥብ ያገኘበትን ጨዋታ ትናንት ወላይታ ድቻን አንድ ለባዶ በማሸነፍ ድል አስመዝግቧል። ከዳሽን ቢራ ጋር ስኬት አልባ ጉዞ ሲያሳልፍ የቆየው ፍጹም ደስአለው የወልድያ ከነማን ብቸኛና የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሯል። ዳሽን ቢራ ፕሪሚየር ሊጉን ሲቀላቀል የብሔራዊ ሊጉ ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀው ፍጹም ደስአለው ክለቡ ፕሪሚየር ሊጉን ከተቀላቀለ በኋላ አንድ ጊዜ ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኖት ቆይቶ ነበር። የጎል ድርቁን ተከትሎም በዳሽን ቢራ ቦታ ያጣው ፍጹም ወደ ወልድያ ተዘዋውሯል። 

የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ ነው። የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው የሁለቱ ክለቦች ግጥሚያ በሳምንቱ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ብቸኛው ጨዋታም ነው። ንግድ ባንክ መሪ የሆነባትን ጎል ፍሊፕ ዳውዝ ሲያስቆጥር ፈረሰኞቹን ከሽንፈት የታደገች ጎል ያስቆጠረው ደግሞ አማካይ ተከላካዩ ምንተስኖት አዳነ ነው። ፈረሰኞቹ ትናንት አቻ መለያየታቸውን ተከትሎ በአዳማ ሶስት ለአንድ የተሸነፈውን ሲዳማ ቡናን በአንድ ነጥብ በመብለጥ የሊጉን መሪነት በብቸኝነት መያዝ ችለዋል።

 ፍሊፕ ዳውዝ ትናንት በፈረሰኞቹ መረብ ላይ ያስቆጠራት ጎል የሊጉን ኮከብ ጎል አግቢነት ደረጃ በብቸኝነት እንዲመራ አስችሎታል። ዳውዝ በ14 ጎል የሊጉን ከፍተኛ ጎል አግቢነት እየመራ ሲሆን ተከታዩን ደረጃ የያዙት የቡናው ቢኒያም አሰፋ በ13 ጎል እና የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኖሜ በ12 ጎሎች ናቸው።

ካሳ ሀይሉ 
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!