በትዕይንቶች ታጅቦ የተጠናቀቀው የደደቢትና የመከላከያ ጨዋታ
ሚያዚያ 22, 2007

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር አንድ ተስተካካይ ጨዋታ በመከላከያና ደደቢት መካከል ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም  ተካሂዶ ነበር። ኢትዮፉትቦል ዶትኮም ቀደም ብሎ ውጤቱን እንደገለጸው ደደቢት በሳሙኤል ሳኖሜ ብቸኛ ጎል አንድ ለባዶ አሸንፏል። በጨዋታው የተፈጠሩትን ነጥቦች በተመለከተ ከዚህ በታች በዝርዝር እናቀርባለን። 

የጨዋታው አጀማመር

ባለፈው ቅዳሜ ከሰዓት ደደቢት ኢትዮጵያ ቡናን ሶስት ለባዶ ካሸነፈው ቡድን ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ የገቡት ደደቢቶች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የመሃል ሜዳውን የበላይነት መቆጣጠር ችለው ነበር። የመሃል ሜዳ የበላይነት የተወሰደባቸው የገብረመድህን ሀይሌ ልጆች ደግሞ በሙሉዓለም ጥላሁን ተደጋጋሚ ጥረት ብልጫውን ለመቀልበስ ጥረት ማድረግ ችለዋል። የተክለወልድን ቦታ መሸፈን ያልቻለው መከላከያ በተለይ አማካዮቹ ሚኬኤሌ ደስታ እና ወጣቱ ኡታግ በተጋጣሚያቸው ሳምሶን ጥላሁንና ሸይቩ ጅብሪል ተበልጠው አምሽተዋል። በተለይ ኡታግ የተባለው የመከላከያው አማካይ ተጫዋች የተሰጠውን ሀላፊነት መወጣት ተስኖት የታየ ሲሆን የእሱን ድክመት ደደቢቶች ተጠቅመው በመከላከያ ላይ ተደጋጋሚ የጎል ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር። የፍሬው ሰለሞንና በሀይሉ ግርማ አለመኖርም መከላከያን የመሃል ሜዳ የበላይነት እንዲወሰድበት አድርጎታል ማለት ይቻላል። 

የጎል ሙከራ

የጨዋታውን የመጀመሪያ የጎል ሙከራ ያደረገው የመከላከያው መሃመድ ናስር ነበር። መሃመድ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ በጥሩ ሁኔታ መቆጣጠር ባለመቻሉ ኳሷን አጠንክሮ ወደ ጎል አለመሞከሩ እንጅ ለጎል የቀረበች አጋጣሚ ነበረች። ከመሃመድ ሙከራ በኋላ ደግሞ ሙሉዓለም ጥላሁን አስተካክሎ ያቀበለውን ኳስ 15 ቁጥሩ ሙሉጌታ አስፋው ከበረኛ ጋር ተገናኝቶ አገባ ሲባል ከጎሉ መስመር ውጭ የላካት ኳስ በመከላከያ በኩል የምታስቆጭ የጎል አጋጣሚ ነበረች። መሃመድ ናስር በአንድ አጋጣሚ አግኝቶ ያልተጠቀመባት ኳስ ደግሞ የአጥቂው ዝግጁ ሆኖ አለመጠበቁ እንጅ ጎል ለመሆን በእጅጉ የቀረበች ነበረች። 

በደደቢት በኩል አጥቂው ሳሙኤል ሣኖሜ የሞከራቸውን ተደጋጋሚ ሙከራዎች ጀማል ጣሰው አድኗል። ከሳኖሜ ሁለት ያለቀላቸው ሙከራዎች በተጨማሪ በረከት ይሳቅ ያባከናቸው ተደጋጋሚ ሙከራዎችና ብርሃኑ ቦጋለ ከርቀት አክርሮ የሞከረው ሙከራ በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የታዩ የጎል ሙከራዎች ናቸው።
ሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ እንደተጀመረ በሁለት ደቂቃ ልዩነት ደደቢቶች ተደጋጋሚ የጎል ሙከራዎችን አድርገው አንደኛዋ ፍሬ አፍርታላቸዋለች። ጎሏን ያስቆጠረው ናይጄሪያዊው ሣሙኤል ሳኖሜ የመከላከያ ተከላካዮችን ያታለለበት መንገድና ጎሏን ያስቆጠረበት ክህሎቱ በተመልካች አድናቆትን እንዲያሰጠው አስችሎታል። ጎሏም በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን ጎሎች 13 አድርሳለታለች። 
ከዚህች ጎል በኋላ ደደቢት ተጨማሪ ጎሎችን ለማግኘት ይበልጥ ተጭኖ የተጫወተ ሲሆን በተለይ ተከላካዩ ስዩም ተስፋዬ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ጎል የላካት ኳስ የጎሉን ቋሚ ብረት ለትማ ተመልሳለች። አማካዮቹ ታደለ መንገሻ እና ብርሃኑ ቦጋለ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን የተወሰኑት በመከላከያው ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰው ሲመለሱ ቀሪዎቹ ደግሞ ከጎሉ ብረት በቅርብ ርቀት ወደ ውጭ ወጥተዋል። በመከላከያ በኩል ያገኟቸውን የጎል እድሎች ወደ ፍሬ መቀየር የሚችል አጥቂ ባለመኖሩ እስከ 80ኛው ደቂቃ ይህ ነው የሚባል የጎል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። 

Dedebit Vs Defence

ኮከብ ጎል አግቢው ግብ ጠባቂ

አማካዮቹን ሸይቩ ጅብሪልንና ሳምሶን ጥላሁንን በእረፍት ቀይሮ ያስወጣው የደደቢቱ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሣህሌ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 15 ደቂቃዎች ሲቀሩት አማከዩን ብርሃኑ ቦጋለን ከቀየረ በኋላ ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት በሰራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ ተደርጓል። ተቀያሪ ተጫዋቾቹን የጨረሰው ደደቢት ቀሪዎቹን 15 ደቂቃዎች የጎሉን መስመር እንዲጠብቅለት በኮከብ ጎል አግቢው ሳሙኤል ሣኖሜ ላይ እምነቱን እንዲያሳድር ተገደደ። 

ጎል ለማሰቆጠር ሲቅበጠበጥ እንጅ የጎል መስመር ሲጠብቅ የማይታወቀው ናይጄሪያዊው ኮከብ ሰማያዊ ማሊያውን አውልቆ የግብ ጠባቂዎችን የተለየ ቀለም ያለው ማሊያ ለብሶ እጆቹን በጓንት ሸፍኖ ከጎሉ መሃል ቆሞ በቆየባቸው 15 ደቂቃዎች የመከላከያዎችን ተደጋጋሚ የጎል ሙከራ በሚገባ ሲመክት ታይቷል። በተለይ ከቁመቱ በላይ የተሞከሩበትን ሙከራዎች ያዳነበት ችሎታውና ኳስን የሚይዝበት መንገድ “ልምድ ያለው ጎል ጠባቂ” አስመስሎታል። የሳኖሜን የጎል ዘበኝነት ብቃት የተመለከቱ ደጋፊዎች አድናቆታቸውን ችረውታል። 
በእለቱ አንድ ጎል አግብቶ እና አራት የሚሆኑ የጎል ሙከራዎችን አድኖ ቡድኑ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ከፍተኛ ሚና የተጫወተው ሳሙኤል ሳኖሜ የእለቱ ልዩነት ፈጣሪ ሆኖ አምሽቷል። ደደቢት ያለፉትን ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሲያሸንፍ ሳሙኤል ሳኖሜ አምስት ጎሎችን በማስቆጠር ወሳኝነቱን አስመስክሯል።
በሳኖሜ ጎሎች ታግዞ ውጤቱን እያሳመረ የመጣው ደደቢት አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ31 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። ተስተካካይ ጨዋታውን ማሸነፍ ከቻለ ሶስተኛ ደረጃን ይይዛል። የትናንቱን ጨምሮ በተከታታይ ሶስት ጨዋታዎችን የተሸነፈው መከላከያ በበኩሉ 26 ነጥብ ይዞ ዘጠንኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ሰሞኑን የጎል አኬር የቆመለት ሳሙኤል ሳኖሜ 13 ጎሎችን አስቆጥሮ ከኢትዮጵያ ቡናው ቢኒያም አሰፋ ጋር በመስተካከል ከንግድ ባንኩ ፍሊፕ ዳውዝ በአንድ ጎል ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ካሳ ሀይሉ 
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!