ጎል አስቆጣሪዎቹና የጎል መስመር ጠባቂዎቹ በውጭ አገር ተጫዋቾች የተሞሉበት ፕሪሚየር ሊግ
ሚያዚያ 23, 2007

ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ያለፉትን አምስት ዓመታት የጎሉን መስመር በንቃት የጠበቀለት ሮበርት ኦዶንካራ የተባለው ዩጋንዳዊ ነው። የናዝሬቱ አዳማ ከነማ ደግሞ በዚህ አመት “ፎዬ” የተባለ ዩጋንዳዊ ጎል ጠባቂ አስፈርሞ የጎሉን መስመር ሲያጠናክር ታይቷል። የውጭ አገር ጎል ጠባቂዎችን በሊጉ መብዛት በተመለከተ ለአገራችን እግር ኳስ የሚኖረውን አወንታዊና አሉታዊ ጎኖች በተመለከተ ኢትዮፉትቦል ዶትኮም ከዚህ ቀደም ሰፋ ያለ ዘገባ ማቅረቧ ይታወሳል። ድረ ገጻችን የውጭ አገር ጎል ጠባቂዎች መብዛታቸውን በተመለከተ ያቀረበችውን ዘገባ ተከትሎ በርካታ የመገናኛ ብዙሃንና የስፖርት ቤተሰብ መነጋገሪያ አድርጎት ቆይቶ ነበር። 

ዛሬ ደግሞ በሊጉ እየተቆጠሩ ካሉ ጎሎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን የውጭ አገር ተጫዋቾች ማስቆጠራቸውን በተመለከተ ዝግጅት ክፍላችን ከዚህ በታች ያለውን ዘገባ ለመስራት ተገዷል። ዘገባው “ለምን የውጭ አገር ተጫዋቾች በሊጋችን በዙ?” የሚል አንደምታ የለውም። ምክንያቱም በየትኛውም ዓለም በሚገኙ የእግር ኳስ ሊጎች በሙሉ አገር በቀል ተጫዋቾች ሲጫወቱ አይታይም። የዘገባችን ትኩረት የሚያጠነጥነው አሃዛዊ መረጃዎችን በማቅረብ በቀረበው መረጃ ላይ ለእግር ኳሳችን እድገት የሚኖረውን ጠቀሜታ እና አሉታዊ ጎን መመልከት ይሆናል። 

27/40 የጋራ ጎል

በፕሪሚየር ሊጉ የኮከብ ጎል አግቢውን መስመር ሶስት ተጫዋቾች በጋራ 40 ጎሎችን አስቆጥረው ይመሩታል። ጎሎቹን ያስቆጠሩት ሁለት ናይጄሪያውያን ተጫዋቾችና አንድ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ናቸው። ናይጄሪያውያኑ በጣምራ 27 ሲያስቆጥሩ ኢትዮጵያዊው የቡና አጥቂ ቢኒያም አሰፋ ደግሞ 13 ጎል አስቆጥሯል። 27 ጎሎችን በጋራ ያስቆጠሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ፍሊፕ ዳውዝ 14 እና የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኖሜ 13 ጎሎችን በማስቆጠር ነው። ይህ ደግሞ ከ40 ጎሎች 72.5 ፐርሰንቱን ማስቆጠር ችለዋል ማለት ነው። 

እንደ ሁለቱ ናይጄሪያውያን አጥቂዎች ባይሆንም በአነስተኛ የጎል ባለቤትነት ስማቸውን ካስመዘገቡት የውጭ አገር አጥቂዎች መካከል አዲሱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ፈራሚ ብሪያን ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች ለአዲሱ ክለቡ ጎሎችን በተከታታይነት እያስቆጠረ ይገኛል። የሲዳማ ቡናው አንጋፋ አጥቂ ኤሪክ ሙራንዳም ለክለቡ የዚህ ዓመት ጥንካሬ ተጠቃሽ ከሆኑት መካከል አንዱ ነው። አጥቂው የእድሜው መግፋት ሳይበግረው በተከታታይ ጎሎችን በማስቆጠር ላይ ይገኛል። ከኢትዮጵያ ቡና ወደ ዳሽን ቢራ በውሰት የተዘዋወረው ቶጓዊው ኤዶምም ቢሆን በጎል አስቆጣሪዎች መዝገብ ስሙን ማስመዝገብ ችሏል።  

የውጭ አገር አጥቂዎች መብዛት የሚኖረው ሚና

ባለፉት አስር ዓመታት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀ እንግሊዛዊ ተጫዋች የለም። በስፔን ላሊጋም ቢሆን እንደ ሊዮኔል ሜሲ ክርስቲያኖ ሮናልዶና ሳሙኤል ኤቶ አይነት ተጫዋቾች እያሉ ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀ ስፔናዊ ተጫዋች አልታየም። በጣሊያን ሴሪአ አንቶኒዮ ዲናታሊ እና አልቤርቶ ጂላርዲኖ የተባሉ አጥቂዎች የአገራቸውን ሊግ በኮከብ ጎል አግቢነት ማጠናቀቅ ቢችሉም አብዛኛውን ጊዜ ግን የውጭ አገር ተጫዋቾች ናቸው በበላይነት ማጠናቀቅ የቻሉት። 

ታላላቆቹን የአውሮፓ ሊጎች የውጭ አገር ተጫዋቾች ኮከብ ጎል አግቢ ሆነው በማጠናቀቃቸው የአገሪቱን እግር ኳስ ደረጃ አውርዶታል፤ የአገሪቱን አጥቂዎች ብቃትም ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል ማለት አይደለም። ለዚህም ነው እንደ ሪያል ማድሪድ ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድ አይነት ክለቦች ስፔናዊ ያልሆኑ አጥቂዎችን ከሌላ አገር በመግዛት የክለባቸውን ደረጃ ከፍ ማድረግ ያቻሉት። ተጫዋቾቹ ማለትም እንደ ሊዮኔል ሜሲ ኔይማር ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሉይስ ሱዋሬዝ ጋሬዝ ቤል እና ማሪዮ ማንዙጊች አይነት ተጫዋቾች ለክለቦቻቸው ከሜዳ ውጭም ሆነ በሜዳ ላይ የሚሰጡት ጠቀሜታ የጎላ ነው። 

ከዚህ በተጓዳኝ በአገራችን የውጭ አገር ተጫዋቾች በመብዛታቸው ለአገር በቀል ተጫዋቾች የውድድር መንፈስን የሚጨምር ከመሆኑም በላይ የአገራችንን እግር ኳስ የውጭ አገር ተጫዋቾች በመጡባቸው አገሮች እንዲተዋወቅ የማድረግ ስራ ይሰራሉ ተብሎ ይታሰባል። ነገር ግን ተጫዋቾቹ ብቃታቸው ከኢትዮጵያውያኑ የማይሻሉ ከሆነ እና ከሜዳ ውጭ ባላቸው ህይወትም አርአያ መሆን የማይችሉና የማስታወቂያ ስራ የማይሰሩ ከሆነ የተጫዋቾቹ ወደ አገር ቤት መምጣት አስፈላጊነቱ አጠያያቂ ነው። 

በዚህ ሃሳብ ዙሪያ አንባቢያን ሃሳባቸውን በመስጠት እንዲወያዩበት እንጋብዛለን።  
  
ካሳ ሀይሉ 
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!