የፕሪሚየር ሊጉ 21ኛ ሳምንት ወሳኝ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል
ሚያዚያ 23, 2007

“ቅጣት ላይ የቆየው ምንያህል ተሾመ በዚህ ወሳኝ ሰዓት ወደ ጨዋታ መመለሱ ለቡድናችነ ጥንካሬ ወሳኝ ነው”   ዘሪሁን ሸንገታ  ለኢትዮ ፉትቦል ዶትኮም

“በርካታ ተጫዋቾቻችን ጉዳት ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን ከጉዳት ነጻ በሆኑትና ከጉዳት ባገገሙት ተጫዋቻችን በቂና ጥሩ ዝግጅት አድርገናል” አንዋር ያሲን ለኢትዮ ፉትቦል ዶትኮም

“በተጫዋቾቼ ላይ የፈጠርኩት አዲስ ነገር የለም። ቡድኑ ላይ የሰራሁት ብቸኛ ነገር ‘ማሸነፍ እንደሚችሉ’ በስነ ልቦና የማዘጋጀት ስራ ነው” ውበቱ አባተ ለኢትዮ ፉትቦል ዶትኮም

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ፣ ነገ እና እሁድ በሚካሄዱ ወሳኝ ጨዋታዎች ቀጥሎ ይውላል። ንግድ ባንክ  ከደደቢት ፤ ሲዳማ ቡና ከሐዋሳ ከነማ  የሚያደርጉት ጨዋታ ወሳኝ ናቸው።

እሁድ ንግድ ባንክና ደደቢት እንዲሁም  ሲዳማ ቡናና ሐዋሳ ከነማ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ከፍተኛ ትኩርት ተሰጥቷቸዋል።  ሶስት ጨዋታዎች በተከታታይ የተሸነፈውና  በሶስት ጨዋታ አንድም ጊዜ ኳስና መረብን ማገናኘት ያልቻለው ኢትዮጵያ ቡና ዛሬ ከቀኑ 10፡00 የሚያደርገውን ጨዋታታም ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ቡና ማሸነፍ ካልቻለ ከባድ ቀውስ ውስጥ የሚወድቅ ነው የሚሆነው። በአንጻሩ ቡናማዎቹ ድል የሚያደርጉ ከሆነ ከነበረባቸው የውጤት ቀውስ በመጠኑም ቢሆን እፎይታ የሚሰማቸው ይሆናል። 

በርካታ ቋሚ ተጨዋቾቹ ጉዳት ላይ የሚገኙበት የኢትዮጵያ ቡናው ተጠባባቂ ዋና አሰልጣኝ አንዋር ያሲን ከኢትዮፉትቦል ዶትኮም ጋር ባደረገው የስልክ ቃለ ምልልስ “በርካታ ተጫዋቾቻችን ጉዳት ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን ከጉዳት ነጻ በሆኑትና ከጉዳት ባገገሙት ተጫዋቻችን በቂና ጥሩ ዝግጅት አድርገናል” ሲል ተናግሯል። በአሁኑ ወቅት ቡድኑ ከውጤት ቀውሱ በተጨማሪ በጉዳት እየታመሰ ሲሆን ከአሰልጣኙ ባገኘነው መረጃ መሰረት አምበሉ ዳዊት እስጢፋኖስንና ኮከብ ጎል አስቆጣሪውን ቢኒያም አሰፋን ጨምሮ ኤፍሬም ወንደወሰን፣ አስቻለው ግርማ እና ኤሊያስ ማሞ ጉዳት ላይ ናቸው። ቀደም ብለው የተጎዳው ዴቪድ በሻህም አላገገም። በምትኩ ጥላሁን ወልዴ እና ካሜሩናዊው ተከላካይ ኦሊቨር እንዲሁም ደረጀ ሀይሉ ከጉዳታቸው አገግመው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ተናግሯል። 

አዳማ ከነማ በተከታታይ እያሸነፈ መምጣቱ የዛሬውን ጨዋታ ተጠባቂ እንዲሆን ያደርገዋል። የዓመቱን የመጀመሪያ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታቸውን አዳማ ላይ ሶስት እኩል መለያየታቸው ይታወሳል። በዚያ ጨዋታ ለኢትዮጵያ ቡና ሶስቱን ጎሎች ካሰቆጠሯቸው ተጫዋቾች መካከል ሁለቱ በዛሬው ጨዋታ አይሰለፉም። 

ይርጋዓለም ላይ ሲዳማ ቡና ከሐዋሳ ከነማ የሚያካሂዱት የሲዳማ ደርቢ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ጨዋታ ነው። ባለፈው ሳምንት በአዳማ ከነማ የሶስት ለአንድ ሽንፈት የደረሰበት ሲዳማ ቡና ሐዋሳን በማሸነፍ ወደ ዋንጫው የሚያደርገውን ጉዞ ለማሳመር እንደሚጫወት ይጠበቃል። በአንጻሩ ሐዋሳ ከነማ የመውረድ ስጋት አፍንጫው ስር ሆኖ የሚያንዣብብበት በመሆኑ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የግድ ጨዋታውን ማሸነፍ እንዳለበት ስለሚያውቅ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የሳምንቱን ተጠባቂ ጨዋታ ሆኗል። 

የሀዋሳ ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለዝግጅት ክፍላችን “በተጫዋቾቼ ላይ የፈጠርኩት አዲስ ነገር የለም። ቡድኑ ላይ የሰራሁት ብቸኛ ነገር ‘ማሸነፍ እንደሚችሉ’ በስነ ልቦና የማዘጋጀት ስራ ነው” ብሏል። ሐዋሳ ከነማ በዓመቱ መጀመሪያ ከአስር ሚሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ ለተጫዋቾች ዝውውር ያወጣ ቢሆንም እንደ ቀድሞው በጥንካሬው መጓዝ ተስኖት በወራጅ ቀጠናው ውስጥ የሚገኝ ክለብ ሆኗል። የክለቡን ደካማ ውጤት ተከትሎም በዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ አሰልጣኞችን ማሰናበቱ ይታወቃል። በቅርቡ ቡድኑን የተረከበው አሰልጣኝ ውበቱ አባታ በስድስት ጨዋታዎች ቡድኑን በመምራት በሶስቱ ሲያሸንፍ በአንዱ አቻ ወጥቶ በሁለቱ ተሸንፏል። 

ሌላው የሳምንቱን ተጠባቂ ጨዋታ የምታስተናግደው የኦሮሚያ ክልሏ አሰላ ከተማ ነች። የአሰላው አረንጓዴ ስታዲየም የሚያስተናግደው የሙገር ሲሚንቶንና የሊጉን መሪዎች የፈረሰኞቹን ጨዋታ ነው። ብራዚላዊውን አሰልጣኝ አሰናብተው በወጣቶቹ ዘሪሁን ሸንገታ እና ፋሲል ተካልኝ እየተመሩ ያደረጓቸውን ሁሉንም ጨዋታዎች በድል የተወጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ባለፈው ሳምንት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አንድ እኩል መለያየታቸው ይታወሳል። 

ጨዋታውን አስመልክቶ አስተያየቱን ለኢትዮፉትቦል የገለጸው የፈረሰኞቹ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ “ቅጣት ላይ የቆየው ምንያህል ተሾመ በዚህ ወሳኝ ሰዓት ወደ ጨዋታ መመለሱ ለቡድናችነ ጥንካሬ ወሳኝ ነው” ያለ ሲሆን ዘሪሁን አያይዞም ቡድኑ በሙሉ የራስ መተማመንና በጥሩ ዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግሯል። በቡድኑ ውስጥ የተጎዳ ተጫዋች መኖሩን ላቀረብንለት ጥያቄ መልስ የሰጠው ዘሪሁን ሸንገታ፤ “አሉላ ግርማ እና ፋሲካ አስፋው ጉዳት ላይ በመሆናቸው ለዛሬው ጨዋታ አይሰለፉም። ከእነዚህ ተጫዋቾች ውጭ ሁሉም የቡድናችን አባሎች በሙሉ የራስ መተማመንና ጥሩ ዝግጅት ላይ ይገኛሉ። ከእግዚያብሔር ጋር ዋንጫውን ለማንሳት ተዘጋጅተናል” ሲል መልሷል። ነገ ጠዋት ወደ አሰላ የሚጓዙት ፈረሰኞቹ ፕሪሚየር ሊጉን በ39 ነጥብ እየመሩ ይገኛሉ። ካሳ ሀይሉ 
ለኢትዮ ፉትቦል ዶትኮም


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!