ኢትዮጵያ ቡና በቤተሰብ ሩጫ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ሰበሰበ
ሚያዚያ 25, 2007

“ውጤት በበጠፋበት ሰዓት ከክለባቸው ጎን የሆኑ ደጋፊዎቻችንን ከልብ እናመሰግናቸዋለን” አቶ ኢሳያስ ታፈሰ የክለቡ ማርኬቲንግ ሀላፊ ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም

 “ክለባችንን ለመደገፍ ውጤት አይገድበንም” ደጋፊዎች ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም
Buna Annual Family Race

ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለቡ አካባቢ እያስገነባ ላለው የተጫዋቾች መኖሪያ ካምፕ ግንባታ የገቢ ማሰባሰቢያ የሩጫ ውድድር አዘጋጅቷል። 
Buna Annual Family Race


መነሻውንና መድረሻውን ካምፑ ከሚገነባበት አካባቢ ያደረገውና ስምንት ኪሎ ሜትር የሸፈነውን የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ስምንት ሺህ የክለቡ ደጋፊዎች እንደታደሙበት ከክለቡ የደረሰን መረጃ ያመለክታል። የክለቡ ማርኬቲንግና ገበያ ልማት ክፍል ሀላፊ አቶ ኢሳያስ ታፈሰ ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም በስልክ እንደገለጹት በሩጫ ውድድሩ ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ መገኘት ችሏል። 
Buna Annual Family Race

Buna Annual Family Race


አቶ ኢሳያስ ከኢትዮፉትቦል ዶትኮም ጋር በስልክ ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ለውድድሩ የተዘጋጀውን ስምንት ሺህ ትኬት በሙሉ ሽጠናል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በስፖንሰር የተገኘ ገንዘብን ጨምሮ ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ መሰብሰብ ችለናል። በተለይ በዚህ ወቅት ሜዳ ላይ ውጤት በጠፋበት ሰዓት የክለባችን ደጋፊዎች ለክለባቸው ያሳዩትን አጋርነት ክለቡ ያመሰግናል። እውነተኛ የክለባችን ደጋፊዎች ስለሆኑ እንኮራባቸዋለን” ብለዋል። በእለቱ ሩጫውን ሀበሻ ቢራ የግማሽ ሚሊዮን ብር ስፖንሰር ያደረገ ሲሆን ወርቤክ ኢንተርናሽናል 150 ሺህ ብር እንዲሁም ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ጀስቲስ ኮንስትራክሽን፣ ራስ ሂል ባር እና ሬስቶራንት እና ብርሃን ኢንሹራንስ ኩባንያ እያንዳንዳቸው የ75 ሺህ ብር ስፖንሰር ማድረጋቸውን ከክለቡ የደረሰን መረጃ አመልክቷል። 
Buna Annual Family Race
Buna Annual Family Race

የክለቡ ደጋፊዎች በበኩላቸው “ለክለባችን ያለንን ታማኝነትና ፍቅር ለመግለጽ ውጤት መሰረት ሊሆነን አይችልም” ሲሉ ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም ገልጸዋል። ቀደም ብሎ የኢትዮፉትቦል ዶትኮም ዘጋቢ በካታንጋ ተገኝቶ ቡድናቸውን ሲደግፉ የነበሩ የክለቡን ደጋፊዎች ባነጋገረበት ወቅት “ኢትዮጵያ ቡና ሀብቱ ደጋፊው ነው። እኛ ደግሞ ክለባችንን የምንደግፈው ውጤት ስለሚያመጣ ሳይሆን ሜዳ ላይ ማራኪ ጨዋታ ስለሚያሳየን ነበር። በዚህ ዓመት ከክለባችን የምንፈልገውን ማግኘት ባንችልም ነገም ሌላ ቀን በመሆኑ ክለባችንን ከመደገፍ የሚያግደን የለም” ሲሉ ገልጸውለት ነበር። 

በዛሬው የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድርም ክለቡ ያዘጋጀውን የመግቢያ ትኬትና የመሮጫ ካናቲራ በመግዛት ለክለባቸው ያላቸውን ፍቅር አሳይተዋል። የእነዚህ ደጋፊዎች ድርጊት የክለቡን አመራርና ተጫዋቾች ልብ የነካ እንደነበረም በቦታው የነበሩ የኢትዮፉትቦል ዶትኮም ምንጮች ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ቡና በ21 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች 28 ነጥብ ብቻ በመያዝ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ካሳ ሀይሉ 
ለኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!