የፕሪሚየር ሊጉ 21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅኝት
ሚያዚያ 26, 2007

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በአራት ከተሞች ሰባት ጨዋታዎችን አካሂዷል። በእነዚህ ሰባት ጨዋታዎች አራቱ አንድ ለባዶ በሆነ ተመሳሳይ ውጤት ሲጠናቀቁ ሁለቱ ደግሞ ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት ተጠናቀዋል። በሳምንቱ በርካታ ጎሎችን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው ትናንት በደደቢት ሶስት ለባዶ በመሸነፉ። በሳምንቱ ከተቆጠሩት 13 ጎሎች መካከል ሶስቱን ጎሎች ያስቆጠሯቸው የውጭ አገር ተጫዋቾች ናቸው። በጨዋታዎቹ ዙሪያ አንዳንድ ነጥቦች ከዚህ በታች እናቀርባለን። 

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከደደቢት 

ሁለት ናይጄሪያውያን አጥቂዎች፣ ሁለት ኳስን ተቆጣጥሮ የሚጫወት አሰልጣኝ የሚያሰለጥናቸው፣ ሁለቱም በአንድ አጥቂ ላይ ብቻ የተንጠለጠሉ ክለቦች ናቸው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ደደቢት። ሁለቱ ቡድኖች ትናንት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በካምቦሎጆ ፍልሚያቸውን ከማካሄዳቸው በፊት የበርካቶችን ትኩረት ስቦ የነበረው ከሁለቱ ናይጄሪያውያን አጥቂዎች የትኛው ጎልቶ ይወጣል? ከሁለቱ አሰልጣኞች ፍልስፍና የማንኛው አሸናፊ ይሆናል? የሚሉ ነጥቦች ነበሩ። የንግድ ባንኩ ኮከብ ጎል አግቢ ፍሊፕ ዳውዝ በምግብ መመረዝ ምክንያት በጉዳት የእለቱ ጨዋታ ያለፈው ሲሆን ሌላኛው ናይጄሪያዊ አጥቂ ሳሙኤል ሳኖሜ ግን ደደቢትን አሸናፊ ካደረጉ ሶስት ጎሎች አንዷን በስሙ አስመዝግቧል። 

የመሃል ሜዳ የኳስ ቁጥጥር ላይ ትኩረት ያደረገ ጨዋታ በታየበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ሳሙኤል ሳኑሜ ከእረፍት በፊት እንዲሁም በረከት ይሳቅ እና ሽመክት ጉግሳ ከእረፍት በኋላ ለደደቢት ጎሎቹን አስቆጥረዋል። ሳሙኤል ሳኖሜ ላስቆጠራት ጎል የንግድ ባንክ ተከላካዮች ስህተት እና የግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ ድክመት በግልጽ የታየባት ነበረች። ሳኑሜም በነጻ ያገኛትን ድንቅ ስጦታ በከንቱ ማባከን ባለመፈለጉ የግብ ጠባቂውን ደካማ ጎን አይቶ ጎሏን በግሩም ሁኔታ አስጥሯታል። 

ከእረፍት መልስ በነበረው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ደደቢት ሳምሶን ጥላሁንን በሰለሞን ሃብቴ ቀይሮ በመግባት የመሃል ሜዳውን ይበልጥ አጠናክሮ ታይቷል። ሶስቱ የቡድኑ አጥቂዎች የጋራ ጥምረት የታየባትን ጎል በረከት ይሳቅ በ59ኛው ደቂቃ ሲያስቆጥር አጥቂዎቹ ሳሙኤል ሳኑሜ፣ ዳዊት ፈቃዱ እና በረከት ይሳቅ የነበራቸው ውህደት በተመልካች አድናቆት የተቸራቸው ሆኗል። በዲስፕሊን ምክንያት ክለቡ ቀጥቶት የቆየው ሽመክት ጉግሳ ከቅጣቱ ተመልሶ በ80ኛው ደቂቃ ዳዊት ፈቃዱን ቀይሮ በመግባት የመጀመሪያ ጎሉን አስቆጥሯል። የሽመክት ጎል ደግሞ የልጁን ብቃት አጉልታ ያሳየች ናት። 

ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን ለጋዜጠኞች የሰጡት የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች በጨዋታው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማሪያም “ሶስቱ የቡድናችን ወሳኝ አጥቂዎች በጉዳትና በቅጣት ባለመሰለፋቸው በተጋጣሚያችን የቡድን ጥልቀት የበላይነት እንዲወሰድብን አድርጎናል። በጣም ጥሩ ጨዋታ አድርገናል ነገር ግን ከእኛ በላይ ጥሩ የነበሩት ደደቢቶች አሸንፈዋል” ሲል የተናገረ ሲሆን ከደደቢት ጋር የመጨረሻ ጨዋታውን ያደረገውና ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ ከዋልያዎቹ ጋር ስራውን በይፋ የሚጀምረው ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሣህሌ በበኩሉ “ቡድኔ በሙሉ የራስ መተማመን ላይ ስለሆነ ጨዋታውን በሚገባ ተቆጣጥሮ አሸንፏል። የፍሊፕ ዳውዝን አለመኖር ስናውቅ አጨዋወታችንን ለመለወጥ ብንገደድም ጨዋታውን መቆጣጠር ችለናል” ሲል ተናግሯል። 
ውጤቱን ተከትሎ ደደቢት በ34 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ንግድ ባንክ በያዘው 34 ነጥብ ላይ ረግቷል። ደደቢት ተስተካካይ አንድ ጨዋታ የሚቀረው ሲሆን ተስተካካይ ጨዋታውን ማሸነፍ ከቻለ ለዋንጫ ተፋላሚነቱን ያጠናክርለታል። 

መከላከያ ከወላይታ ድቻ

አንድ ለእናቱ የሆነውን አዲስ አበባ ስታዲየምን በጋራ ከሚጠቀሙ የአገራችን ክለቦች አንዱ የሆነው መከላከያ የትናንቱን ጨዋታ ያካሄደው በሜዳው ቢሆንም ስታዲየሙን ሞልተው የታዩት ግን የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ነበሩ። በበርካታ የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ታጅቦ የተጫወተው መከላከያ ከሶስት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል። ጨዋታው ከእረፍት በፊትና ከእረፍት በኋላ ሁለት ገጽታዎችን ተላብሶ የተካሄደ ጨዋታ ነበር። ከእረፍት በፊት በመሃል ሜዳ የተገደበ ጨዋታና ሀይል የተቀላቀለበት አጨዋወት በሁለቱም ቡድኖች በኩል የታየ ሲሆን ከእረፍት መልስ ደግሞ ሁለቱም ክለቦች ወደ ተጋጣሚዎቻቸው የጎል ክልል በፍጥነት እየቀረቡ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደረጉበት ነበር።

ከእረፍት በፊት በ13ኛው ደቂቃ የወላይታ ድቻው አላዛር ፋሲካ በግንባሩ ገጭቶ የሞከራት ሙከራ ለጥቂት ከግቡ ቋሚ በላይ ስትሄድ በ33ኛው ደቂቃ ደግሞ የመከላከያው ተስፋዬ በቀለ ወይም ጃምቦ የሰራውን ስሀተት ተጠቅሞ የወላይታ ድቻው ባዬ ገዛኸኝ ኳስ ቢያገኝም በጀማል ጣሰው ጥረት ጎል ከመሆን ድናለች። ከሰበታ ከነማ መከላከያን የተቀላቀለው ወጣቱ ቁመተ መለሎ ቴዎድሮስ በቀለ ደግሞ በ36ኛው ደቂቃ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምባት የቀረች የጎል እድል ተጠቃሽ ሙከራዎች ናቸው። 

ከእረፍት መልስ ግን አምስት ያለቀላቸው የጎል ሙከራዎች ተደርገው ሶስቱ መረብ ላይ አርፈዋል። የመጀመሪያዋን ጠንካራ ሙከራ ያደረገው የመከላከያው ሙሉዓለም ጥላሁን ሲሆን ሙሉዓለም የወላይታ ድቻ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቀሞ ክለቡን መሪ ያደረገች ጎል አስቆጠረ። የወላይታ ድቻው አርጋው ባደገ የሞከራት ኳስ ደግሞ የግቡን ቋሚ ለትማ ተመልሳለች። ከእረፍት በፊት በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ከጎሉ ብረት በላይ የወጣችበት አላዛር ፋሲካ በ75ኛው ደቂቃ በግንባሩ ገጭቶ ክለቡን አቻ ያደረገች ጎል አስቆጠረ። 

ከጎሏ በኋላ በሁለቱም ክለቦች በኩል ተደጋጋሚ የጎል ሙከራዎች የተካሄዱ ሲሆን ተመልካችንም ብድግ ቁጭ ያደረጉ ነበሩ። በ88ኛውና በ89ኛው ደቂቃ ሁለት ሙከራዎችን ያደረገው የመከላከያው ሳሙኤል ሳሊሳ አንዷን ወደ ጎል ቀይሮ ክለቡን ከሶስት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ አሸናፊነት መልሷል። ሳሙኤል ላስቆጠራት ሁለተኛ ጎል የቡድን አጋሩ ማራኪ ወርቁ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ሲሆን ከተመልካችም አድናቆትን አሰጥቶታል። ሳሙኤል ጎሏን ያስቆጠረበት መንገድም የልጁን ችሎታ ያስመሰከረ ነበር። 

ክልል ላይ በተካሄዱ ሶስት ጨዋታዎች ደግሞ ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራ በኤዶም ብቸኛ ጎል ወልድያ ከነማን አንድ ለባዶ በማሸነፍ በመጀመሪያው ዙር ደርሶበት የነበረውን የአንድ ለባዶ ሽንፈት ማወራረድ ችሏል። ከስፍራው የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው ወልድያ ከነማ “የዳኛ በደል ደርሶብኛል” በማለት ቅሬታውን ሲገልጽ የዳሽን ቢራ ተጠባባቂ አሰልጣኝ ካሊድ መሃመድ በበኩሉ በጥሩ ጨዋታ ማሸነፍ በመቻሉ መደሰቱን ገልጿል። 

ይርጋዓለም ላይ የተካሄደውን የሲዳማ ደርቢ ደግሞ ሃዋሳ ከነማ በተመስገን ተክሌ ብቸኛ ጎል አንድ ለባዶ ማሸነፍ ችሏል። ሲዳማ ቡና የትናንቱን ጨምሮ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን በመሸነፉ ከዋንጫው ፉክክር እንዳይርቅ ተሰግቷል። ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአራት ነጥብ ዝቅ ያለ ሲሆን አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ደደቢትንም የሚበልጠው በሁለት ነጥብ ብቻ ነው። ፈረሰኞቹ ወደ አሰላ ተጉዘው ሙገር ሲሚንቶን ሁለት ለአንድ አሸንፈው ተመልሰዋል። ድሉን ተከትሎም ነጥባቸውን 42 በማድረስ ከተከታያቸው በአራት ነጥብ ልቀው ሊጉን በብቸኝነት እየመሩ ይገኛሉ። 

ኮከብ ጎል አግቢነቱን ሁለቱ ናይጄሪያውያን አጥቂዎች የሲዳማ ቡናው ሳሙኤል ሳኖሜ እና የንግድ ባንኩ ፍሊፕ ዳውዝ በእኩል 14 ጎል ይመሩታል። የወራጅ ቀጠናውን ወልድያ ከነማ እና ሙገር ሲሚንቶ ይዘውታል።

ካሳ ሀይሉ 
ለኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Gizachew [992 days ago.]
 Good riport

abate alemu [988 days ago.]
 betam tiru new.ine gazetenga silehonku tifeligungalachihu?melisulingi.

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!