የአሰልጣኝ ዮሃንስ ሣህሌ ፈተናዎችና ተስፋዎች- ክፍል አንድ
ሚያዚያ 29, 2007

ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሣህሌ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ አዲስ አይደለም። ከተጫዋችነት እስከ ቴክኒክ ዳይሬክተርነት የዘለቀው የእግር ኳስ ታሪኩ በቅርቡ ለደደቢት እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ አድርጎት ቆይቶ ነበር። ደደቢት የአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ውጤት አልባ ጉዞ ተስፋ ሲያስቆርጠው ንጉሴን አሰናብቶ በምትኩ ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሣህሌን መቅጠሩ ይታወሳል። “ከመጀመሪያውም ያልተሰራ ቡድን ስለሆነ ደደቢት ንጉሴን አሰናብቶ ዮሃንስን ቢቀጥርም የተለየ ውጤት መፍጠር አይችልም” ተብሎ ቢተችም አሰልጣኝ ዮሃንስ ሣህሌ  ግን የትም አይደርስም የተባለውን ቡድን ገና አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ነጥቡን 34 በማድረስ 21 ጨዋታዎችን ካካሄደው ኢትዮጵያ ቡና በላይ መሆን ችሏል። ደደቢት ከሰበሰባቸው 34 ነጥቦች 25ቱን የሰበሰበው በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሣህሌ እየተመራ መሆኑ እና እንደ ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መከላከያ አይነት ጠንካራ ክለቦችን ማሸነፍ መቻሉ የአሰልጣኙ ቅጥር የዘገየ እንጅ ስህተት ነው ብሎ መጥራት አይቻልም። 

አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶን “ውጤት ማምጣት አልቻሉም” ብሎ ያሰናበተው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለመመለስና በቻን ዋንጫም ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሣህሌን መቅጠሩን አሳውቋል ። ፌዴሬሽኑ ለኢንስትራክተር ዮሃንስ ሃላፊነቱን ሲሰጠው አያይዞም ግዴታ አሸክሞታል። ለመሆኑ አሰልጣኝ ዮሃንስ ላይ የተጫነው ግዴታ ምንድን ነው? ግዴታውንስ እንዴት ሊወጣው ይችላል? የሚሉትን ነጥቦች ከዚህ በታች እንደሚከተለው እንዳስሳለን። 

በአራተኛው የቻን ዋንጫ መሳተፍ ቀላሉ የቤት ስራ

የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአህጉሩን እግር ኳስ ለማሳደግ ይረዳል ብሎ ከቀየሳቸው እቅዶች አንዱ በአገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚወዳደሩ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት “ቻን” የሚባለውን ውድድር ማካሄድ ነው። ውድድሩ ከዚህ ቀደም ለሶስት ጊዜያት ተካሂዶ ኢትዮጵያ በአንዱ መሳተፍ ችላለች።
 
በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች “ፊታቸውን የሚነሱት” እየተባለ የሚተቸው ቻን ዋንጫ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የእግር ኳስ ደረጃቸው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች ውድድሩ መዘጋጀቱና በመድረኩ ተሳታፊ መሆን ጠቀሜታው የጎላ ነው። በዚህ ውድድር ለመሳተፍ በምድብ ድልድል ተደልድሎ በማጣሪያ ማለፍ አይጠበቅም። ከአንድ አገር ጋር በደርሶ መልስ አሸናፊ የሆነ ቡድን በቀጥታ የሚያልፍበት ውድድር ነው። በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ በሶስተኛው የቻን ዋንጫ ለመሳተፍ የእግር ኳስ ደረጃዋ ከእሷ የባሰ ዝቅተኛ ከሆነችው ሩዋንዳ ጋር 180 ደቂቃ ተጫውታ አንድ እኩል በመለያየቷ በመለያ ፍጹም ቅጣት ምት አሸናፊ በመሆኗ ነበር ያለፈችው። ዘንድሮስ? ዘንድሮ አገሪቱ የተደለደለችው ከጎረቤት አገር ኬኒያ ጋር ነው። በረጅም ርቀት ሩጫ ተፎካካሪ የሆኑት ሁለቱ አገሮች ለቻን ዋንጫ ለማለፍ ደግሞ ሊፋለሙ ነው ማለት ነው።

ኬኒያውያን ሲነሱ አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ አብሮ ይነሳል። የሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴንና የኬኒያውያንን አይረሴ ፉክክር እናስታውስና ወደ ዋናው ጉዳያችን እንመለሳለን። በደቡብ ኮሪያ ሲኦል ተካሂዶ በነበረው የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና  አትሌት ሀይሌ ገብረሥላሴ ሳይታሰብ ከኋላ አፈትልኮ የሩጫውን የመጨረሻ ክር ሊበጥስ ሲል ከጀርባው ያረፈበትን ጠንካራ ቡጢ በርካታ ኢትዮጵያውያን አንዘነጋውም። አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴም ቢሆን ሁኔታውን ሲያስታውስ በፈገግታ ታጅቦ ነው። ሀይሌን በቡጢ የደሰለቀው ማቹካ የተባለው ኬኒያዊ አትሌት ነው። 

በሌላ ጊዜ ደግሞ በሲድኒ ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር ሩጫ የወርቅ ዳሊያውን ለማግኘት የሰከንዶች እድሜ ብቻ የቀረው ኬኒያዊው ፖል ቴርጋት ወርቁን አገኘሁ ብሎ ተስፋ ሲሰንቅ ኢትዮጵያዊው “ልማደኛ” ፖል ቴርጋትን በአንገቱ ቀድሞ በመግባት የወርቅ ሜዳሊያው ባለቤት ሆነ። ሌላኛው ኬኒያዊ አትሌት ዳንኤል ኮመን ደግሞ “ከሀይሌ ጋር ከዚህ በኋላ መሮጥ አልፈልግም” ብሎ በይፋ መናገሩ ይታወሳል። 

በ1997 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ተካሂዶ የነበረው የሴካፋ ዋንጫ ሲነሳ የድሉ ባለቤት የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ እና አማካይ ተከላካዩ አንተነህ አላምረው ቀድመው ይታወሳሉ። ብሔራዊ ቡድኑ ዋንጫውን ከማንሳቱ በፊት በግማሽ ፍጻሜው ከኬኒያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ሲጫወት ማሸነፍ የቻለው በመለያ ፍጹም ቅጣት ምት ነበር። ዘንድሮስ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የቀደመ የበላይነት ታሪካችንን ያስቀጥላል ወይስ ታሪክ ይገለበጣል? ለማንኛውም የተጋጣሚያችንን ደረጃ የተመለከተው እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኬኒያን አሸንፈን ወደ አራተኛው የቻን ዋንጫ ማለፍ አለብን የሚል ግብ አስቀምጧል። ይህንን ግብ ለማሳካት ደግሞ አዲሱ አሰልጣኝ ከአሁኑ ስራውን የሚጀምር ከሆነ ፈተናውን በቀላሉ በማለፍ ወደ ትልቁ ፈተና ይሸጋገራል ብለን እናስባለን። ቀጣዩ ፈተናስ?

ይቀጥላል!!

ካሳ ሀይሉ 
ለኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Babi [967 days ago.]
 በጣም እኮ ነው የሚገርመው ቢኒያም አሰፋ ስንት ዓመቱ ነው ለብሄራዊ ብድን የተመረጠው በወጌሻነት ነው እንዴ እነ አዳነ ግርማ ገና ብዙ ነገር ለለብሄራዊ ብድናችን መስራት እየቻሉ ለወጣቶች ቦታቸውን ሲለቁ ቢኒያም ደግሞ ኮች በመሆኛው ሰዓት ናሽናል ቲም መጠራቱ ይገርማል ይደንቃልም ሃሃሃሃሃ አይ ኮች ዮሃንስ ገና ከጅምሩ አስቂኝ የተጫዋቾች ምርጫ መርጠህ አስደምመኸናል አስቀኸናል፥፥ መመረጥ የሚገባቸው ሃገሪቱ ውስጥ ያሉት ሁለቱ ምርጥ የአማካይ ተካላካዮች ተስፋዬ አለባቸው እና ናቲን መዝለልህ የስፖርት ቤተሰቡን ማነጋገሩን ቀጥሏል ገና ወደፊት ብዙ የሚያስቁ ነገሮች ሰርተህ ስፖርት ቤተሰቡን ዘና ፈታ የምታደርገው ይመስለኛል

ግርማ ዘዉዴ [918 days ago.]
 ግርማ ዘዉዴ

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!