የፌዴሬሽኑና የኢንስትራክተር ዮሃንስ ሳህሌ የመጀመሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ
ግንቦት 01, 2007

በ1936ዓ.ም የተቋቋመው፣ በ1945 የዓለም ዓቀፉ እግር ኳስ ማህበር እንዲሁም በ1949 የአፍሪካ እግር ኳስ ማህበር አባል የሆነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ባለፈው ሳምንት አሰልጣኝ መቅጠሩ ይታወቃል፡፡ ፌዴሬሽኑ በዋና አሰልጣኝነት የተቀጠሩትን አቶ ዮሃኒስ ሳህሌን አስመልክቶ  ትናንት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ለተውጣጡ ጋዜጠኞች ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ፡፡ 
የፌዴሬሽኑና የኢንስትራክተር ዮሃንስ ሳህሌ የመጀመሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት አቶ ጁነዲን ባሻን ጨምሮ አዲሱ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አቶ ዮሃኒስ ሳህሌ ተገኝተዋል። ኢንስትራክተር ዮሃኒስ ሳህሌ ከቴክኒክ ኮሚቴ እሰከ ደደቢት ክለብ ዋና አሰልጣኝነት በሀገር ውስጥ እንዲሁም በአሜሪካን ሀገር የተለያዩ ክለቦችን ያሰለጠኑ በትምህርት ዘርፍም የባችለር ድግሪያቸውን በኮሙኒኬሽን ያገኙ ሰው መሆናቸወን በእለቱም ተገልጿል፡፡ 

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የመጡ ጋዜጠኞችች ስለ አሰልጣኙ ማንነትና የስራ ልምድ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ ከጥያቄዎቹ  ውስጥ አሰልጣኝ ዮሃኒስ ሳህሌ ለብሄራዊ ቡድኑ ይመጥናሉ ወይ? ማሪያኖ ባሬቶ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ እያገኙ ኢንስትራክተር ዮሃኒስ ሳህሌ በ75 ሺህ ብር መቀጠራቸው ፍተሃዊ ነው ወይ? የቀድሞ ብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በምርጫው ውስጥ ለምን አልተካተቱም? በምርጫው ላይ ያሉ ፕሮሰሶች ለመገናኛ ብዙሃን ግልጽ አልነበሩም ዛሬ ላይ ምርጫው ካለቀ በህዋላ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱ ለምን አስፈለገ? የቴክኒክ ኮሚቴው በእግር ኳስ ላይ ምንም ዓይንት እውቅና የሌላቸው ሆነው ለምን እንዲቀጥሉ ተደረገ? በቀጣይስ እንደ አዲስ ኮሚቴውን ለማቋቋም አልታሰበም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተው ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ 

አቶ ጁነዲን ባሻ በተነሱት ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸው ፌዴሬሽኑ የትኛውንም አሰልጣኝ ሲቀጥር ግልጽና የማያሻማ መንገድ ተጠቅሞ መሆኑንና አቶ ዮሃኒስ ሳህሌ ያላቸው ልምድ፣ የትምህርት ዝግጅት እና የአሰልጣኝነት ሰርተፊኬት ተገምግሞ ከሌሎቹ የተሻሉ በመሆናቸው መሾማቸውን ጠቁዋል፡፡ አቶ ዮሃኒስ ከፌዴሬሽኑ ጋር የተዋዋሉት ኢትዮጵያን ለ2017ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ለማሳለፍ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ ከሜዳ ጋር እና በተለይም ከትጥቅ፣ የወዳጅነት ጨዋታ ማመቻቸት ጋር፣ የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት መነጋገራቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ጁነዲን ገለጻ በቅርቡ እንኳ አንድ ተጨዋች ውጭ ሀገር ይዞ ለመሄድ ቪዛ ለማውጣት ሲሄድ የአዲስ አበባ መታወቂያ የሌለው ሆኖ መገኘቱ አሰገራሚ ሆኖባቸዋል፡፡  እንደዚህ ዓይነት ችግሮችን ለመቅረፍ ተጨዋቾቹም ሊያግዙ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ከአሰልጣኙ የስራ ዘመን ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ አሰልጣሹ ዛሬ ላይ የያዘው ቦታ ጠንክሮ ከሰራ ማንም የማያንቀሳቅሰው እንደሆነ፣ ለውጥ የማያመጣ ከሆነ ግን ራሱም መልቀቅ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለና የሚፈልጉትን መረጃ እንደሚሰጧቸው የጠቆሙት አቶ ጁነዲን «አሰልጣኝ መሾም እና መሻር በእግር ኳሱ የተለመደ ሂደት ነው፡፡ እኛም ባዘጋጀነው  መስፈርት መሰረት ከሃገር ውስጥና ከአገር ውጭ  የሚያሰለጥኑ ኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች መካከል የተሻለ ነው ብለን ያመንበትን አሰልጣኝ ዮሃንስን መርጠናል፡፡›› በማለት ምርጫው ፍትሃዊና ሁሉም ያስገቡት አሰልጣኞችን የመዘነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከደሞዝ ጋር ተያይዞ ለተነሳውም ጥያቄ ከወራት በፊት ለማሪያኖ ባሬቶ ለምን ይህንን ያህል ደሞዝ ይከፈላል? ሲሉ የነበሩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ዛሬ ላይ ለምን በዚህ ደሞዝ ቀጠራችሁ? ብለው መጠየቃቸው ትዝብት እንደፈጠረባቸው ጠቁመው ከዮሃንስ ጋር በተያያዘ የትኛውም ቀጣሪ ድርጅት ተቀጣሪው እስከተስማማ ድረስ በፈለገው ደሞዝ የማሰራት መብት እንዳለውና አቶ ዮሃንስም በሚከፈላቸው ደሞዝ ሙሉ በሙሉ ተስማምተው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በበኩላቸው ለዚህ ቦታ ይመጥናሉ ወይ? ተብሎ ለተነሳው ጥያቄ ሲመልሱ «የአሰልጣኝነት መስፈርቱ በመጫወት ከሆነ እስከ ብሄራዊ ቡድን ተጫውቻለሁ፣ በኮሙኒኬሽን ትምህርት የባችለር ድግሪ አለኝ፣ ልምድ ከሆነ 20 አመት በአሰልጣኝነት አሳልፌያለሁ፡፡ እግር ኳስ አለም አቀፍ ይዘት አለው ከተባለ የአለም አቀፍ ልምዴ ለምን አይቆጠርም? ለምሳሌ ፔፕ ጋርድዮላን መውሰድ ይቻላል፡፡ ጋርዲዮላ የባርሴሎናን ቢ ቡድን አነድ ዓመት ብቻ ያሰለጠነ ቢሆንም ዋናውን ክለብ አሰልጥኖ ውጤታማ ሆኖአል፡፡ እኔም አራተኛ ደረጃ ፍቃድ አለኝ፣ በኔ ደረጃ የሚገኙ አሰልጣኞች የአለም ዋንጫ ቡድኖችን እያሰለጠኑ ነው፡፡» ሲሉ ተደምጠዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብዙም ግልጽነት ባልታየበት የአሰልጣኝ ሹመት አቶ ዮሃኒስ ሳህሌን ለብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝነት በወር ያልተጣራ 75 ሺህ ብር በመክፈል የቀጠረ ሲሆን አሰልጣኝ ዮሃኒስ ሳህሌም በቅርብ ቀን ምክትል አሰልጣኞችን በመሾም ስራ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡  

ዜና ሪፖርታዥ
ይርጋ አበበ 
ለኢትዮ ፉትቦል


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!